በደቡብ አፍሪካው ነውጥ መጠነኛ ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ተገለጸ

ደቡብ አፍሪካ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በደቡብ አፍሪካ በተነሱ የተቃውሞ ሰልፎች እና ነውጥ የኢትዮጵያዊያን ሕይወት አለማለፉ ተገለጸ።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵዊያን ሕይወት ባያልፍም ጉዳት የደረሰባቸው ግን አሉ።

ጥቂት ኢትዮጵያውያን መጠነኛ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው፤ ሕክምና ያገኙ እንዲሁም በመታከም ላይ ያሉ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

"ሙሉ ለሙሉ ንብረታቸው ወድሟል"

ከ15 ዓመታት በላይ በስደት ነው የኖርኩት የሚለው ኮስሞስ ገብረሚካኤል የደርባን ነዋሪ ነው።

ከሰሞኑ በደቡብ አፍሪካ ከተነሳው አመጽ እና ረብሻ ትልቁ የሚባለው በደርባንና አካባቢው መከሰቱን ይገልጻል።

በዚህም መጠነ ሰፊ ጉዳት ቢደርስም፤ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ከሚደርስባቸው ጉዳት አንጻር የአሁኑ አነስ ያለ መሆኑን ጠቁሟል።

በእስካሁኑ አመጽ "በግሌ ስለሞቱ ኢትዮጵያዊያን የደረሰኝ መረጃ የለም። እንደ አክቲቪስት ስለማገለግል ብዙ መረጃ ይደርሰኛል። ነገር ግን ስለዚህ የደረሰኝ መረጃ የለም" ሲል ይገልጻል።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊያን በንግድ ሥራ መሠማራታቸውን የሚገልጸው ኮስሞስ፤ እነዚህም በሦስት ሊመደቡ የሚችሉ መሆናቸው ይጠቁማል።

የመጀመሪያዎቹ 'ሎኬሽን' በሚባሉ አካባቢዎች የሚሠሩ ናቸው። 'ሎኬሽን' ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ናቸው።

በእነዚህ አካባቢዎች በአነስተኛ ሱቅ የሚተዳደሩ ኢትዮጵያዊያን ሲኖሩም፤ አብኛዎቹን በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ቁጥር ይይዛል።

በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚሠሩ ኢትዮጵያዊያን "ሙሉ ለሙሉ ንብረታቸው ወድሟል" ብሏል ኮስሞስ ለቢቢሲ ሲገልጽ።

በሎኬሽን ለሚሠሩ ነጋዴዎች እቃዎችን በማቅረብ እና በማከፋፈል የሚሠሩ ኢትዮጵያዊን በሁለተኛው ምድብ ሲገኙ ሆቴሎች፣ የባሕል ልብስ መሸጫዎች እና ግሮሰሪዎችንም ያቀፉ ናቸው።

እነዚህኛዎቹ ደግሞ ቀደም ሲል መጤ ጠል [ዜኖፎቢክ] ጥቃቶች ከደረሱ በኋላ አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ለመጠበቅ ተደራጅተው በመንቀሳቀሳቸው የደረሰባቸው ጉዳት አነስተኛ ነው ይላል።

አቅም ያላቸው እና በሦስተኛው ምድብ የሚገኙት ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የንግድ እንቅስቃሴያቸውን የሚያደርጉት በትላልቅ የንግድ ማዕከላት [ሞሎች] ውስጥ ሲሆን "በእነዚህ ውስት የሚሠሩ ሙሉ ለሙሉ ንብረታቸውን ያጡበት ሁኔታ ነው ያለው" ብሏል ኮስሞስ።

አያይዞም፤ "ትኩረት የተደረገው እነዚህ ሞሎች ላይ በመሆኑ የተረፈ ሞል የለም። ጭሱ እንኳን እሳተ ገሞራ እንደፈነዳ ነው። ጭሱ እስካሁን አልጠፋም። ከሁለት ቀን በኋላም ብዙ ሕንፃዎች ተቃጥለዋል" ብሏል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው ኤምባሲ 'ደብዳቤ ከመጻፍ እና መልዕክቶችን ከማስተላለፈው ውጭ' ያደረገውን ድጋፍ አላየሁም ያለው ኮስሞስ፤ "የጠፋው ጠፍቷል። ሌላውን ሕ ብረተሰቡ ከመኖሪያው እስከ ቢዝነሱ መትረፍ ያለበትን አትርፏል" ሲል ገልጿል።

"ከዜጎቻችን ሕይወቱ ያለፈ የለም"

በደቡብ አፍሪካ በፕሮቴሮሪያ ኤምባሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም እንደሚሉት፤ ባለፉት ቀናት በደቡብ አፍሪካ የተከሰተው ነውጥ እንደ ከዚህ በፊት አመጾች የውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጠረ አይደለም።

