ኩባ ነውጡን ተከትሎ ከውጪ የሚገቡ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የጣለችውን ቀረጥ አነሳች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኩባ በአስር አመታት ውስጥ አይታው የማታውቀውን የአደባባይ የተቃውሞ ነውጥ መከሰቱን ተከትሎ ከውጭ በሚገቡ ምግብ፣ መድኃኒትና ሌሎች መሰረታዊ በሚባሉ ሸቀጦች ላይ የጣለችውን ቀረጥ አንስታለች።
ከሚቀጥለው ሰኞ ጀምሮ ከውጭ አገር የሚመጡ መንገደኞች የሚያመጧቸው መሰረታዊ ሸቀጦች አይቀረጡም የተባለ ሲሆን ይህም በጊዜያዊነት ይተገበራል ተብሏል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿ እሁድ እለት በደሴቲቱ የኮሚዩኒስት መንግሥት ላይ የተቃጣ የተቃውሞ ሰልፎችን አካሂደዋል።
ኩባውያን በኢኮኖሚው ውድቀት፣ በምግብ እና መድኃኒት እጥረት፣ በሸቀጦች ዋጋ መናር እና በመንግሥት የኮቪድ-19 እንዝህላል አያያዝ ተቆጥተዋል።
ተቃዋሚዎቹ ካነሷቸው ጥያቄዎችም መካከል ከውጭ አገር የሚመጡ መንገደኞች የሚያስገቧቸው ሸቀጦች ላይ የተጣለው ቀረጥ እንዲነሳ ነው።
በባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተነሱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ በመላው አገሪቱ የተካሄዱ ሲሆን በርካቶችም ለእስር ተዳርገዋል።
ባለስልጣናቱ እንዳረጋገጡትም አንድ ግለሰብ ሞቷል።
በአገሪቱ ውስጥ ፍቃድ የሌላቸው ሰልፎች ህገወጥ የሚባሉ ሲሆን ፀረ-መንግሥት ተቃውሞዎች የተለመዱ አይደሉም።
አስፈላጊ ውሳኔ
ጠቅላይ ሚኒስትር ማኑኤል ማሬሮ ክሩዝ ረቡዕ ዕለት በመንግስታዊው ቴሌቪዥን በተላለፈው ስብሰባ ላይ ስለ ቀረጡ ለውጥ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በበርካታ መንገደኞች የቀረበ ጥያቄ ነበር እናም እዚህ ውሳኔ ላይ መውሰድ አስፈላጊ ነበር" ብለዋል።
መንግሥታቸው ከታህሳስ በኋላ ሁኔታውን ይገመግመዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ኩባ የሚጓዙ መንገደኞች እስከ 10 ኪሎ ግራም መድኃኒት ወደ ሀገር ውስጥ ከቀረጥ ነፃ ሊያመጡ ይችላሉ።
ሆኖም ለማምጣት በሚፈቀድላቸው ውስን የምግብ እና የግል ንፅህና አቅርቦቶች ላይ የጉምሩክ ቀረጥ መክፈል አለባቸው።
እንዲህ ዓይነቱ የጉምሩክ የቀረጥ ለውጥ ምን አይነት ተፅእኖ እንደሚኖረው ግልጽ አይደለም። በአሁኑ ወቅት በተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ወደ ኩባ የሚጓዙ ጥቂት ሰዎች ናቸው።
"አይ እኛ ፍርፋሪ አንፈልግም። ነፃነት እንፈልጋለን። ጥቂት ተጨማሪ ሻንጣዎችን ለማስገባት በኩባ ጎዳናዎች ላይ ደም አልፈሰሰም" በማለት የመንግስት ተቺው እና ጋዜጠኛው ዮአኒ ሳንቼዝ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።












