አሜሪካ እንግሊዝኛ በማስተርጎም ያገዟትን አፍጋኒስታዊያንን ወደ አገሯ ልታስወጣ ነው

አፍጋኒስታናዊ አስተርጓሚ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ላለፉት 20 ዓመታት በነበራት የአፍጋኒስታን ቆይታ ቋንቋ በማስተርጎም ተግባር ላይ ያገዟትን የአገሬውን ዜጎች ወደ አገሬ እወስዳቸዋለሁ አለች፡፡

ይህን የወሰነችው ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ በማሰብ ነው ተብሏል፡፡

የአሜሪካ ሰራዊት ለሁለት ዐሥርታት በአፍጋኒስታን ከቆየ በኋላ በጆ ባይደን ትዕዛዝ ከመስከረም 11 በፊት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ እንዲወጣ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎ የአሜሪካ ወታደሮች ተጠቃለው በመውጣታቸው ባለፉት ሳምንታት አፍጋኒስታን በርካታ አካባቢዎችን መቆጣጠሩ ሲዘገብ ነበር፡፡

‹እንግሊዝኛ አስተርጓሚ የነበሩ አፍጋኒስታዊያን ጀግኖች ናቸው፡፡ ለዚህ ጀብዱ ተግባራቸው እውቅናና ዋጋ መስጠት እንፈልጋለን፡፡›› ብለዋል የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ፡፡

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ የማይሹ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ እንደተናገሩት 2ሺ 500 የመሆኑና በአስተርጓሚነት ያገለገሉ አፍጋኒስታዊያን ለጊዜው በአሜሪካ ወታደራዊ ካምፖች ወይም በሌላ ሦስተኛ አገር እንዲቆዩ ተደርጎ የቪዛ ሒደቱ እየተሳለጠላቸው ነው፡፡

የሚያገኙት የቪዛ አይነትም ‹ልዩ የኢሚግራንት ቪዛ› ይሆናል ተብሏል፡፡

የአሜሪካን ሰራዊት ከታሊባን መውጣት ተከትሎ በነዚህ አስተርጓሚዎች ላይ ታሊባን የበቀል እርምጃ እንዳይወስድ ተፈርቷል፡፡

በተለይም ታሊባን ከኢራን፣ ታጃኪስታንና ቱርኬሜኒስታን የሚያዋስኑ የድንበር ከተሞችን መቆጣጠሩን ተከትሎ የአሜሪካ አስተርጓሚ የነበሩ ዜጎች ላይ ጥቃት ሊሰነዝ ይችላሉ የሚለው ስጋት አይሏል፡፡

ታላቢና ባለፈው ረቡዕ ካንዳሃር አካባቢ ሙሉ ቁጥጥር አድርገው ባንዲራቸውን መስቀላቸው ይታወሳል፡፡

የታሊባንን ወደፊት መገስገስ ተከትሎ በርካቶች የአፍጋኒስታን የጸጥታ መዋቅር ሙሉ በሙሉ እንዳይሽመደመድና የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ጆርጅ ቡሽ ከ20 ዓመት በፊት የአሜሪካ ወታደሮችን ወደ አፍጋኒስታን ከመላካቸው በፊት ወደነበረችው ዜጎቿን ጨቋኝ አፍጋኒስታን እንዳይመለሱ ፍርሃት ነግሷል፡፡

ከጀርመን ሚዲያ ዶቸ ቬሌ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ቡሽ የጆባይደንን ከአፍጋኒስታን ሙሉ በሙሉ ለቆ መውጣት ተችተዋል፡፡ ይህ ውሳኔ የአፍጋኒስታንን ሕዝብ ‹በደም እንዲቃባ› የመፍቀድ ያህል ነው ብለዋል፡፡

በ90ዎቹ አካባቢ ታሊባን አፍጋኒስታን ላይ ሙሉ ቁጥጥር ይዞ በነበረ ጊዜ በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ይፈጽም እንደነበር ይዘገባል

ይህ የቆመው በአሜሪካ ወረራ ጣልቃ ገብነት ምክንያት እንደሆነ አሜሪካ ትገልጻለች፡፡

ታሊባን አፍጋኒስታንን በሚያስተዳድርበት በዚያ ዘመን ጥፋተኞችን በስቅላት መቅጣት፣ ቴሌቪዥን፣ ሲኒማና ሙዚቃ መከልከል እና ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ማገድ የተለመደ ነበር፡፡