በተደራጁ ቡድኖች ተጨማሪ ስጋት የተጋረጠባቸው ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ

ጥቃት በመፍራት ሱቁን የሚዘጋ ባለሱቅ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጥቃት በመፍራት ሱቁን የሚዘጋ ባለሱቅ

ከቀናት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ ላቀና ፖሊሶችን በየቦታው በተጠንቀቅ ሲንቀሳቀሱ ይመለከታል።

የአሌክሳንድራ ደግሞ የተለየ ነው።

ምነው ካሉ የአካባቢው ነዋሪዎች እና በንግድ በተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎች መካከል ጠብ ይቀሰቀሳል በሚል ስጋት የሚል ምላሽ ያገኛሉ።

ስጋቱ አሁንም እንዳለ ነው።

ስጋት ከገባቸው መካከል ኢትዮጵያዊያንም ይገኙበታል።

ለዚህ ሁሉ ምክንያት ከሆነው ጉዳይ እንጀምር።

እንደ አሌክሳንድራ አይሁን እንጂ በመላዋ ደቡብ አፍሪካ የኑሮ ልዩነት በሰፋት ይታይባታል።

ለዚህ ሁሉም የራሱን ምክንያት ያስቀምጣል።

አንዳንዱ ሥርዓቱ ነው ይላል።

ሌሎች ደግሞ "መጤዎች ናቸው ለዚህ ያበቁን" ባይ ናቸው።

ችጋር ተጫወተብን ብለው የሚያማምርሩ ደቡብ አፍሪካዊያን ባሉባት አገር በሰማይ በምድር ብለው ገቡ ስደተኞች ደግሞ በኑሮ እየበለጸጉ ነው።

ይህን አወዛጋቢ ጉዳይ አንግበው ሁለት ቡድኖች ብቅ ብለዋል።

'ዘ አሌክሳንድራ ዱዱላ ሙቭመንት' እና 'ኦፕሬሽን ዱዱላ' የተባሉ።

ሁለቱም ሰነድ አልባ የሆኑ መጤ አፍሪካውያን ከአገራቸው እንዲወጡ የሚቀሰቅሱ ናቸው።

ሆድ ለባሰው. . . እንደሚባለው ሆነና ተገፍተናል፣ የድርሻችንን አላገኘንም በሚለው ሕዝብ ዘንድ ሃሳባቸው ገዢ አግኝቶላቸዋል።

እነዚህ ቡድኖች የሚፈልጉት ምንድን ነው?

በአገሪቱ ዜጎች እና በሰነድ አልባ ስደተኞች መካከል ለሚፈጠረው ውጥረት ቀዳሚው ምከንያት ድህነት ነው። ትክክልም ይሁኑ አይሁኑ እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያን ለሚያነሷቸው ቅሬታዎች ምክንያት የሚሉት እነዚህኑ ሰነድ አልባ ስደተኞች ነው።

ዱዱላ በዙሉ ቋንቋ "አስወጧቸው" ወይንም "ይሂዱልን" ማለት ነው። ይህ ደግሞ ቡድኖቹ ምን እንደሚፈልጉ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ምንም እንኳ እነዚህ ሁለት ቡድኖች የተለያዩ ቢሆኑም የመደራጀታቸው ምክንያት ግን ተመሳሳይ ነው፤ ሁለቱም ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች ከደቡብ አፍሪካ እየመነጠሩ ማስወጣት።

ይህንን በማድረጋቸውም ደግሞ ለደቡብ አፍሪካውያን ሥራ እና የንግድ በሮችን እንደሚከፍቱ በብርቱ ያምናሉ።

ይህ ነው ለኢትዮጵያዊያኑም ስጋት ሆነው።

ይህ ነው እንቅልፍም የነሳቸው።

ባለፈው ወር የዱዱላ ቡድን አባላት ሶዌቶ ውስጥ ሰልፍ ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ወር የዱዱላ ቡድን አባላት ሶዌቶ ውስጥ ሰልፍ ሲያደርጉ

"ጥያቄያቸው የውጭ ዜጎች ይውጡ እኛ ንግዱን እንቆጣጠር የሚል ነው" ሲል ሃሳቡን ለቢቢሲ ያጫወተው መኖሪያውን በጆሃንስበርግ ያደረገው ገዛኸኝ ሱማሞ ነው።

