የደርባኗ እናት ህጻን ልጇን ለማታውቃቸው ሰዎች ለምን ከፎቅ ወረወረች?

በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ በጭስ ከተሞላ ፎቅ የሁለት አመት ህፃን ልጇን ለተሰበሰቡ ሰዎች የወረወረችው እናት ልጇን ላዳኗት ሰዎች ምስጋናዋ ከፍ ያለ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጻለች፡፡
ናሌዲ ማኒዮ "ማድረግ የቻልኩት የማላውቃቸውን ሰዎች ማመን ነበር፡፡
እናት እና ልጅ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉም አክላ ተናግራለች፡፡
የነበሩበት ህንጻ በዘራፊዎች ነበር በእሳት የተያያዘው፡፡
አለመረጋጋቱ የተፈጠረው የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰራቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የ 79 ዓመቱ ቀድሞ ፕሬዝዳንት በቀረበባቸው የሙስና ክስ ምርመራ ላይ ባለመገኘታቸው ባለፈው ወር ተፈርዶባቸዋል፡፡
የ 15 ወር የእስር ቅጣታቸውን ለመጀመር ባለፈው ረቡዕ እጃቸውን ለፖሊስ አሳልፈው ሰጥተዋል።
ይህን ተከትሎም በትውልድ ስፍራቸው በክዋዙሉ-ናታል የተጀመሩት ተቃውሞዎች፣ የእሳት ቃጠሎ ጥቃቶችን እና አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ የመዝረፍ ተግባር ወደ ሌሎች ከተሞች ተዛምቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ሲርል ራማፎሳ ከ 1990 ዎቹ ወዲህ ያተስተዋሉት እጅግ የከፋ ሁከት እና ብጥብጥ ብለው በገለጹት አመጽ ቢያንስ 72 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ህጻን ሜሎኩህልን እንዴት ታደጓት?
የቢቢሲው የካሜራ ባለሙያ ቱቱካ ዞንዲ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ደርባን ከተማ በዘራፊዎች ከታመሰች በኋላ በደርባን ከተማ መሃል በሚገኝ አንድ ጎዳና ላይ እያለ ማኑኒ ልጇ ሜሎኩህልን ስትወረውር በቪዲዮ ቀርጿት ነበር፡፡
ማኒዮ የትዳር አጋሯን እየጎበኘች በነበረችበት ሕንጻ ስር የሚገኙ ሱቆች ላይ የእሳት ቃጠሎ ጀምሯል፡፡
የእሳቱን ጭስ ሲመለከቱ በህንጻው ክፍል 16ኛ ወለል ላይ ነበሩ፡፡
በቃጠሎው የተነሳ የህንጻው አሳንሰር እየሰራ ስላልነበረ ማኒዮኒ በፍርሃት ከልጇ ጋር በደረጃው መውረድ ጀመረች፡፡
ሆኖም አካባቢው ተዘግቶ ስለነበር ወደ ታችኛው ወለል መድረስ አልቻለችም፡፡
በሁለተኛ ፎቅ ላይ ወደሚገኘው የተጨናነቀ በረንዳ በማቅናት መንገደኞችን ለእርዳታ እንደለመነች ትናገራለች፡፡
"ማሰብ የቻልኩት ልጄ እንድትኖር ማረጋገጥ ብቻ ነበር" ትላለች፡፡
መሬት ላይ ነበሩ ሰዎች መሰላል በመጠቀም ሰዎችን ከአደጋው ማዳን ከጀመሩ ከ 20 ደቂቃ በኋላ ነበር የእሳት አደጋ ሠራተኞች ወደ ስፍራው የደረሱት። ማኒዮኒም በተመሳሳይ መንገድ ነበር ከሴት ልጇ ጋር እንደገና የተገናኘችው፡፡
እኩለ ሌሊት አካባቢ ወደ ቤቱ መመለስ እንደቻሉ ለቢቢሲ አክላ ተናግራለች፡፡
የዙሉ ንጉስ ተማጽኖ
ለቀናት የቆየው ረብሻ በደርባን የዳቦና የነዳጅ እጥረት አስከትሏል። በሱቆች እና በነዳጅ ማደያዎች ረዥም ሰልፎች ተፈጥረዋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት የደቡብ አፍሪካ ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ ሥራውን ማቋረጡን ገልጿል። በሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ህዝባዊ አመጽ ከክዋሉ-ናታል የሚገቡና የሚወጡ ምርቶች በረብሻው ምክንያት መቋረጥን አስታውቋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ትልቁ የአርሶ አደሮች ድርጅት አግሪሳ ሥራ አስፈጻሚ እንዳሉት በሎጂስቲክስ "መስተጓጎል" ምክንያት አምራቾች ሰብላቸውን ወደ ገበያ ለማቅረብ እየታገሉ ነው፡፡
ክሪስቶ ቫን ደር ሬድ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "ህግና ስርአት በፍጥነት መስፈን አለበት። ምክንያቱም ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ ያጋጥመናል" ብለዋል፡፡
የዙሉው ንጉስ ሚሱዙሉ ካዝዌሊቲኒ በሁከቱ ዙሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት አስተያየት ዝርፊያውን አውግዘው ስለህብረተሰቡ መጥፎ ስዕል ከመቅረጹም በላይ ጥፋቱ ድሆችን ብቻ የሚጎዳ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"የአባቴ ሰዎች የራሳቸውን ሀገር በማቃጠል ይሳተፋሉ ብዬ በጭራሽ አላሰብኩም ነበር" ብለዋል፡፡
ንጉስ ሚሱዙሉ "ይህ ሁሉ በወረርሽኝ ጊዜ እና በጣም አደገኛ በሆነ የቫይረሱ ዝርያ ስርጭት ወቅት መሆኑ ሲታይ አባቴ ሰዎች ራሳቸውን እየገደሉ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሳል" ሲሉ ገልጸዋል።