"ትላልቅ የንግድ እና የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ነው። ተቋማቱን ማውደም መዝረፍ እና ማቃጣል ነው" ብለዋል።

72 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ጠቅሰው "እስካሁን ባለን መረጃ ከዜጎቻችን ሕይወቱ ያለፈ የለም። ጥቂት ዜጎቻችን የተወሰነ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። እነዚህም በአቅራቢያቸው በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ሕክምና ተከታትለዋል። አንዳንዶቹም ሕክምና እየተከታታሉ ነው" ሲል ገልጸዋል።

በትላላቅ የንግድ ማዕከላት እና 'ሎኬሽን' ያሉ የኢትዮጵያዊያን ሱቆች መዘረፋቸውን እና መቃጠላቸውን አስታውቀው "የጥፋቱ እና የውድመቱ መጠን ወደፊት ነገሮች ሲረጋጉ የምናየው ይሆናል" ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በየአካባቢው በመደራጀት ራሳቸውን እና ንብረታቸው ከመጠበቅ ባለፈ ኤምባሲው እና የኮሚውኒቲ ሚዲያን በመጠቀም በተላለፈው መልዕክት ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

እንደ አምባሳደር ሽፈራው ከሆነ ባለፉት ሁለት ቀናት መረጋጋት እየታየ ነው።

የአገሪቱ መንግሥትም መከላከያ ሠራዊቱን ማሰማራቱን ጠቅሰው፤ "እነዚህን ተከትሎ ቶሎ ሱቅ መክፈት ላልተጠበቅ ጥቃት እንዳያጋልጥ እንዲጠነቀቁ እና ተደራጅተው መጠቃቸውን እንዲቀጠሉ በኤምባሲው ማኅበራዊ ድረ ገጽ እና በማኅበረሰብ መገናኛ ብዙኃን እየተሠራ ነው" ብለዋል።

ከማኅበረሰቡ የሚነሱ መልዕክቶችን የሚመለከታቸው የደቡብ አፍሪካ የመንግሥት አካላት ጋር በማድረስ በትኩረት እየሠሩ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደሙ በተለየ ሁኔታ የአሁኑ በደቡብ አፍሪካ ነውጥና የንብረት ውድመት "ታላላቅ የማምረቻ፣ የንግድ እና የኢኮኖሚ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ነው። ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ በአነስተኞቹ ላይ ሳይሆን ትላልቆቹ ላይ ያነጣጠረ ነው። በትላላቅ የገበያ ማዕከላት የሚሠሩ ሱቆች ተዘረፈፈዋል፣ ተቃጥለውል፣ ወድመዋል። በሎኬሽንም ይሄው ሆኗል ብለዋል።

ትላልቆቹ የንግድ ተቋማት በኢንሹራንስ እንደሚሸፈበኑ አስታውቀው፤ አነስተኛዎቹ ደግሞ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉም ነገር ወደ መደበኛው ሥራ ሲመለስ ማኅበረሰቡ የሚደጋገፍበት አካሄድ እንደሚኖር ጠቁመዋል።

በደቡብ አፍሪካ የተፈጠረው ምንድን ነው?

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማን እስር ተከትሎ በመላው አገሪቷ የተቃውሞ ሰልፎች ተቀስቅሰዋል።

ጃኮብ ዙማ ከቀናት በፊት እጃቸውን ለፖሊስ ከሰጡ በኋላ የቀድሞው ፕሬዝደንት ደጋፊ የሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣት ጀምረዋል።

ፖሊስ እንደሚለው በጃኮብ ዙማ የትውልድ ቦታ ክዋዙሉ-ናታል ተቀስቅሶ በመላው አገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣውን አለመረጋገት ወንጀለኛ ቡድኖች መጠቀሚያ እያደረጉት ነው።

ሰኞ ከሰዓት ወደ 200 የሚደርሱ መገበያያ ሕንፃዎች መዘረፋቸውን የደቡብ አፍሪካ የንግድ ማኅበረሰብ መሪ ቡሲሲዌ ማቩሶ መናገራቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።

በሶዌቶ የሚገኙ መደብሮችም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ኤቲኤም ማሽኖች ተሰብረዋል። ሬስቶራንቶች እንዲሁም መጠጥና ልብስ የሚሸጡ መገበያያዎች ተሰርቀዋል።

ከፖሊስ ጋር የተሠማሩ ወታደሮች ይህን ጉዳት ካደረሱ መካከል ጥቂቱን መያዛቸው ተዘግቧል። እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች ቁጥር 800 ደርሷል።