ኢትዮጵያውያንን 'ምን የማይሠሩት አለ?' ሲሉ እንደሚገልጿቸው ይናገራል።

ኢትዮጵያዊያንን 'ቤት ሠራተኛ፣ አስተናጋጅ እና ታክሲ አሽከርካሪዎች እነሱ ናቸው' በሚል ነው 'ምን የማይሠሩት አለ' ሲሉ የሚገልጿቸው።

ይህን ሁሉ የሚሠሩት ኢትዮጵያዊያን ናቸው እንግዲህ ስጋት የገባቸው።

ሱቄ ይዘረፍ ይሆን፣ እባረር ይሆን፣ ከባሰም ህይወቴን አጣ እሆን እስከሚል ድረስ ያለ ስጋት።

ከዚህ ቀደም "በዚህ ጎድተውናል። በሰው አገር የሠራነውም ከንቱ አድርገውታል" ይላል ገዛኸኝ።

"አሌክሳደንራ የሚባል ቦታ ላይ የውጭ ዜጎች ቢዝነስ ይልቀቁ የሚል እንቅስቃሴ ቢኖርም የሕግ አካላት ተቆጣጥረውታል" ከሰሞኑ ግን ጉዳት አላደረሱም ይበል እንጂ አንድ ኢትዮጵያዊ ህይወቱ ማለፉን አጫውቶናል።

"እንዴት አንደሞተ አይታወቅም" የሚለው ገዛኸኝ "እንዴት አንደሞተ አይታወቅም ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ተገድሏል" ካለ በኋላ ከዚሁ እንቅስቃሴ ጋር ስለመያያዙ እየተካታተሉ መሆኑን ጨምሮ ጠቁሟል።

የአዲሱ ሕግ ሌላ ስጋት

ስሙን እንዳንጠቅስ የጠየቀን የፒተመርስበርግ ነዋሪ ደግሞ በአካባቢያቸው ብዙም ስጋት አለመኖሩን አጫውቶናል።

በሌሎች ቦታዎች ግን ስጋት ተፈጥሮ እንደነበር ሰምቷል።

አንድ ስደተኞችን ከአገር ሊያስወጣ ነው የተባለ ሕግ ሊጸድቅ ነው ከተባለ በኋላ የዱዱላ አባላት እንቅስቃሴ ጨምሯል ይላል።

"ዱዱላ የሚባለው ቡድን ስደተኛውን በኃይል እናስወጣለን በሚል ፖሊስንም ሆነ የመንግሥትን ሕግ አንጠበቅም እያሉ በእራሳቸው እየየሞከሩ ነው።"

እንደ ገዛኸኝ ከሆነ የዚህ ቡድን አባላት 'ውጡ ከተባሉ ይወጣሉ።' አድርጉ የተባሉትን ለማድረግም ሁሌም ዝግጁ ናቸው።

የቡድኑ ዓላማ የውጭ አገር ዜጎችን ማስወጣት ነው የሚለው ገዛኸኝ "ደቡብ አፍሪካውያን ሥራ አጥተው ሲቪ ይዘው ቁጭ ብለዋል። ሲቪያችሁን ይዛችሁ ለተቃውሞ ውጡ በሚል ነው የሚቀሰቅሰው" ይላል።

በዚህም ነው ስጋቱ እየጨመረ የመጣው።

ይህንንም "አሁን ሕዝባችን በጣም ሰቀቀን ውስጥ ነው ያለው። መቼ መጠው ያቃጥሉናል እያለ ድባቴ ውስጥ የገባው ቁጥር ብዙ ነው። ሆስፒታል ብዙ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ይሄዳሉ። ብዙ ችግር እየፈጠረብን ነው" ሲል ያስረዳል።

አሌክሳንድራ ውስጥ ያሉ የዱዱላ ደጋፊዎች በውጭ ዜጎች ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አሌክሳንድራ ውስጥ ያሉ የዱዱላ ደጋፊዎች በውጭ ዜጎች ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ

ንብረትንና እራስን ለመጠበቅ ክፍያ

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀን ሌላው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ባሉበት አካባቢ በየወሩ ክፍያ እየፈጸማችሁ እንዳትወጡ እናዳረጋለን ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር እየሠሩ መሆኑን ጠቅሷል።

"እስካሁን ጉዳት የደረሰበት የለም። እኔ ባለሁበት ጉዳት የደረሰበት የለም። እንቅስቃሴው ግን አለ። ኅብረተሰቡ ዘንድ ስጋት ቢኖርም አሁን ጥሩ ይመስላል። በተለይ በእኛ [በኢትዮጵያውያን] ዙሪያ ጥሩ አመለካከት አለ" ብሏል።

