ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም ምን እንዲሟላ ይሻሉ? ለኤርዶዋንስ ምን ነገሯቸው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቱርክ ከሩሲያም ከዩክሬንም ወገን ሳትሆን ከአስታራቂዎቹ ወገን ራሷን በመመደብ ሁለቱን ሃገራት ለማግባባት ደፋ ቀና እያለች ነው።
ሐሙስ ከሰዓት የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ለቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ስልክ መተዋል።
ፑቲን ከኤርዶዋን ጋር በነበራቸው የስልክ ወይይት የሩሲያን ፍላጎት ዘርዝረው አስረድተዋቸዋል።
ስልክ ከተዘጋ ከ30 ደቂቃ በኋላ የኤርዶዋን ዋና አማካሪና ቃል አቀባይ ኢብራሂም ካሊን ለቢቢሲ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
ኢብራሂም የስልክ ልውውጡን ካዳመጡ ጥቂት ሰዎች መካከል ናቸው።
የሩሲያ ፍላጎት ምንድነው?
ሩሲያ ይህ ጦርነት እንዲቆም የምትሻው የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው። እኚህ ቅድመ ሁኔታዎች በሁለት ይከፈላሉ።
ቃል አቀባዩ እንደሚሉት ሩሲያ ከደረደረቻቸው ቅደመ ሁኔታዎች መካከል አራቱ ዩክሬን ልታሟላቸው የምትችላቸው ናቸው።
ዋናው የሩሲያ ፍላጎት ዩክሬን የኔቶ አባል እንዳትሆን ነው። ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ይህንን አምነው የተቀበሉ ይመስላሉ።
ሩሲያ፤ ዩክሬን ትጥቅ እንድትፈታ ትሻለች፤ በዩክሬን የሩሲያ ቋንቋ እንዲከበር ትጠይቃለች፤ አልፎም 'ዲ-ናዚፊኬሽን' እንዲካሄድ ትፈልጋለች።
ዲ-ናዚፊኬሽን አሊያም በግርድፍ ትርጉሙ የናዚ ሥርዓትን መፋቅ የሚለው የሩሲያ መርህ ለዜሌንስኪ የሚዋጥ አይደለም።
ዜሌንስኪ አይሁድ ናቸው። ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በሆሎኮስት ዘመን አጥተዋል።
ቱርክ ግን ይህን ለስምምነት የሚከብድ ነጥብ አይደለም ትላለች። ዩክሬን ኒዎ-ናሲዚምን ማውገዝ ብቻ ነው የሚጠበቅባት ትላለች ቱርክ።
በሁለተኛው ጎራ ያሉ ቅድመ ሁኔታዎች ቱክርም ሆነች ሌላ አስታራቂ ሃገር በቀላሉ ሊያደርገው የሚችለው አይደለም።
ፑቲን ከኤርዶዋን ጋር ሲያወሩ ይህ ጦርነት የሚቆመው ከፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ጋር በአካል ተገኛኝተው ከተደራደሩ እንደሆነ ይናገራሉ።
ዜሌንስኪ ከዚህ በፊት ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር ተገናኝተው ቁጭ ብለው ለማውራት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረው ነበር።
ቃል አቀባዩ ካሊን እንደሚሉት ሁለቱ መሪዎች ከተገናኙ ስለዶንባስ ማውራት አለባቸው። በምስራቅ ዩክሬን የምትገኘው ዶንባስ ደግሞ በሩሲያ እጅ ወድቃለች።
ሩሲያ፤ ዩክሬን የዶንባስን ባለቤትንትን አሳልፋ እንድትሰጣት ትፈልጋለች። የክሬሚያ ጉዳይም እንዳለ ነው። ታድያ ይህ ለዩክሬን ቀላል ይሆናል ብሎ ማሰብ ራሱ ቀላል አይደለም።
ዩክሬን ዶንባስንና ክሬሚያ በኦፊሴላዊ መንገድ ለሩሲያ አሳልፋ ሰጠች ማለት ሽንፈትን ፈቅዳ ተቀበለች ማለት ነው።
ሩሲያ ኮሚዩኒዝም በወደቀ ጊዜ ክሬሚያ የራሷ ግዛት አለመሆኗን የሚያሳይ ወረቀት ላይ ፈርማለች። ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነው ፕሬዝደንት ፑቲን ወደሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ነው።
ይህ ያልተዋጠላቸው ፑቲን በነሱ አቆጣጠር 2014 በግድ ክሬሚያን ከዩክሬን ገንጥለው መውሰዳቸው ይታወሳል።
ፑቲን ከኤርዶዋን ጋር የተነጋገሩባቸው ነጥቦች ብዙዎች እንደፈሩት ለማሟላት የሚከብዱ አይደሉም።
ፑቲን ያሉት ቢሳካላቸው በይፋ ጦርነቱን አሸነፉ ማለት ነው። ዩክሬን ግን ቅድመ ሁኔታው ብትቀበል ሩሲያ ሌላም ጊዜ ልትወረኝ ትችላለች የሚል ስጋት ይፈጥርባታል።
ሁለቱ ሃገራት ሰላም ለማውረድ በቀላሉ ይስማማሉ ተብሎ አይጠበቀም። ነገር ግን የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ ቢያንስ ደም መፋሰሱን ሊገታው ይችላል።
በዚህ ጦርነት ዩክሬን ከፍተኛ ቁሳዊ ኪሳራ ደርሶባታል። በሩሲያ ጦር ከጥቅም ውጭ የሆኑ ከተሞችን መልሶ መገንባት ዓመታት የሚፈጅ ነው።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤት ንብረታቸው ጥለው የተሰደዱ ዜጎቿን ተቀብላ ማስተናገድም ይጠበቅባታል።
ፑቲንስ?
ፑቲን የጤና መቃወስ ሳያጋጥማቸው አይቀርም የሚሉ ወሬዎች መሰማት ጀምረዋል። የአእምሮ ሕመም ሳያጋጥማቸውም አይቀርም የሚሉ ወሬዎች ሾልከዋል።
ፑቲን የስልክ ልውውጥ ላይ ሳሉ እንደው ጤንነታቸው ምን ይመስል ነበር ተብለው የተጠየቁት ቃል አቀባዩ "ኧረ ፍፁም ጤነኛ ነበሩ" ሲሉ መልሰዋል።
ፑቲን፤ ኔዎ ናዚስምን ቀብረው የዩክሬን ጦርነት በድል ቢቋጩ እንኳ ሃገር ቤት ሰላም ይጠብቃቸዋል ማለት አይደለም።
በርካታ ሰዎች ፑቲን በዚህ ጦርነት ያላሰቡት ነገር እንደገጠማቸው ይስማሙበታል።
በዚህ ጦርነት በዩክሬን ጦር የተገደሉ የሩሲያ ጦር አባላት ዜናም ወደ ሞስኮው ማቅናት ጀምሯል።












