ከልዑል ቻርልስ የብሪታኒያን የክብር ኒሻን የተጎናፀፈው ለምን ሲሳይ ምን ይላል?

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ገጣሚ ለምን ሲሳይ በቅርቡ ያገኘውን ክብር "ወጣት ሳለሁ የነበረውን አስከፊ ጊዜ ላሳለፍኩት ጊዜ" መታሰቢያ ይሁንልኝ ብሏል።
ለምን፤ ኦቢኢ [ኦርደር ኦፍ ዘ ብሪቲሽ ኢምፓዬር] የተሰኘው ክብር ተሰጥቶታል።
የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር የሆነው ለምን በእንግሊዟ ዊጋን ከተማ በወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያ ነው ያደገው።
"ወጣቱ እኔ" በጭራሽ ይህን ክብር አገኛለሁ ብሎ አያስብም ይላል ለምን። ወጣቱ ለምን ሲሳይ ራሱን ለሥነ-ፅሑፍና ሰብዓዊ እርዳታ አሳልፎ የሰጠ እንደነበርም ያወሳል።
ለምን በፈረንጆቹ 1967 ትምህርት ለመቅሰም ወደ እንግሊዝ ካቀናችው ኢትዮጵያዊ እናቱ ነው የተወለደው።
ዊጋን ከተማ ወደሚገኝ የሕፃናት ማሳደጊያ ከተወሰደ በኋላ ስሙ ኖርማን ግሪንዉድ ተባለ።
በ18 ዓመቱ እናቱን መልሶ ካገኛት በኋላ ስሙ ለምን እንደሆነ ነገረችው። ሕፃናት ማሳደጊያ ሳለ መልሳ በእቅፏ ልታሳድገው ብዙ እንደጣረችም አስረዳችው።
ለምን ልጅ ሳለ የደረሰበትን በደል አስመልክቶ ከዊጋን ከተማ ምክር ቤት ጋር ለ34 ዓመታት ተካሷል፤ ተውቅሷል። በስተመጨረሻም በፍርድ ቤት ድል ማድረግ ችሏል።
'ዊንድሰር ካስል' በነበረ ደማቅ ሥነ-ሥርዓት ይህን ክብር ያገኘው ለምን "ሰዎች ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ክብር ሲያገኙ ለእናቴ አሊያም ለአባቴ እስክናገር ቸኩያለሁ ይላሉ። ምንክያቱም የሚያኮራ ነገር ስለሆነ" ብሏል።
"ነገር ግን እኔ ይህ የለኝም። እንግዲህ ይህ ታሪኬ ነው። በኔ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳረፈ ታሪኬ ነው" ሲል ተናግሯል።
ለምን ወጣት ሳለ የሚያውቀው ማንነቱ የኦቢኢ ክብር እንዳገኘ ቢያውቅም ደስታውን መቆጣጠር እንደሚሳነው ይናገራል።
"ለጎረምሳው ለምን፤ አንድ ቀን ዊንደሰር ካስል ውስጥ ከልዑል ቻርልስ የኦቢኢ ክብር ትቀበላለህ ብዬ ብነግረው፤ ይህን ዓይነት ተረት የመሰለ ንግግር አምኖ አይቀበለኝም ነበር።"
ይህን ክብር የምቀበለው ይላል ለምን "ይህ ክብር የምቀበለው በ18 ዓመቱ የሕፃናት ማሳደጊያን ጥሎ ለወጣ፤ ቤተሰቦቹን ላጣ፤ በዚያ ዕድሜው ማንንም ጠልቆ ለማያውቀው፤ በርካታ የገና በዓላትን ብቻውን ላሳለፈው ማንነቴ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ከኢትዮጵያዊ እናት የተገኘው ገጣሚ ለምን ሲሳይ የብሪታኒያ መንግሥት በሙያቸው ብዙ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጠውን ክብር ከልዑል ቻርልስ እጅ ተቀብሏል።
ለምን የመጀመሪያውን የግጥም መድብሉን የ21 ዓመት ወጣት ሳለ ነው ያሳተመው።
'ማይ ኔም ኢዝ ዋይ' አሊያም በግርድፍ ትርጉሙ 'ስሜ ለምን ነው' በተሰኘው መፅሐፉ የብሪታኒያን የሕፃናት ማሳደጊያ ማዕከላትን ታሪክ ልቅም አድርጎ ይተነትናል።
በፈረንጆቹ 1995 ኢንተርናል ፍላይት የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ከቢቢሲ ጋር በመጣመር ሠርቷል።
ሰምቲንግ ዳርክ የተሰኘው ብቻውን የሚተውንበት የራድዮ ቅንብርም በቢቢሲ ራድዮ 3 ጣቢያ ተላልፎለታል።
ለምን ኤምቢኢ የተሰኘውን ክብር የተጎናፀፈው በፈረንጆቹ 2010 ነበር። ከማንችስተር ዩኒቨርሲቲ የቻንስለርነት ማዕረግ ያገኘው ደግሞ በ2015 ነው።
"እኔን ለመሰሉ በማሳደጊያ ማዕከላት ለሚገኙ ወጣቶች ይህን ማሳየት ትልቅ ነገር። 'እኔም ይህን ላደርግ እችላለሁ' እንዲሉ ያደርጋቸዋልና" ይላል ለምን።
"እኒህ ወጣቶች 'እኔም ዶክተር መሆን እችላለሁ፣ አሊያም ጠበቃ፣ አሊያም ፀጉር አሳማሪ ወይም ደግሞ እሱ እንደሆነው እሆናለሁ' እንዲሉ ያስችላቸዋል።"












