ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በሠራተኞቹ ግድያ ዙሪያ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ አቀረበ

የፎቶው ባለመብት, MSF
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ባለፈው ዓመት ትግራይ ውስጥ ስለተገደሉት ሠራተኞቹን በተመለከተ የዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባን ተከትሎ በግድያው ዙሪያ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡን ገለጸ።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በጋዜጣው ላይ የቀረበው ዘገባ ለሠራተኞቼ ግድያ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል እና አዛዡን ተጠያቂ ያደርጋል ያለ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ሪፖርት ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቋል።
የኤምኤስኤፍ-ስፔን ፕሬዝደንት ፖውላ ጊል ትናንት ሐሙስ ባወጡት መግለጫ የሠራተኞቹን ግድያ በተመለከተ ድርጅቱ በራሱ ያካሄደው ምርመራ በቀጥታ ገዳዮቹ እነማን እንደሆኑ እና ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻለም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ፕሬዝደንቷ ከዚህ ቀደም የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሠራተኞቹ የተገደሉት ሆን ተብሎ በቅርብ ርቀት በተደጋጋሚ በጥይት ተመትተው ነው ብለው ነበር።
ጋዜጣው በበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሠራተኞች ላይ ግድያ የፈጸሙት የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት መሆናቸውን የሚገልጽ ዘገባ ካወጣ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት አስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።
ኒው ዮርክ ታይምስ በዘገባው ምን አለ?
ሰኔ 17/2013 ዓ.ም. ሦስት የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች በትግራይ ክልል ለሰብዓዊ ሥራ እየተጓዙ ሳለ ከቅርብ ርቀት በተተኮሰባቸው ጥይት መገደላቸው ይታወሳል።
ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የሦስቱን ግለሰቦች ግድያ በተመለከተ በሰራው ዘገባ፤ የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች የተገደሉት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ነው ብሏል።
ጋዜጣው የመከላከያ ሠራዊት አባላት፤ የእርዳታ ሠራተኞች እና ግድያውን የሚመረምሩ ሰዎችን ዋቢ አድርጎ በሰራው ዝርዝር ዘገባ፤ ሦስቱ ሠራተኞች እያፈገፈጉ በነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መገደላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
በጥቃቱ የተገደሉት የኤምኤስኤፍ ረዳት አስተባባሪ የነበረው የ31 ዓመቱ ዮሐንስ ሃለፎም፣ የግብረ ሰናይ ድርጅቱ አሸከርካሪ የነበረው የ31 ዓመቱ ቴድሮስ ገብረ ማሪያም እና ለዓመታት የድንገተኛ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ የነበረችው የ34 ዓመቷ ስፔናዊት ማሪያ ኽርናንዴዝ ናቸው።
ሦስቱ የሰብዓዊ ድርጅቱ ሠራተኞች በተገደሉበት ዕለት ከመቀመጫቸው አቢ አዲ ወደ ደቡብ አቅጣጫ በጦርነት የተጎዱ ሰዎችን ፈልገው ለመርዳት ሲጓዙ ነበር በማለት አንድ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኛ ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግራል።
በዕለቱ ከሰዓት 9 ሰዓት አካባቢ ሼዌት ሁጉማ ተብሎ ወደሚጠራ መንድር ለመድረስ 2 ኪሎ ሜትሮች ያክል ሲቀራቸው ሲጓዙባት የነበረችው ላንድ ክሩዘር መኪና በተመሳሳይ አቅጣጫ ሲጓዝ ከነበረ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መኪኖች ጀርባ ይደርሳል።
ይህም የ31ኛ ዲቪዥን ኮማንደር ለሆኑት ኮሎኔል ታደሰ በቀለ ሪፖርት መደረጉን በአካባቢው የነበሩ ስድስት የመከላከያ ሠራዊት አባላት ለኒው ዮርክ ታይምስ መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
መኪናቸው ውስጥ ሳሉ ተኩስ የተከፈተባቸው ሦስቱ የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች እራሳቸው ከዒላማ ለማዳን ከመኪናቸው ወርደው ነበር።
በመጨረሻም ዮሐንስ፣ ቴድሮስ እና ማሪያ የተባሉት የእርዳታ ድርጅቱ ሠራተኞች በ31ኛ ዲቪዥን ኮማንደር ትዕዛዝ ከቅርብ ርቀት ተመትተው መገዳለቸውን ሻምበል ግርማይ ሞገስ የተባለ የመከላከያ ሠራዊት አባል እንደነገሩት ኒው ዮርክ ታይምስ ገልጿል።
እነዚህ ጋዜጣው የጠቀሳቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ኃይሎች ተማርከር በመቀለ እስር ቤት የሚገኙ ናቸው። ኒው ዮርክ ታይምስ እነዚህ የጦር አባላት ቃላቸውን የሰጡት ጫና ውስጥ ሆነው ስለመሆኑ ምንም ምልክት አላገኘሁም ብሏል።
የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሠራተኞቹ እንዲገደሉ ትዕዛዝ የሰጠው የጦር መኮንን በጦር ግንባር ላይ ስለመገደሉ ከበርካታ ወታደሮች ሰምቻለሁ ብሏል።

በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች ክልሎች በስተፋፋው ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት አስከትሏል።
ምዕራባውያን አገራት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በዚህ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት አካላት በሙሉ የጦር ወንጀል ሊሆን የሚችል ጥፋት ፈጽመዋል ይላሉ።
ለሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ውድመቶች ተጠያቂ የሆኑ የጦር አባላት በሕግ እንዲዳኙም ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል።
ምንም እንኳ የትግራይ ኃይሎች በመብት ጥሰት ተጠያቂ ያደረጓቸው የጦር አባላቶቻቸው ስለመኖራቸው እርግጥ ባይሆንም፤ የፌደራሉ መንግሥት ግን በጦር ቀጠናዎች ውስጥ ሕግ የተላለፉ ናቸው ባላቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ክስ መስርቶ፤ የጥፋተኝነት ውሳኔም ማስተላለፉ ተነግሯል።















