ኢንጂኒየር ስለሺ በአሜሪካ፣ ጄነራል ባጫ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a
ባለፉት ዓመታት የውሃ፣ ኢነርጂ እና መስኖ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር ኢ/ነ ስለሺ በቀለ በአሜሪካ እንዲሁም ጄነራል ባጫ ደበሌ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ።
ዛሬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ በቅርቡ በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የአምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸው ዲፕሎማቶች የተመደቡባቸውን አገራት ይፋ አድርገዋል።
በዚህ መሠረት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሲነሳ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ኢንጂኒየር ስለሺ በቀለ መቀመጫቸውን ዋሸንግተን ዲሲ በማድረግ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲሆኑ ተመድበዋል።
ቀደም ሲል በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሲሰሩ የቆዩት ፍጹም አረጋ የነበሩ ሲሆን አሁን ይፋ በተደረገው የምደባ ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም።
ዶክተር ኢንጂኒየር ስለሺ በቀለ የውሃ፣ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትር ከዚያም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድንበር ተሻጋሪ ወሃዎችን አማካሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው አዲስ አበባ ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመረጣቸው ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force/fb
እንዲሁም ከትግራይ ጦርነት ጋር በተያያዘ ስማቸው ጎልቶ የወጡት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች አምባሳደር ባጫ ደበሌ እና አምባሳደር ሀሰን ኢብራሂም ኬንያ እና ግብፅ ተመድበዋል።
ጄነራል ባጫ ከትግራዩ ጦርነት መቀስቀስ በኋላ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ከጥቂት ወራት በፊት ነበር የሙሉ ጄነራልነት ሹመትን ያገኙት።
አምባሳደር ተፈራ ደርበው ጃፓን የተመደቡ ሲሆን፣ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ-ደቡብ ኮሪያ፣ አምባሳደር ዳባ ደበሌ-ሩዋንዳ፣ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው-አውስትራሊያ፣ አምባሳደር ምህረተአብ ሙሉጌታ-ስዊዲን፣ አምባሳደር ፍቃዱ በየነ-ኤርትራ ተመድበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ተቀማጭነታቸው በኢትዮጵያ ሆኖ በተለያዩ አገራት የሚሰሩ እና ምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደሮች መሾማቸውን ዲና ሙፍቲ ገልጸዋል።












