"በደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ፈርተው ዛሬ መደብር አልከፈቱም"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የጃኮብ ዙማን እስር ተከትሎ በአገሪቱ ሰላማዊ ሰልፎችና ነውጥ መቀስቀሱን ተከትሎ በጆሀንስበርግ የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬ መደብራቸውን ዘግተው እንደዋሉ በከተማዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊን ለቢቢሲ ተናገሩ።
በንግድ ሥራ የተሰማራው ዳዊት ተወልደመድኅን፤ በጆሀንስበርግ በተለይም ጂፒ ጎዳና እና ብሪ ጎዳና በሚባሉት አካባቢዎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ፈርተው ዛሬ ሐምሌ 5/2013 ዓ.ም. መደብራቸውን ዘግተው ለመዋል መገደዳቸውን ተናግሯል።
ትላንት ሐምሌ 4/2013 ዓ.ም. በዚያው አካባቢ በተነሳው ነውጥ የኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ስደተኞች መደብሮች ላይ ጥቃት ሲሰነዘር ፖሊስ እንደተከላከለ ዳዊት ይናገራል።
በደቡብ አፍሪካ የተባበሩት ኢትዮጵያ ማኅበሰረብ ማኅበር ዋና አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆነው ንጉሥ ተመስገን እንደሚናገረው ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያን፣ ፓኪስታናውያን እንዲሁም ሌሎችም የሚነግዱበት አካባቢ ዛሬ ተዘግቶ ውሏል።
"ኒውካስል አካባቢ ሁለት ኢትዮጵያውያን ጥቃት ደርሶባቸዋል። ከባድ ግን አይደለም። ዛሬ ሶዌቶ አካባቢ አመጽ ስላለ በንግድ የተሰማራው የሀበሻው ማኅበረሰብ ሱቁን ዘግቷል። ደርባን ትላንት ሌሊት ሲዘረፍ፣ መኪና ሲቀጠል ነበር" ይላል።
ከኢትዮጵያውን ማኅበረሰብ እና ከፖሊስ በተገኘው መረጃ መሠረት ከባድ የሚባል ጉዳት እስካሁን እንዳልደረሰ ያክላል።
"ትላንት የስደተኞች መደብሮች ላይ ጥቃት እየተሰነዘረ እንደሆነ ኢትዮጵያውን ሲሰሙ ተሰብስበው ወደ ጂፒ ስትሪት ሄደው ሱቆቻቸውን ተከላከሉ። ፖሊሶችም ሀበሾችን ሲረዱ ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ተሰብስበው ባይሄዱ ኖሮ የከፋ ነገር ይፈጠር ነበር" ይላል ነጋዴው ዳዊት።
በተለይም ጆሀንስበርግ ውስጥ ረብሻ ሲነሳ ጥቃት የሚሰነዘረው ስደተኞች እንዲሁም የንግድ ተቋሞቻቸው ላይ እንደሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል።
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ በሥልጣን ዘመናቸው ተፈጽመዋል የተባሉ የሙስና ጉዳዮች እየተመለከተ በሚገኘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠይቀው ሳይገኙ በመቅረታቸው ፍርድ ቤትን በመድፈር ጥፋተኛ ተብለው የ15 ወራት እስር ተፈርዶባቸዋል።
የጃኮብ ዙማን እስር ተከትሎ የእሳቸው ደጋፊ የሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣት የጀመሩት ጃኮብ ዙማ እጃቸውን ለፖሊስ ከሰጡ በኋላ ነው።
ከዚህ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ በተነሳው ነውጥ ሕንጻዎች እና ተሽከርካሪዎች ወድመዋል። መደብሮችም ተቃጥለዋል።
ግርግር፣ ዝርፊያና ንብረት ማቃጠል
ጆሃንስበርግ ውስጥ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ወ/ሮ መዓዛ ተስፋዬ እንደተናገሩት ረብሻው መቀስቀሱን ተከትሎ በጣም አሳሳቢ እና አስፈሪ ሁኔታ ተከስቷል።
ግርግር፣ ዝርፊያና ንብረት የማቃጠል ድርጊት በየቦታው እንደነበርና መንገዶችም በተቃዋሚዎቹ በሚቃጠሉ ጎማዎች ተዘግተው እንደነበር ገልጸዋል።
ተቃውሞው በጃኮብ ዙማ መታሰር የተቀሰቀሰ ይሁን እንጂ ቢቢሲ ያናጋራቸው ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት፤ ከተቃውሞው ባሻገር በተለያዩ ስፍራዎች ዝርፊያዎችና የንብረት ውድመት ተፈጽሟል።
በተለይ የንግድ ሱቆች የተቃዋሚዎቹ የጥቃት ኢላማ በመሆናቸው በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት ሱቆቻቸውን ዘግተው ቤታቸው ተቀምጠዋል።
ረብሻው እሳቸው በሚኖሩበት ጆሃንስበርግና ደርባን ከተሞች ውስጥ የበረታ መሆኑን የሚናገሩት ወ/ሮ መዓዛ፤ ፖሊስ አመጸኞቹን ለመቆጣጠርና የንብረት ውድመት ለማስቆም እየጣረ ነው ብለዋል።
ለሁለት ቀናት ከዘለቀ ተቃውሞና የንብርት ውድመት በኋላ ከትናንት ዕሁድ በተሻለ ሰኞ ዕለት መረጋጋት በጆሃንስበርግ መመለሱን የተናገሩት ወ/ሮ መዓዛ "ከተማው ጸጥ ብሏል" ብለዋል።
የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በረብሻው የወደሙ ንብረቶችናና የደረሰ ጉዳትን በተመለከተ ተከታታይ ዘገባዎችን እያቀረቡ ሲሆን ወ/ሮ መዓዛና ሌሎች ኢትዮጵያውያን ለሁለት ቀናት ከሥራ ውጪ ሆነው መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ሌሎች ኢትዮጵያውያንና የመገኛኛ ብዙኃን እንደሚሉት ረብሻው ከተከሰተ በኋላ ከጆሃንስበርግ ይልቅ በደርባን ከባድ ጉዳት መድረሱን እንደተረዱ ጠቅሰዋል።
"ረብሻ ሲነሳ ጥቃት የሚደርሰው ስደተኞች ላይ ነው"
