የጃኮብ ዙማን እስር ተከትሎ በመላው ደቡብ አፍሪካ ተቃውሞ ተስፋፋ

ተቃውሞ በደቡብ አፍሪካ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማን እስር ተከትሎ በመላው አገሪቷ የተቃውሞ ሰልፎች ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን ፖሊስም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች አስሯል።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ደጋፊ የሆኑ ደቡብ አፍሪካውያን የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት አደባባይ መውጣት የጀመሩት ጃኮብ ዙማ ከቀናት በፊት እጃቸውን ለፖሊስ ከሰጡ በኋላ ነው።

ፖሊስ እንደሚለው በጃኮብ ዙማ የትውልድ ቦታ ክዋዙሉ-ናታለ ተቀስቅሶ በመላው አገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣውን አለመረጋገት ወንጀለኛ ቡድኖች መጠቀሚያ እያደረጉት ነው።

ዘረፋ ተፈጽሞባቸዋል በተባሉ ስፍራዎች ፖሊስ ምላሽ እየሰጠ ሲሆን እስካሁን ድረስ 60 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንም ይፋ አድርጓል።

ትናንት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች ዱላ እና ፍልጥ ይዘው በጆሃንስበርግ ከተማ መሃል ታይተዋል።

ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች የጆሃንስበርግን ዋና ጎዳናን ዘግተው ነበር። ከትናንት በስቲያ በነበረው ተቃውሞ ሕንጻዎች እና መኪኖች በእሳት ወድመዋል።

አሌክሳንድራ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ወደ 800 የሚጠጉ ሰዎች ተሳትፈውበታል በተባለው አመጽ አንድ የፖሊስ አባል በጥይት መመታቱ ተዘግቧል።

የክዋዙሉ-ናታለ ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይ ናኢከረ ለሮይተርስ "ወንጀለኞች እና ጥቅም የሚፈልጉ ግለሰቦች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሃብት ማካበት ፈልገዋል" ብለዋል።

ፕሬዝደንት ሲርል ራማፎሳ ትናንት ምሽት ግጭት እያስከተሉ ያሉ ተቃውሞዎች እንዲቆሙ የጠየቁ ሲሆን፤ "ለዚህ አመጽ እና የንብረት ውድመት ምንም ዓይነት ምክንያት ሊቀርብ አይችልም" ብለዋል።

የቀድሞው ፕሬዝደንት በስልጣን ዘመናቸው ተፈጽመዋል የተባሉ የሙስና ጉዳዮች እየተመለከተ በሚገኘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠይቀው ሳይገኙ በመቅረታቸው ፍርድ ቤትን በመድፈር ጥፋተኛ ተብለው ተፈርዶባቸዋል።

15 ወራትን በእስር እንደሚያሳልፉ የተገለጸው ዙማ በስልጣን ዘመናቸው ምንም ዓይነት ሙስና አለመፈጸማቸውን ይከራከራሉ።

የጃኮብ ዙማ ጠበቆች ዛሬ ለአገሪቱ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለት የፍርድ ጊዜውን ለማሳጠር ይሞክራሉ ተብሏል።