በአሜሪካ ከመጠን ያለፈ መድሀኒት በመውሰድ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ከመጠን ያለፈ መድሀኒት በመውሰድ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መጨመሩ ተነገረ
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክስተት መካከል በአሜሪካ ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከመጠን ያለፈ መድሀኒትን በመውሰድ ለህልፈት መዳረጋቸውን አንድ ይፋዊ መረጃ አመላክቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 በጠቅላላው 93 ሺህ 331 የሚገመቱ አሜሪካውያን ከመጠን ባለፈ የመድሃኒት አጠቃቀም ምክንያት ሞተዋል ይህ ቁጥር ከቀዳሚው ዓመት [ከ2019] ጋር ሲነፃፀር ወደ 30 በመቶ ገደማ ጭማሪ አሳይቷል።
ታዲያ እንደ ባለሙያዎች ገለጻ የሁኔታው እየከበደ መምጣት አንዳንድ መድኃኒቶች ምን ያህል ገዳይ እንደሆኑና ወረርሽኙ በኅብረተሰቡ ላይ እያደረሰ ያለው አስከፊ ጫና ያሳያል።
በሀገሪቱ ከመጠን ያለፈ መድሃኒት በዚህ ደረጃ ሲጨምር 'ፌንቲናል' የተሰኘው መድሃኒት ግማሽ ያህሉን ድርሻ ይወስዳል። ጠንካራና ሰው ሰራሽ ኦፒዮይድ የተሰኘውን ንጥረ ነገር የሚይዘው 'ፌንቲናል' ከ'ሄሮይን' በ 50 እጥፍ ይልቃል ተብሏል ፡፡
ታዲያ ሌሎች መድሃኒቶች 'ጠንከር ያለ' ይዘት እንዲኖራቸው ሻጮች በ'ፌንቲናል' 'እየበከሏቸው' እንደሆነ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መገለል እና የብቸኝነት ስሜት ከመጠን ባለፈ የመድሃኒት አወሳሰድ ምክንያት ለጨመረው የሞት ቁጥር ሌላው በምክንያትነት የተቀመጠ ጉዳይ ሆኗል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ያልተጋባ መድሃኒት አጠቃቀም ቁጥጥር ዳይሬክተር ኖራ ቮልኮው በሰጡት መግለጫ "ይህ በ 12 ወራት ጊዜ ውስጥ ከተመዘገቡት እጅግ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ነው ፣ እና ቢያንስ ከ 1999 ወዲህ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል" ብለዋል።
ከቀናት በፊት በወጣው መረጃ አኃዞች ሲተነተኑ በየቀኑ 250 ገደማ የሚሆኑ ወይም በሰዓት ወደ 11 ያህል ሰዎች ሰዎች ከመጠን ባለፈ መድሃኒት ምክንያት ለህልፈት ይዳረጋሉ እንደ ማለት ነው።












