በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች አያያዝ ህግን መከተል አለበት-ኢሰመኮ

የኢሰመኮ አርማ

የፎቶው ባለመብት, EHRC

በእስር ላይ የሚገኙት የኢትዮ-ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች አያያዝ በህግ አግባብ ሊሆን እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትናንትናው ዕለት ሐምሌ 3፣ 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የፍርድ ቤትም የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በአፋጣኝ ሊለቀቁ እንደሚገባም ኢሰመኮ አፅንኦት ሰጥቷል።

በእስር የሚገኙት በቃሉ አላምረው፣ ያየሰው ሽመልስ፣ ፋኑኤል ክንፉ፣ አበበ ባዩ፣ መልካም ፍሬ ይማም፣ ፍቅርተ የኑስ፣ ዊንታና በርሄ እና ምህረት ገብረክርስቶስን ጨምሮ 21 የኢትዮፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች ናቸው።

እነዚህ ጋዜጠኞችና ሰራተኞች ሰኔ 23፣ 24 እና 25 ቀን 2013 ዓ.ም.በፌደራል የፀጥታ ኃይሎች እንደተያዙ የጠቆመው መግለጫው የእስር አያያዛቸውን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር በቅርበት እየተከታተለ መሆኑንም ገልጿል።

ከእነዚህም መካከል ሶስቱ እስረኞች ማክሰኞ ሰኔ 29፣ 2013 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ተለቀዋል። ቀሪዎቹ ግን በወንጀል ስለተጠረጠሩ ለምርመራ በእስር እንዲቆዩ በፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ መሰጠቱን ፖሊስ ገልጾልኛል ብሏል ኢሰመኮ።

ነገር ግን ኮሚሽኑ መግለጫውን እስካወጣበት ቀን ድረስ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አለማየቱን፣ ታሳሪዎቹን አለመጎብኘቱን ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ታሳሪዎቹ ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከጠበቆቻቸው ጋር ሳይገናኙ ከአንድ ሳምንት በላይ መቆየታቸው እንዳሳሰበው አስፍሯል።

"ማማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑና በእስር ያሉ ተጠርጣሪዎች በጠበቆቻቸው እና በቤተሰቦቻቸው የመጎብኘት መብት ፈጽሞ ሊከለከሉ የማይገቡና፤ ተጠርጣሪዎች በሕይወት መኖራቸውንና አካላዊ ደኅንነታቸው መጠበቁን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው መሰረታዊ የሕግ ጥበቃዎች ናቸው።" በማለትም አስቀምጧል ።

የፌዴራል ፖሊስና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በእስር ላይ ያሉትን ጋዜጠኞችና ሰራተኞች በሙሉ በአፋጣኝ ከቤተሰቦቻቸውና ከጠበቆቻቸው እንዲገናኙ እንዲያደርጉም ጠይቋል።።

እንዲሁም የታሳሪዎቹን የእስር ሁኔታ ሕጋዊነት እንዲያስረዱና፣ ከፍርድ ቤት የተሰጠ የእስር ትዕዛዝ ካልቀረበ በስተቀር ታሳሪዎቹ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ኢሰመኮ አሳስቧል።

መግለጫው ዋና ኮሚሽነሩን ዳንኤል በቀለን ዋቢ አድርጎ እንዳሰፈረውም "ሕግን ያልተከተለ ማንኛውም አይነት እስር በሕግና ፍትሕ ሥርዓት ላይ የሚኖርን እምነትን ይሸረሽራል።ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር ሙሉ በሙሉ መቆም ያለበት ተግባር ነው።" በማለት አትቷል።