ፕሬዝደንት ባይደን ፑቲንን 'የጦር ወንጀለኛ' ማለታቸው ሩሲያን አስቆጣ

ፑቲን እና ባይደን እአአ 2021 ላይ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፑቲን እና ባይደን እአአ 2021 ላይ።

የዩናይትድ ሰቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን “የጦር ወንጀለኛ ነው” በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ ተናግረዋል።

ይህ የፕሬዝደንቱ ንግግር በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ሊያሻክረው እንደሚችል ታምኗል።

ፕሬዝደንት ባይደን ይህንን ቃል የተናገሩት ዋይት ሃውስ አንድ ጋዜጠኛ ለሰነዘረላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ነው።

ዋይት ሃውስ ፕሬዝደንቱ “ከልባቸው ነው ይህን ያሉት” ብሏል።

የፕሬዝዳንት ፑቲን ጽህፈት ቤት ግን ይህ “ይቅርታ የማይደረግለት ንግግር ነው” ሲል ቁጣውን ገልጿል።

“በመላው ዓለም በመቶ ሺዎች ሚቆጠሩ ሰዎችን በቦምብ የገደለ ሃገር መሪ መሰል ንግግር ማድረጋቸው ይቅርታ የማይደረግለትና ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲሉ የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ጋዜጠኛው “ፕሬዝደንት ባይደን እንደው ይህን ሁሉ ካየን በኋላ ፑቲን የጦር ወንጀለኛ ሊሏቸው ፈቃደኛ ነዎ?” ሲል ነው የጠየቃቸው።

ፕሬዝደንት መጀመሪያ ካቅማሙ በኋላ ፈርጠም ብለው “አዎ የጦር ወንጀለኛ ነው” ሲሉ መልሰዋል።

የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ በሰጡት መግለጫ ፕሬዝደንት ባይደን “ከልባቸው እንደተናገሩ” ገልጠዋል።

ነገር ግን ይህ ኦፊሴላዊ አይደለም ያሉት ሳኪ፤ ፑቲን የጦር ወንጀለኛ ናቸው አይደሉም የሚለውን ለመወሰን ምርመራ እየተካሄደ ስለመሆኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቀስ በቀስ በአሜሪካና ሩሲያ መካከል ያለው ዲፕሊማሲያዊ ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ ማምራት ጀምሯል።

የፕሬዝደንቱ ንግግር ሞስኮ እና ዋሺንግተን ጉዳዮችን በንግግር እንዳይፈቱ ሊያደርግ እንደሚችል በርካታ ተንታኞች ያምናሉ።

ከዚህ በኋላ አሜሪካ ማንኛውንም ነገር ከሩሲያ ጋር በሰላማዊ መንገድ ለማድረግ ብትቆርጥ “እንዴት ከጦር ወንጀለኛ ጋር?” የሚል ጥያቄ ያጭራል።

ክፕሬዝደንቱ ንግግር ቀደም ብሎ የዩክሬኑ መሪ ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ለአሜሪካ ኮንግረስ አባላት በቪድዮ መስመር ብዙዎች ቆመው እንዲያጨበጭቡ ያስገደደ ንግግር አድርገዋል።

ከዜሌንስኪ መልዕክት በኋላ ባይን ለዩክሬን እርዳታ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን ያደረግችው ድጋፍ 1 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

በሌላ በኩል ፕሬዝደንት ፑቲን በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው ምዕራባዊያንን ተችተዋል።

ምዕራባዊያን ሩሲያን “ለመከፋፈል” እየሠሩ ነው፤ ሩሲያን ለማጥፋት ሲሉ “የእርስ በርስ ጦርነት ለመቀስቀስ እየጣሩ ነው”፤ ነገር ግን ሩሲያዊያን ለዚህ ሤራ እጅ አይሰጡም ብለዋል።