የኦነግ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዓመት በኋላ ከቤታቸው ውጪ ታዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዓመት በኋላ ከቤታቸው ውጪ መታየታቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።
ቢቢሲ አቶ ዳውድ ዛሬ ረፋድ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ስብሰባ ለመቀመጥ ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምርተው እንደነበር ከታማኝ ምንጮች ተረድቷል።
የሊቀ መንበሩን ከእቁም እስር መለቀቅን ፓርቲያቸውም አረጋግጧል።
የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ሽጉት ገለታ፤ "ታጉረው ከነበሩበት ቤታቸው መውጣት ችለዋል። መቶ በመቶ ተፈተዋል ማለት ባይቻለም ትልቅ ለውጥ ግን አለ። . . . ሰው አያነጋግራቸውም ነበር፣ ከቤት እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም ነበር። ምርጫ ቦርድ ካነጋገራቸው በኋላ ግን ከቁም እስር ተለቀዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ምርጫ ቦርድ ከቀናት በፊት የኦነግ የረጅም ጊዜ ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ከቤታቸው እንዳይወጡ ተከልክለው በቁም እስር ላይ እንደቆዩ ባደረገው ማጣራት ማረጋገጡን ገልጾ ነበር።
ይህም ድርጊት ከሕግ ውጪ መሆኑን በመጥቀስ በሊቀ መንበሩ ላይ የተጣለው የመንቀሳቀስ ገደብ በአፋጣኝ እንዲነሳ ቦርዱ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን እና ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን በደብዳቤ መጠየቁ ይታወሳል።
ከአቶ ዳውድ የቁም እስር በተጨማሪ በርካታ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በእስር ላይ ይገኛሉ።
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ሚካኤል ቦረን እና አብዲ ረጋሳን ጨምሮ ኬነሳ አያና፣ ኮሎኔል ገመቹ አያና፣ ዳዊት አብደታ እና ለሚ ቤኛ በእስር ላይ ይገኛሉ።
የኦነግ ቃል አቀባይ በቴ ኡርጌሳ ደግሞ ከጥቂት ቀናት በፊት ከእስር ቢለቀቁም፤ በእስር ላይ ሳሉ ያጋጠማቸውን የጤና መታወክ ተከትሎ በጤና ተቋም ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።
የፖለቲከኞቹ ጠበቆች ደንበኞቻችን በፍርድ ቤት በነጻ ቢለቀቁም ፖሊስ ነጻ ለማሰናበት ፍቃደኛ አይደለም ሲሉ ከዚህ በፊት ለቢቢሲ ተናግረዋል።