በተለይም ስደተኞችን ሊያስወጣ ነው የሚለው ሕግ ነው ስጋት የፈጠረው ባይ ነው።

እንደገዛኸኝ ከሆነ ከዚህ ዱዱላ ከተባለው ቡድን ጀርባ ኢትዮጵያዊንም ተሳታፊ ናቸው።

ለምን? ምንስ ይጠቀማሉ? ሲባል "በየጊዜው ግርግር ሲነሳ ግርግሩን ለማረጋጋት በሚል ብር ይሰባሰባል። ኢትዮጵያዊያኑ ከእሱ [ከዱዱላ ቡደን አባላት] ጋር ብር ይካፈላሉ" ሲል ምላሽ ይሰጣል።

ቢቢሲ የዱዱላ እንቅስቃሴን በተመለከተ ከዚህ ቀደምም ዘግቦ የነበረ ቢሆንም ስለኢትዮጵያዊን ተሳትፎ ግን ማረጋገጥ አልቻለም።

እንደ መረጃ ሰጪያችን ከሆነ ቀደም ሲል የነበረው ችግር ነው በኢትዮጵያዊያኑ አዕምሮ ውስጥ እየተመላለሰ የሚገኘው።

"'እንዴት ይጸድቃል? እንዴት ይሆናል?' የሚል አለ። ብዙ ስደተኛ አለ። ወረቀት የሌላቸው ብዙ ናቸው። ቤተሰቡ፣ ወንድሙ ወይም ጓደኛው ወረቀት የሌለው ስላለ ምን ይሆናሉ? የሚል አለ። በዚህ አሳበው እንደበፊቱ ዝርፊያ እና የተለየያዩ ችግሮች ይከሰታሉ የሚል ስጋትም አለ" ብሏል።

ባለፉት ቀናት ነገሮች የተረጋጉ ቢመስሉም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ተመሳሳይ ጥሪ ከቡድኑ እየቀረበ ነው።

". . . ዝግጅት እያደረጉ ነው" የሚለው ገዛኸኝ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናትም ኢትዮጵያዊያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

ስደተኛው መኖሪያ ፈቃድ ይሰጠኛል ብሎ ሲጠብቅ ይህ ማጋጠሙ ተገቢ አይደለም ይላል።

ይህንን እንቅስቃሴ የሚቃወሙ ሰዎችን ጭምር በግል ዒላማ መሆናቸውን ይገልጻል።

በዚህ ምክንያትም በ37 ከተሞች እየተዘዋወረ ኅብረሰተቡን ለማንቃት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጿል።

ይህም በተወሰኑት ከተሞች ተጀምሯል። በሚቀጥሉት ቀናትም ለዚሁ ሥራ ወደ ተለያዩ ከተሞች እንደሚያቀና አጫውቶናል።

በደቡብ አፍሪካ ያሉ ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ጉዳይ ዝም የማይሉ መሆናቸውን ገዛኸኝ ደጋግሞ ይጠቅሳል።

ለህዳሴው ግድብ ቦንድ ከመግዛት ባለፈ በተለያዩ አገርን በሚደግፉ እንቅስቃሴዎች መሳተፋቸውንም በአስረጂነት ያነሳል።

ደቡብ አፍሪካ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስለሚያደርግላቸው ድጋፍ ሲጠየቅ ኤምባሲው አሁን ትኩረቱ በሌላ ጉዳይ ላይ መሆኑን ይገልጻል።

ቢቢሲም ከዚሁ የኢትዮጵያውያን ስጋት አንጻር የኤምባሲውን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም።

ገዛኽኝ በዱዱላ እየታየ ያለው ስሜት ይህ ግን የሁሉም ደቡብ አፍሪካዊያን ፍላጎት አለመሆኑን ያሰምርበታል።

ስደተኞች ያላቸውን ትልቅ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በመጥቀስ የሚከራከሩ እንደ ታቦ ምቤኪ (የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ናቸው) ያሉ ፖለቲከኞች መኖራቸውም ተስፋ ሰንቆላቸዋል።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ደግሞ የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ ኤኤንሲ ፓርቲ አባል የሆኑ አንድ ሚንስትር 'ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ መልስ እንሰጣለን' በማለታቸው እነገዛኸኝ ትንሽም ቢሆን የተስፋ ጭላንጭል እያዩ ነው።