ፍትሕ፡ በሐሰት ተመስክሮባቸው ከ5 ዓመት እስር በኋላ የተለቀቁት ኢትዮጵያዊት እናት ምን ይላሉ?

የፎቶው ባለመብት, ENA
በሰሜን ሸዋ ዞን ሞጃና ወደራ ወረዳ 'የእንጀራ ልጃቸውን ገድለዋል' በሚል 20 ዓመት የተፈረደባቸው ሴት ከአምስት ዓመታት እስር በኋላ ነጻ መውጣታቸውን የዞኑ ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ለቢቢሲ ገለጸ።
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ እና የጥበቃና መረጃ ደኅንነት ቡድን መሪ ኮማንደር ዘውገ ጌታቸው 'ተገድላለች' የተባለችው ልጅ በሕይወት በመገኘቷ አዛለች ቤተ የተባሉት ሴት ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም ከእስር መለቀቃቸውን ተናግረዋል።
ይህ ለመሆኑ አሁንስ በቂ ማስረጃ አላችሁ ወይ ተብለው የተጠየቁት ኮማንደር ዘውገ፤ "ተገድላለች የተባለችው ልጅ በአካል መምጣቷ ለፖሊስ ጥቆማ ከደረሰ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውላ በየደረጃው ባሉ የፍትሕ አካላት በቂ ማጣራት ተደርጓል" ብለዋል።
ልጅቷ መገኘቷ ከተረጋገጠ በኋላም በ2010 ዓ.ም የወጣውን የሕግ ታራሚዎች የይቅርታ መመሪያ መሠረት በማድረግ ወ/ሮ አዛለች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ለክልሉ የይቅርታ ቦርድ እንዳሳወቁና ከክልል ምክር ቤቱ ውሳኔ በኋላ ሴትየዋ በይቅርታ መለቀቃቸውን ኮማንድር ዘውገ አስረድተዋል።
ወ/ሮ አዛለች "በ2006 ዓ.ም የእንጀራ ልጃቸውን ገድለዋል" ተብለው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት በ2007 ዓ.ም ነበር።
ወ/ሮ አዛለች እንደዋዛ በእስር ስላሳለፏቸው ዓመታት ምን ይላሉ?
ወ/ሮ አዛለች ቤተ አሁን 55 ዓመታቸው ነው።
በሰሜን ሸዋ ሰላ ድንጋይ በተባለች አነስተኛ ከተማ ከባለቤታቸው እና ከባለቤታቸው ሦስት ልጆች ጋር ነበር የሚኖሩት።
ባለቤታቸው በጥበቃ ሥራ ተሰማርተው፤ እርሳቸው ደግሞ ዳቦ እየሸጡ ኑሯቸውን በፍቅር ይመሩ ነበር። በመካከል ግን ባለቤታቸው ባደረባቸው ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ባለቤታቸው በሞት ከተለዩ በኋላ ግን ሕይወት እንደተለመደው አልቀጠለም።
ከሦስት የእንጀራ ልጆቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት እየሻከረ መጣ።
በ2006 ዓ.ም ግድያው ተፈጽሟል በተባለበት ቀንም በወ/ሮ አዛለችና 'የ22 ዓመት ወጣት ናት' ባሏት የእንጀራ ልጃቸው መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። እርሳቸው እንደሚሉት አለመግባባቱ የእናትና የልጅ እንጂ ያን ያህል የተካረረ አልነበረም።
በርግጥ ከዚያም በፊት በተፈጠረ አለመግባባት ልጅቷ ከቤት ወጥታ ሦስት ወር ከቆየች በኋላ ተመልሳለች። በወቅቱም ዘመድ ጋር መሄዷን ነበር ያረጋገጡት።
ተገደለች በተባለችበት ዕለትም በተፈጠረ አለመግባባት ሻንጣዋን ይዛ ከቤት ስትወጣ "ልማዷ ነው ብዬ ዝም አልኩ" ይላሉ ወ/ሮ አዛለች።
እንደተለመደው ዘመድ ጋር ትሄዳለች እንጂ የውሃ ሽታ ሆና ትቀራለች ብለው አላሰቡም ነበር።
