የታሊባን ሰንደቅ አላማ በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን ድንበር እየተውለበለበ ነው

የፎቶው ባለመብት, Twitter
ታሊባን በአፍጋኒስታንና በፓኪስታን መካከል የምትገገኘውን ቁልፍ የተባለች የድንበር ኬላ ላይ ሰንደቅ አላማውን የሰቀለ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በቁጥጥሩ ስር እንደምትገኝ አስታውቋል።
በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ እየተሰራጩ ያሉ ቪዲዮዎች ካንዳሃር አቅራቢያ ከሚገኘው ስፒን ቦልድክ በተሰኘችው ከተማ የድንበር መሻገሪያ ላይ ነጭ ባንዲራ ሲውለበለብ ታይቷል።
የአፍጋኒስታን ባለስልጣናት የድንበር መሸጋገሪያዋ በታሊባን ቁጥጥር ስር መሆኗን ቢያስተባብሉም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ቪዲዮች የታሊባን ታጣቂዎች ከፓኪስታን የድንበር ጠባቂዎች ጋር ሲነጋገሩ የሚያሳዩ ናቸው።
ቢቢሲ ከምንጮቹ እንደሰማው ታሊባን ያለ ምንም ተቃውሞ የድንበር መሸጋገሪያዋን ያለ ምንም ውጊያ እንደተቆጣጠሩት ነው።
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የታሊባን ታጣቂዎች አገሪቷ ከኢራን፣ ታጂኪስታን እና ቱርክሜኒስታን የሚያዋስኗትን የድንበር ኬላዎችን ከአፍጋኒስታን ኃይል በመውሰድ ተቆጣጥረዋል ተብሏል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ሰራዊታቸውን እስከ መስከረም 1 2014 ድረስ ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት ቀነ ገደብ አስቀምጠው የነበረ ቢሆንም ቀድማ ወታደሮቿን አስወጥታለች።
አሜሪካ አፍጋኒስታንን ከ20 አመታት በፊት መውረሯን ተከትሎ ተገፍቶ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ዋነኛ የሚባሉ የአገሪቷን መንገዶች ተቆጣጥረዋል።
በአገሪቱ ባሉ ከተሞች የሚደርሱ አቅርቦቶችንም እንዳይደርሱ ለማድረግ ነውም ተብሏል።
በአሁኑ ሰዓት ታሊባን የተቆጣጠራት የድንበር ኬላ በአፍጋኒስታን በኩል በካንዳሃር ግዛት የምትገኘውን ስፒን ቦልዳክ ከተማን በፓኪስታን በኩል ደግሞ ቻማን የምታገናኝና በአገራቱ መካከልም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያለባት መሸጋገሪያ ናትተብሏል።
የካንዳሃር ግዛትን ከፓኪስታን ወደቦች ጋር የምታገናኝ ሲሆን በየቀኑ ወደ 900 የሚጠጉ የጭነት መኪናዎችም ይተላለፉባታል።
የቢቢሲው ዘጋቢዋ ሊሴ ዱኬት እንደምትለው ታሊባን የድንበር መሻገሪያውን መቆጣጠሩ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠውና ስትራቴጂካዊ ጠቃሚነቱም ከፍተኛ ነው ተብሏል።
ከገቢና ከወጪ ንግድም ከሚገኘው ጉምሩክም ገቢ መሰብሰብ ከመቻላቸው በተጨማሪ እንዲሁም የታሊባን መሪዎች እና ተዋጊዎች ለበርካታ አመታት መቀመጫቸው የሆነውን የፓኪስታን ግዛቶችም ቀጥታ መዳረሻዎችን አንደሚፈጥርላቸውም ተገልጿል።
ቢቢሲ ዘገባዎቹን በተናጥል ማረጋገጥ ባይችልም ግን የፓኪስታን ባለሥልጣናት ታሊባን የድንበር መሸጋገሪያዋን መያዛቸውን አረጋግጠዋል።