ንጉሥ እንደሚለው፤ ማንኛውም አይነት ነውጥ ሲነሳ ያንን ሰበብ በማድረግ የንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ጥቃት ይሰነዘራል።
አሁን የተነሳው አይነት አለመረጋጋት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ባለፉት ጥቂት ቀናት ሲነገር እንደነበር እና ሸቀጣቸውን ከመደብር ያወጡ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች እንዳሉ ገልጿል።
"ዛሬ ጥቃት እንደሚደርስ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ስለተነገረ መላው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ከቤቱ አልወጣም" ብሏል።
ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የወጣው የእንቅስቃሴ ገደብ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ላይ ያሳደረው ጫና ላይ አሁን የተነሳው ነውጥ ሲጨመር ማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ቀውስ እንደሚያስከትልም ንጉሥ ይናገራል።
ዳዊት እንደሚለው፤ ከዚህ ቀደምም እንደታየው አንዳች ነውጥ ሲነሳ ስደተኞች ላይ ጥቃት ይሰነዘራል።
ይህንን የሚያውቁት ኢትዮጵያውያን ስጋት ስለገባቸው ዛሬ መደብራቸውን አልከፈቱም።
"ትላንት ኢትዮጵያውኑ ተሰብስበው ሳይሄዱ በፊት ጉዳት የደረሰባቸው ሱቆች ነበሩ። ዛሬም ምን ሊፈጠር እንደሚችል ስለማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ሱቃቸውን ዘግተው ውለዋል" ይላል።
ትላንት የናይጄርያውያን መኪና መሸጫ፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብርና ሌሎችም የንግድ ተቋማት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ይናገራል።
"ትላንት ሀበሾች በቁጣ ሱቃቸውን ለመጠበቅ ወጡ። ፖሊስም አገዛቸው። ከዚህ በፊት ፖሊሶችም ጭምር ችግር ይፈጥሩብን ነበር" ይላል።
ኢትዮጵያውያኑ ስጋት ውስጥ እንደሆኑና የጃኮብ ዙማ የፍርድ ቤት ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ወይም እስኪረግብ ድረስ ወደ ሥራ መመለስ እንደሚያስቸግር ዳዊት ለቢቢሲ ገልጿል።
ሁሌም ረብሻ ሲነሳ ስደተኞች ጥቃት እንደሚደርስባቸው የሚጠቅሰው ነጋዴው፤ "ድንገት መጥተው ሊዘርፉን ወይም ሊያጠቁን ስለሚችሉ ዘግቶ መጠበቅ ይሻላል" ሲል ያስረዳል።
ጆሃንስበርግ ውስጥ የሚነግዱ ኢትዮጵያውያን በማንኛውም ጊዜ ነውጥ ሊነሳ እንደሚችል እንደሚሰጉ ገልጾ "የለመድነው ችግር ስለሆነ ሁሌም በተጠንቀቅ ነው የምንጠብቀው። ረብሻ ሲነሳ ጥቃት የሚደርሰው ስደተኞች ላይ ነው" ብሎም አክሏል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም ስደተኞች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ብዙ ጊዜ ተፈጽመዋል።
ዳዊት "ስደተኞች ሲጠቁ ዓለም የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን ስለሚጠይቅ ስደተኞችን ለማጥቃት ምክንያት ይፈለጋል" ሲል ሁኔታውን ያስረዳል።
በደቡብ አፍሪካ መከላከያ ሠራዊቱ ስለመሰማራቱ
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት፤ በጃኮብ ዙማ የትውልድ ቦታ ክዋዙሉ-ናታለ ተቀስቅሶ በመላው አገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣውን አለመረጋገት ለማርገብ የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት እንዳሰማራ ተገልጿል።
ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች ፖሊስ ምላሽ እየሰጠ ሲሆን እስካሁን ድረስ 60 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም ይፋ አድርጓል።
ትናንት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች ዱላ እና ፍልጥ ይዘው በጆሃንስበርግ ከተማ መሃል ታይተዋል።
ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች የጆሃንስበርግን ዋና ጎዳናን ዘግተው ነበር። ከትናንት በስቲያ በነበረው ተቃውሞ ሕንጻዎች እና መኪኖች በእሳት ወድመዋል።
አሌክሳንድራ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ወደ 800 የሚጠጉ ሰዎች ተሳትፈውበታል በተባለው አመጽ አንድ የፖሊስ አባል በጥይት መመታቱ ተዘግቧል።
ፕሬዝደንት ሲርል ራማፎሳ ትናንት ምሽት ግጭት እያስከተሉ ያሉ ተቃውሞዎች እንዲቆሙ የጠየቁ ሲሆን፤ "ለዚህ አመጽ እና የንብረት ውድመት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊቀርብ አይችልም" ብለዋል።
ፍርድ ቤትን በመድፈር ጥፋተኛ ተብለው የ15 ወራት እስር የተፈረደባቸው ጃኮብ ዙማ በሥልጣን ዘመናቸው ምንም ዓይነት ሙስና አለመፈጸማቸውን ይከራከራሉ።
የጃኮብ ዙማ ጠበቆች ዛሬ ለአገሪቱ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት የፍርድ ጊዜውን ለማሳጠር ይሞክራሉ ተብሏል።












