"እነ ጃዋር ይፈቱ" በሚል ተቃውሞው ታስሮ የነበረው መሃመድ ዴክሲሶ ተፈታ

መሃመድ ዴክሲሶ

የፎቶው ባለመብት, Sulxaan Deksiisoo

የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ "እነ አቶ ጃዋር መሃመድና የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ" በሚል ባስተላለፈው መልዕክት ለወራት ያህል ለእስር ተዳርጎ የቆየው መሃመድ ዴክሲሶ ቅዳሜ ሐምሌ 3/2013 ዓ.ም ከእስር ተለቋል።

መሃመድ "በአዋሽ መልካሳ የዶሮ እርባታ" ከአንድ ወር ተኩል በላይ በእስር መቆየቱንና እና ከአርብ ጀምሮ እሱን ጨምሮ በርካቶች ሲለቀቁ አሁንም ሌሎች በዶሮ እርባታው ቦታ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ "ፍትህ ለሃጫሉ ሁንዴሳ፣ የኦሮሞ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ ጃዋር መሃመድ ይፈታ" ሲል መልዕክት ማስተላለፉን ተከትሎ ነው ለእስር የተዳረገው።

ከቢቢሲ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረገው መሃመድ በታሰረባቸው ባለፉት አምስት ወራት፣ አምስት ወይም ስድስት የእስር ቦታዎች የቆየ መሆኑንም ገልጿል።

መሃመድ እንደሚለው ከነዚህ ቦታዎች ውስጥ "ሁለቱ ብቻ መደበኛ ማቆያ ነበሩ፣ ቀሪዎቹ ሕገወጥ የማሰቃያ ቦታዎች ናቸው" ሲል ተናግሯል።

መሃመድ ታስሮ የቆየባቸው ቦታዎችን በተመለከተ መንግሥትም ሆነ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች አስካሁን ያሉት ነገር የለም።

ቅዳሜ ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም ጥዋት አካባቢ መፈታቱንና እና ከቤተሰቦቹ ጋር ከቀኑ ሰባት ሰዓት መገናኘቱን መሃመድ አስረድቷል።

'ከዶሮ እርባታው' ቦታ ባለፉት ሦስት ቀናት በርካታ ሰዎች ቢፈቱም በቁጥር የማያስታውሳቸው ብዙዎች አሉ ብሏል።

"ቀናቶቹ ዓመታት ያህል ነበሩ፣ አልቆጠርኳቸውም፣ ግን ከአንድ ወር በላይ ይመስለኛል" ሲል አክሏል።

በእስር ወቅት ምን እንዳጋጠመው ከመግለፅ የተቆጠበ ቢሆንም "እኔን የገጠመኝ ከሌሎች ሰዎች በላይ አይደለም፤ ሌሎች በርካታ ሰዎች በእስር ቤት ይገኛሉ" ሲል መሃመድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

መሃመድ አክሎም በቆየበት 'የዶሮ ማርቢያ ቦታ' ስለነበረው አያያዝም "ያው የሚታወቅ ነው የዶሮ ማርቢያ ሲባል፣ የሚመች አያያዝ አልነበረም" በማለት አስረድቷል።

መሃመድ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፈው መልዕክት ቁጭት እንደሌለበት እና "ማንም ማወቅ ያለበት ነገር የመብት ጥያቄ ስለሆነ ያነሳሁት፤ የሚያሳስበኝ ወይም የሚያስፈራኝ ነገር የለም" ብሏል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዲሁም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት ታድመው ነበር።

መሃመድም ሙዚቃውን ሲጫወት ከነበረው ሙሉጌታ ሺቴ ላይ የድምፅ ማጉያ ተቀብሎ ነበር መልዕክቱን ያስተላለፈው።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የካቲት 18/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ከየካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ እንደሚገኝና የጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በዋስ እንዲለቀቅ ያሳለፈውን ውሳኔ በመተላለፍ ከእስር አለመለቀቁ እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር።

መሃመድ ዴክሲሶን ጨምሮ ሌሎችም በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸው በእስር ላይ የሚገኙ እስረኞች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ማሳሰቡም የሚታወስ ነው።

መሃመድ በእስር ላይ እያለ ኢሰመኮ በጎበኘበት ወቅት እንደተናገረው የምርቃት ፕሮግራሙ እንዳለቀ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ፖሊሶች በግቢው ውስጥ ወዳለው ካምፕ እንደወሰዱትና ፖሊሶቹ በጥፊ እንደመቱት፣ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ከዩኒቨርስቲው ግቢ ውጪ ወስደውት በዱላ ሁለቱን እግሮቹን እንደደበደቡት፣ በጎኑ አካባቢም እንደመቱት አስረድቷል።

መሃመድ አክሎም "በጅማ ዩኒቨርሲቲ የነበሩ ፖሊሶች ለአንድ ሰዓት ያክል ካቆዩኝና ከደበደቡኝ በኋላ ወደ ጅማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወሰዱኝ፣ በፖሊስ ጣቢያው ከደረስኩ በኋላ ግን የተፈጸመብኝ ድብደባ የለም" ብሏል።

ኢሰመኮ መሃመድን በጎበኘበት፣ የካቲት 10/2013 ዓ.ም ዕለትም መሃመድ በእግሮቹ ላይ መጠነኛ እብጠት የሚታይ መሆኑንና የሚያነክስ መሆኑን አስፍሯል።

እስረኛው ሕክምና እንዲያገኝ ለፖሊስ ጣቢያው ቢጠየቅም እስከ የካቲት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ሕክምና ያላገኘ መሆኑን እንዳላረጋገጠ ኢሰመኮ በወቅቱ ገልፆ ነበር።

የጅማ ወረዳ ፍርድ ቤት የካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም መሃመድ በሁለት ሺህ ብር ዋስ እንዲለቀቅ ቢወስንም ፖሊስ ይህንን ውሳኔ በመተላለፍ በእስር ላይ እንደሚገኝ ኢሰመኮ አረጋግጦ ነበር።

ለሳምንታት የት እንደታሰረ ሳይገለፅ ቆይቶም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት አዲስ ክስ ተመስርቶበትም ነበር።

"መሃመድ ዴክሲሶ በተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የፈጸመው ተግባር ከነገሩ ሁኔታ አንጻር ምናልባት ሊነቀፍ ወይም ሊያስወቅስ ከሚችል በስተቀር፣ ከመነሻውም ለወንጀል ክስና አስር ምክንያት ሊሆን አይገባም ነበር" ሲል የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ላይ መጥቀሱ ይታወሳል።