ሩሲያ ሃይፐርሶኒክ የተባለውን ሚሳኤል በዩክሬኑ ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ መጠቀሟን ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ ጦር ኃይል ሃይፐርሶኒክ የተባለውን ተወንጫፊ ሚሳኤል በመተኮስ በምዕራብ ዩክሬን ውስጥ ከመሬት በታች የሚገኝን የጦር መሳሪያ ማከማቻ ማውደሙን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ከሞስኮ አስታወቀ።
ይህ ጥቃት ከተረጋገጠ 'ኪንዣል' ወይም ሳንጃ የተባለውን በአብዛኛው ሚግ-31 ከሚባለው የጦር አውሮፕላን ከአየር የሚተኮሰውን ተወንጫፊ ሚሳኤል ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ጦርነት ውስጥ መጠቀሟ ይሆናል።
ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ምንድን ነው?
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተለያዩ አጋጣሚዎች አገራቸው ከድምጽ በአምስት እጥፍ ፍጥነት በሚጓዘው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ላይ ስታወከናውን ስለቆየችው ተግባር በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።
የሚሳኤሉን ብቃት በሚመለከት ያሉ መረጃዎች እጅግ አስደናቂ ናቸው። የሩሲያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ይህ 'ኪንዣል' የተባለው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል እስከ 2,000 ኪሎ ሜትር ርቆ ያለን ኢላማ የሚመታ ሲሆን በሰዓት ከ6,000 ኪሎ ሜትር በላይ ይፈጥናል።
ነገር ግን ሚሳኤሉ ሊያደርስ ስለሚችለው ጉዳት ጥያቄዎች ይነሳሉ። በካርኒጌ የዓለም ሰላም ተቋም ውስጥ የኒውክሌር ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ጄምስ አክተን፣ ሚሳኤሉ የሚኖረው ከፍ ያለ ውጤት ላይ ጥያቄ አላቸው።
"ከፍ ያለ ውጤት ይኖረዋል ብዬ አላስብም። ሩሲያ ይህንን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን በመጠቀም ምን ያህል የበላይነትን እንደምታገኝ አለውቅም።"ይላሉ።
ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ከተተኮሱ በኋላ አቅጣጫቸውን ለመለየትና በፀረ ሚሳኤል ለመምታት አስቸጋሪዎች ናቸው። ምክንያቱም አየር ላይ እየተጓዙ አቅጣጫቸውን ለመቀየር ስለሚችሉ ነው።
ከጥቂት ወራት በፊት ፕሬዝዳንት ፑቲን አገራቸው በሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል በኩል ዓለምን እየመራች እንደሆነ በልበ ሙሉነት ተናግረው ነበር።
ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ በዚሁ ሚሳኤል አደረስኩት ስላለችው ጥቃት ቪዲዮ ይፋ አድርጋለች። በጥቃቱ በደቡብ ምዕራብ ዩክሬን ክሩሜንያ ድንበር 100 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኝ አንድ መንደር በሚገኝ የጦር መሳሪያ መከማቻ ላይ የተፈጸመ ነው።
ዙሪክ ውስጥ የደኅንነት ጥናቶች ማዕከል ባለሙያ የሆኑት ዶሚኒካ ኩኔርሮቫ እንዳሉት "ለማሳያነት የተደረገ ነገር ነው። ጥቅም ላይ ቢውል እንኳን ነጠላ ክስተት ይሆናል፤ ምክንያቱም ሩሲያ ጥቅም ላይ ልታውለው የምትችለው ከፍተኛ መጠን ያለው ሚሳኤል የላትም" ብለዋል።
የሚሳኤሉ ውጤት
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ይህን 'ኪንዣል' የተባለውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን ከአራት ዓመት በፊት ይፋ ሲያደርጉ፣ አገራቸው እየገነባቻቸው ካሉት የማይበገሩ የጦር መሳሪያዎች አንዱ እንደሆነና የጠላትን መከላከያ የሚሰብር ብለውት ነበር።
ሌሎቹ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች 'ዚርኮን' እና 'አቫንጋርድ' የሚባሉ ሲሆኑ ሁለቱም ፈጣንና በጣም ረጅም ርቀትን የሚጓዙ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች ናቸው።
'ኪንዣል' የተባለው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መደበኛ እና የኒውክሌር አረር ሊሸከም ይችላል። ይህንን ሚሳኤል የሚያስወነጭፉት ሚግ-13 ተዋጊ አውሮፕላኖች በርካታ የአውሮፓ ከተሞችን ለመድረስ ወደሚቻልባት የሩሲያ ካሊኒንግራድ እንዲሰማሩ ተደርገዋል።
ሩሲያ ይህንን ዘመናዊ ሚሳኤል በዩክሬኑ ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመች ሲሆን ጥቃቱ ከየት እንደተፈጸመ ምንም የሚያመለክት ነገር አልተገኘም።
"ምዕራባውያን መሳሪያዎችን ወደ ዩክሬን ለማሻጋገር እየሞከሩ ስለሆነ ፑቲን ተቆጥተዋል። ስለዚህም የዚህ ሚሳኤል ጥቅም ላይ መዋል ለምዕራባውያን የተላከ ማስጠንቀቂያ ነው" ሲሉ ኩኔርቶቫ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ኢላማውን በመምታት በኩል ያለው ብቃት አጠያያቂ ነው፤ ስለዚህ በጦርነት ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም።"
ጄምስ አክተን እንደሚሉት 'ኪንዣል' ለተዋጊ አውሮፕላኖች ተብሎ የተዘጋጀው ኢስካንደር ሚሳኤል ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር፤ ነገር ግን ኢስካንደር ሚሳኤል ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከመሬት ላይ በሩሲያ ኃይሎች ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። ይህ ሚሳኤል ከአየር ላይ ከሚተኮሰው በታም ዝቅ ያለ ርቀትን የሚጓዝ ነው።
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት እንዳለው ሩሲያ ከሞላ ጎደል ያሏትን ኢስካንደር ሚሳኤሎችን በሙሉ በጦርነቱ የመጀመሪያ 20 ቀናት ውስጥ በዩክሬን ላይ ተጠቅማቸዋለች።
አንድ የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣን ከቀናት በፊት እንደተናገሩት የሩሲያ ኃይሎች ከ1,080 በላይ ሚሳኤሎችን ወረራው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ተኩሰዋል።

ስለጦርነቱ ተጨማሪ ዘገባዎች
















