በደቡብ አፍሪካው ነውጥ ከፎቅ የተወረወረው ሕፃን

በሕንፃው የመጀመሪያው ፎቅ ላይ የሚገኙ መደብሮች ተዘርፈው፣ ሕንፃው ከተቃጠለ በኋላ ነበር ሕፃኑ ከፎቅ ላይ የተወረወረው።
የምስሉ መግለጫ, በሕንፃው የመጀመሪያው ፎቅ ላይ የሚገኙ መደብሮች ተዘርፈው፣ ሕንፃው ከተቃጠለ በኋላ ነበር ሕፃኑ ከፎቅ ላይ የተወረወረው።

በደቡብ አፍሪካ የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 72 ደርሷል።

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ መታሰራቸውን በመቃወም የተነሳው ነውጥ በመላው ደቡብ አፍሪካ ለቀናት እንደቀጠለ ነው።

በተለያዩ ከተሞች መደብሮች ያቃጠሉ፣ የዘረፉ ሰዎች ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

ደርባን ውስጥ አንድ ሕፃን ከሕንፃ ሲወረወር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ቢቢሲ ቀርጿል። በሕንፃው የመጀመሪያው ፎቅ ላይ የሚገኙ መደብሮች ተዘርፈው፣ ሕንፃው ከተቃጠለ በኋላ ነበር ሕፃኑ ከፎቅ ላይ የተወረወረው።

ይህ ከመከሰቱ ከአንድ ቀን በፊት ሶዌቶ ውስጥ የሚገኝ የግብይት ማዕከል ሲዘረፍ 10 ሰዎች ተረጋግጠው ሞተዋል።

ባለፈው ሳምንት የተነሳውን ነውጥ እንዲያረግብ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ተሠማርቷል።

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ 12 ብጥብጡን ቀስቅሰዋል ያላቸውን ዜጎች እንደለየና ባጠቃላይ 1,234 ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ አስታውቋል።

ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ ከ1990ዎቹ ወዲህ በደቡብ አፍሪካ የተነሳ ከፍተኛ ነውጥ ነው ብለዋል።

እንደ ኩዋዙሉ-ናታል እና ጋውተንግ ያሉ ከተሞችን ጨምሮ በበርካታ የደቡብ አፍሪካ ግዛቶች እሳት ተነስቷል፣ አውራ ጎዳናዎች ተዘግተዋል፣ የንግድ ተቋማት ተዘርፈዋል።

የአገሪቱ ሚንስትሮች ዝርፊያ ከቀጠለ በአንዳንድ አካባቢዎች መሠረታዊ የምግብ አቅርቦት ሊቋረጥ እንደሚችል ቢያስጠነቅቁም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አልታወጀም።

ከፎቅ የተወረወረው ሕፃን

ከሕንፃ ላይ የተወረወረው ሕፃን መሬት ላይ ከመውደቁ በፊት ሰዎች ተሰብስበው በመቅለብ ሕይወቱን አድነውታል። የሕፃኑ እናት ልጇን ከእሳት ለመታደግ ልጇን ከፎቅ ለመወርወር ተገዳለች።

እናቲቱ በስሜት ተውጣ ስለነበር መናገር እንኳን አልቻለችም።

በሕንፃው ውስጥ የነበሩ ሰዎችንም ከእሳቱ ታድገዋቸዋል።

ደርባን በሚገኘው ስሚዝ ጎዳና ላይ ካለው ሕንፃ ውስጥ መደብሮች ሲዘረፉ የነበሩ ሰዎች ናቸው እሳቱን ያስነሱት።

እሳቱ ከመጀመሪያው ፎቅ ተነስቶ ሰዎች ወደሚኖረበት የሕንፃው የላይኛው ክፍል ተሰራጭቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከፎቅ ላይ የተወረወረውን ሕፃን ሕይወት ከታደጉ በኋላ ሌሎች የሕንፃው ነዋሪዎችን ለማዳን መሰላል ዘርግተዋል።

ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸውም በመሰላሉ ወደ መሬት ወርደው ከሞት ተርፈዋል።

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ወደ አካባቢው የደረሱት ከ20 ደቂቃ በኋላ ነው።

በሁከቱ ሳቢያ ምን ያህል ጉዳት ደረሰ?

ሰኞ ከሰዓት ወደ 200 የሚደርሱ መገበያያ ሕንፃዎች መዘረፋቸውን የደቡብ አፍሪካ የንግድ ማኅበረሰብ መሪ ቡሲሲዌ ማቩሶ መናገራቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።

በሶዌቶ የሚገኙ መደብሮችም ጉዳት ደርሶባቸዋል። ኤቲኤም ማሽኖች ተሰብረዋል። ሬስቶራንቶች እንዲሁም መጠጥና ልብስ የሚሸጡ መገበያያዎች ተሰርቀዋል።

ከፖሊስ ጋር የተሠማሩ ወታደሮች ይህን ጉዳት ካደረሱ መካከል ጥቂቱን መያዛቸው ተዘግቧል። እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች ቁጥር 800 ደርሷል።

ሆኖም ግን ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርሱት አዋኪዎች ቁጥር ከፖሊሶች እንደሚበልጥ ተነግሯል።

የደቡብ አፍሪካው ታይምስላይቭ እንደዘገበው፤ በኩዋዙሉ-ናታል የቀንድ ከብት ተዘርፏል። አምቡላንሶች ላይም ጥቃት ተሰንዝሯል።

ፕሬዘዳንት ራማፎሳ ሰኞ እለት ንግግር ሲያደርጉ ደርባን ውስጥ የደም ባንክ ሲዘረፍ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ወጥቷል።

ደቡብ አፍሪካና የምጣኔ ሀብት ቀውስ

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ጄኮብ ዙማ ከእስር እንዲፈቱ የሚጠይቁ ደጋፊዎቻቸው ናቸው ሁከቱን ያስነሱት።

በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞው ፕሬዘዳንት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ፍርድ ቤት በመዳፈር እንዲታሰሩ ሲወሰን ተቃውሞው ተቀጣጥሏል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሥራ አጥነት መጠን 32.6% ደርሷል። በወጣቶች ዘንድ ደግሞ ቁጥሩ ወደ 46.3% ከፍ ይላል።

ሁከቱ በከፍተኛ ሁኔታ ከተቀጣጠለባቸው ምክንያቶች አንዱ ሥራ አጥነት መሆኑም ይታመናል።

ፕሬዘዳንት ራማፎሳ ነውጡን ማብረድ አልቻሉም በሚል ተተችተዋል።

ተቃውሞውን ለማቆም የተሠማራው መከላከያ 2,500 ብቻ ነው። አምና የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተጣለው የሰዓት እላፊ ለማስከበር የተሠማራው ግን 70,000 ሠራዊት ነበር።

ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ የተባለው ተቃዋሚ ፓርቲ፤ መከላከያ ከማሠማራት ይለቅ ለችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት ያዋጣል ብሏል።

ደቡብ አፍሪካ ወረርሽኙ ካሳደረባት ተጽዕኖ ባሻገር የምጣኔ ሀብት ቀውስ ገጥሟታል። ዙማን ተከትሎ የመጣው የራማፎሳ አስተዳደር በዚህ ቀውስ እየተተቸ ይገኛል።