በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቁበት የቤልግሬዱ የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ሰለሞን ባረጋ

የፎቶው ባለመብት, World Athletics

የምስሉ መግለጫ, ሰለሞን ባረጋ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ነው

ሰርቢያ ቤልግሬድ ውስጥ ዛሬ ከመጋቢት 9 ተጀምሮ አስከ 11/2014 ዓ.ም በሚቆየው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና አፍሪካዊያን አትሌቶች ሜዳሊያ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኬንያዊው አትሌት ፈርዲናንድ ኦሙርዋ ኦማንያላ ከእነዚህ መካከል አንዱ ሲሆን የዩሴይን ቦልትን የ100 ሜትር የዓለም ክብረወሰን መስበር እንደሚችል ተናግሯል።

ኬንያዊው አትሌት በሰርቢያው ሻምፒዮና ውድድሩን 60 ሜትር ይጀምራል።

የ26 ዓመቱ አትሌት በ9.77 በሆነ ሰከንድ የአፍሪካን የ100 ሜትር ክብረወሰን በእጁ አስገብቷል። በአጭር ርቀት መሻሻል ካሳየ የቦልትን ክብረ ወሰን (9.58 ሰከንድ) ለመስበር እንደሚረዳው ያምናል።

"ምንም የማይቻል ነገር የለም ብዬ አምናለሁ። የዓለም ክብረ ወሰን የሚሳካ ነገር ነው" ሲል ኦማንያላ ለቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ተናግሯል።

"ይህን ክብረ ወሰን መስበር የሚችል ሰው ካለ እኔ ነኝ ብዬ አምናለሁ።''

"የአፍሪካን ክብረ ወሰን ተመልከቱ። ሩጫ ስጀምር ሰዎች በቅርቡ አይሰበርም ብለው አስበው ነበር። ይህን ግን ባለፈው ዓመት አሳክቻለሁ።''

ይህም የኦማንያላ ክብረወሰን የምንጊዜም ፈታኝ ሰዓቶች ስምንተኛው አድርጎታል። ይህን ግን ያሳካው የ14 ወራት የአበረታች መድኃኒት እገዳ በ2017 ከተጣለበት በኋላ ነው።

መድኃኒቱ የተገኘበት በውስጡ ስቴሮይድ አለበት ያለውን የህመም ማስታገሻ ከወሰደ በኋላ መሆኑን ጠቅሶ "በሁኔታው ተጎድቻለሁ" ብሏል።

ሻምፒዮን ለመሆን ጣሊያናዊውን የ100 ሜትር የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ማርሴል ጃኮብስን እና የወቅቱን የቤት ውስጥ ሻምፒዮን አሜሪካዊውን ክርስቲያን ኮልማንን ማሸነፍ ይኖርበታል።

ኬንያዊው አትሌት ፈርዲናንድ ኦሙርዋ ኦማንያላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኬንያዊው አትሌት ፈርዲናንድ ኦሙርዋ ኦማንያላ

በቤልግሬድ የሚወዳደሩ ሌሎች አፍሪካውያንስ?

በ2022ቱ የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ከ137 አገራት የተውጣጡ 680 አትሌቶች ይሳተፋሉ። ውድድሩ ከመጋቢት 9 እስከ 11/2014 ሰርኒያ ቤልግሬድ ውስጥ ይካሄዳል።

ስድስቱ ተጠባቂ አፍሪካዊያን

ሰለሞን ባረጋ (ኢትዮጵያ) - የ22 ዓመቱ አትሌት የ10,000 ሜትር የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ነው። በ2018 በዓለም የቤት ውስጥ ውድድር በ3000 ሜትር ያገኘውን የብር ሜዳሊያ ለማሻሻል ይወዳደራል።

ለሜቻ ግርማ (ኢትዮጵያ) - በ3000 ሜትር መሰናክል የዓለም እና የኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ነው። የ21 ዓመቱ አትሌት የ3000 ሜትር አሸናፊ ለመሆን ከሰለሞን ጋር ይፎካከራል።

ሳሙኤል ተፈራ (ኢትዮጵያ) - የ1500ሜ የዓለም የቤት ውስጥ ክብረ ወሰን ባለቤት ሲሆን በ2018 በርሚንግሃም ላይ ያገኘውን የወርቅ ሜዳሊያ ለማስጠበቅ ይወዳደራል።

ጉዳፍ ፀጋይ (ኢትዮጵያ) - የ5,000 ሜትር የኦሊምፒክ እና የ1500 ሜትር የዓለም ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ 24 ዓመቷ አትሌት በ1500 ሜትር ትጠበቃለች።

ኢሴ ብሩሜ (ናይጄሪያ) - የኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊዋ የ26 ዓመቷ አትሌት፣ የአፍሪካ ሻምፒዮን ናት። በሴቶች የአግድሞሽ ዝላይ ውድድር ትሳተፋለች።

ሃሊማ ናካዪ (ኡጋንዳ) - የ27 ዓመቷ አትሌት በ2019 ዶሃ ላይ ባስመዘገበችው የ800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮና ወርቅ ላይ ተጨማሪ ድል ለማስመዝገብ ትፎካከራለች።

ያሲር ትሪኪ (አልጄሪያ) - ባለሦስትዮሽ ዝላይ (ትሪፕል ጃምፕ) በ16.95 ሜትር በመዝለል ከወቅቱ የዓለም ምርጥ 5ቱ ውስጥ ተካቷል።