ድምጿ ሲጠፋ ለአጎቷና ለአክስቷ 'አስፈልጓት' ሲሉ ተናገሩ። እርሳቸውም ማጠያየቅ ያዙ። እርሷ ግን የለችም።
በጭንቀት ጉዳዩን ከሚነግሯቸው ሰዎችም "ሕጻን ልጅ አይደለችም ፤ የት ትሄዳለች ብለሽ ነው። ትመጣለች" የሚል መልስ ነበር የሚያገኙት።
ጊዜው ነጉዶ ልጅቷ ከቤት ከወጣች አንድ ዓመት አለፋት።
ወ/ሮ አዛለች ዳቦ በሚሸጡበት አካባቢ 'ገድላታለች!' የሚል ጉምጉምታ መስማት ጀመሩ።
በዚህ ግራ የተጋባ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ልጅቷ በጠፋች ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ፖሊስ ወደ ቤታቸው መጣ።
በወቅቱ የዳቦ ሊጥ እያቦኩ ነበር። ፖሊስ ጣቢያ እንደሚፈለጉ ሲነገራቸው የሚያሳድጉትንና የባለቤታቸው የክርስትና ልጅ ነው ያሉትን የ7 ዓመት ታዳጊ ይዘው ወደዚያው አመሩ።
'በግድያ ስለተጠረጠሩ ማረፊያ ቤት ይግቡ' ተባሉ።
ያቦኩትን ሳይጋገሩ፣ የተጋገረውን ሳይሸጡ፤ ደጃቸውን እንኳን በውል ሳይዘጉ እዚያው ቀሩ። ዘመድ ጋር ደውለው "ቤቴን አደራ" ከማለት ውጪ ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም።
"ልጅቷን ገድለሽ ሽንት ቤት ጨምረሻታል"
ወ/ሮ አዛለች "ልጅቷን ገድለሽ ሽንት ቤት ጨምረሻታል" በሚል ተጠርጥረው መያዛቸው ተነገራቸው። ሽንት ቤቱን እንዲያስፈትሹ ታዘዙ።
"ለቀን ሠራተኛ 150 ብር ከፍዬ ሽንት ቤቱ ተፈተሸ" ይላሉ ወ/ሮ አዛለች። ይህ የሆነው እርሳቸውም ባሉበት ነበር።
"አስክሬን አለ፤ በሰው ኃይል አይሆንም፤ ሽንት ቤት የሚመጥ መኪና ይምጣ" ተባለ፤ መጣ።
የተማሪ የደንብ ልብስና ፀጉር ተገኘ [ወ/ሮ አዛለች እንደሚሉት ልጅቷ ትጠቀምበት የነበረ አርተፊሻል ፀጉር ነው] አገሬው ግልብጥ ብሎ ወጣ። ጉድ ተባለ። "ገድላለች! ትገደል!" የሚል ሀሳብም ከአገሬው ሰው መስተጋባት ጀመረ።
ወ/ሮ አዛለች ተመልሰው ፖሊስ ጣቢያ ገቡ። በድጋሚ ቤታቸውና ግቢው ተቆፈረ- አስክሬን ፍለጋ ። ምንም አልተገኘም።
"እውነቱን አውጭ እየተባልኩ ድብደባም ተፈጽሞብኛል፤ አሁን ላይ ያንን ከባድ ነገር ለማንሳት እቸገራለሁ" ይላሉ- ወ/ሮ አዛለች።
የምርመራ ሂደቱ በዚህ መልኩ ቀጥሎ የሰሜን ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት "በከባድ ሰው መግደል ወንጀል" 20 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ውሳኔ አስተላለፈ። ደብረብርሃን ማረሚያ ቤት ገቡ።
በሰው ግድያ ምክንያት የተጣሉ ሰዎችን የሚያስታርቁ ሽማግሌዎች [በእርሳቸው አገላለፅ የደም አስታራቂ] "እኛ ልጅቷ መሞቷን አናውቅም፤ ገድያለሁ ብላ ትመንልን" እያሉ ይወተውቷቸው እንደነበርም ወ/ሮ አዛለች ያስታውሳሉ።
እርሳቸው ግን "አላምንም" አሉ።
"'ሞተች ብሎ ፍርድቤቱ ቀጥቶኛል፤ እግዚአብሔር ከፈቀደ እወጣለሁ፤ ካልፈቀደም ሬሳዬ ይወጣል' አልኩ" ይላሉ።
ወ/ሮ አዛለች በተደጋጋሚ "እኔ አልገደልኩም" እያሉ ይወተውቱ እንደነበር ኮማንደር ዘውገ ተናግረዋል።
ዓመታት ነጎዱ።
በዚህ መካከል ወ/ሮ አዛለች ከወንድ ታራሚዎች አካባቢ ልጅቷ አዲስ አበባ ነው ያለችው የሚል ጉምጉምታ ሰሙ።
ጉዳዩን የሚከታተል ዐቃቤ ሕግ ሊያነጋግራቸው ሲሄድ የሰሙትን በማስረዳት "እባካችሁ ልጅቷን ፈልጉልኝ" ሲሉ አልቅሰው ተማጸኑ።
ወ/ሮ አዛለች እንደሚሉት ዐቃቤ ሕግና ፖሊስ ቃለ ጉባኤ ይዘው ለፍለጋ ሲሰማሩ [ይህን የሚያውቅ ቤተሰብ ነገራት መሰል ይላሉ] በ15 ቀን ውስጥ ልጅቷ ከነበረችበት ሰላ ድንጋይ ከተማ ከተፍ አለች።
"ሞተች የተባለችው ልጅ 'ደቡብ ክልል ሄዳ፣ አግብታ፣ ልጅ ወልዳ መጥታለች፤ ታስራለች' አሉኝ" ይላሉ ወ/ሮ አዛለች።
ወ/ሮ አዛለች ይህንን ሲሰሙ ማመን አቃታቸው። "ራሴን ስቼ ወደቅኩ" ይላሉ።
በፖሊስ ከተያዘች በኋላ የተነሳችውን ፎቶ ሲያሳዩዋቸው ነበር መረጋጋት የቻሉት።
አሁን ልጅቷ እርሷ መሆኗ ተረጋግጦ ከእስር መለቀቋን ወ/ሮ አዛለች ሰምተዋል። በአካል ግን አልተገናኙም።
ሕይወት ከ5 ዓመታት እስር በኋላ
ወ/ሮ አዛለች ከእስር ወጡ በኋላ ወደ ቀያቸው አልተመለሱም። 'በሐሰት ያሳሰሩኝ ለሕይወቴም አይመለሱም' የሚል ስጋት አላቸው። ቀረኝ የሚሉት ሀብትም የለም።
"አራት ክፍል ቤት ነበረኝ ተሸጧል። እንዴት እንደተሸጠ አላውቅም፤ የባለቤቴ መሬትም ተሸጧል፤ ከየት እንደምጀምር አላውቅም ፤ ሜዳ ላይ ነው የወደቅኩት" ይላሉ።
ለደረሰባቸው በደል ካሳ ከተሰጣቸው ነው ኑሯቸውን ሀ ብለው ለመጀመር ያሰቡት።
ወ/ሮ አዛለች ክስ የመመስረት ሃሳብ ግን እንደሌላቸው ተናግረዋል።
"ዛሬ አንድ ወረቀት ለማጻፍ 700 እና 800 ብር ነው የሚጠየቀው፤ እንኳን ለዚህ የምበላው የለኝም፤ ከሳሽ ፈጣሪ ነው፤ ፈጣሪ ይክሰሳቸው" ብለዋል።
ወ/ሮ አዛለች እንደሚሉት ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅል መነሻ የሆነችውን የእንጀራ ልጃቸውን ያሳደጓት እርሳቸው ናቸው። እስከ ስምንተኛ ክፍልም አስተምረዋታል።
"በጣም ነው የምወዳት፤ ይቅርታ መጠየቅ ካሸነፋት፤ እኔ እንደ እናት ይቅርታ እጠይቃታለሁ" ብለዋል።
"ከአምስት ዓመቱ እስር የአራት ወራቱ ይበልጥ አበሳጭቶኛል"
ወ/ሮ አዛለች ገድለዋታል የተባለችው ልጅ በሕይወት መገኘቷን ተከትሎ በነጻ እንዲሰናበቱ የተወሰነላቸው ከአራት ወራት በፊት የካቲት ወር ላይ ነበር። ይሁን እንጂ አራት ወራትን ሳይፈቱ ቆይተዋል።
"ከአምስት ዓመቱ እስር ነጻ መሆኔ ከተወሰነ በኋላ የታሰርኩት አበሳጭቶኛል" ይላሉ።
ይቅርታ ሊጠየቁ ሲገባቸው እንዲጉላሉ በመደረጋቸውም የፍትሕ ሥርዓቱን ወቅሰዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን የማረሚያ ቤቶች መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር ዘውገ፤ ወ/ሮ አዛለች ቤተ ያለምንም ወንጀል እስር ላይ እንደቆዩ እና እንዲለቀቁ ለክልሉ የይቅርታ ቦርድ ማመልከቻ በወቅቱ መጻፉን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ወ/ሮ አዛለች እንዲፈቱ ከክልሉ የይቅርታ ቦርድ የደብዳቤው ምላሽ በመዘግየቱ ነጻ ከተባሉ በኋላ ማረሚያ ቤት ለመቆየት መገደዳቸውን ኮማንደር ዘውገ ተናግረዋል።
"በወቅቱ በፀጥታ ጉዳይ የተለያዩ አመራሮች በሥራ መብዛት ምክንያት ባለመገኘታቸው የይቅርታ ቦርዱ መሰብሰብ አለመቻላቸውን ነው ያሳወቁን" ያሉት ኮማንደሩ፤ "ሴትየዋ ያለ ወንጀላቸው ተጨማሪ ጊዜ መቆየታቸው ስህተት ነው፤ በዚህም ተጸጽተናል" ብለዋል።












