የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በምን ጉዳይ ላይ ተነጋገሩ?

ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የአሜሪካ ጉዳይ ፈጻሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን

የፎቶው ባለመብት, Min of Foreign Affairi of ETH

የምስሉ መግለጫ, ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የአሜሪካ ጉዳይ ፈጻሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ የአገራቸው ዋነኛ ትኩረት በጦርነት ለደቀቀው የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ መሆኑን ተናገሩ።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ቆይታ ካደረጉ በኋላ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በቀጠናው የጆ ባይደን አስተዳደር ዋነኛ ትኩረት በጦርነት ብዙ መስቅልቅል ላጋጠመው ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ቀን ልዩ መልዕክተኛው ከመጋቢት 12 እስከ መጋቢት 13/2014 ዓ.ም. የቆየ ጉብኝት በኢትዮጵያ እንደሚያደርጉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ሰኞ ዕለት መግለጹ ይታወሳል።

ዴቪድ ሳተርፊልድ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆን፣ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ትኩረቱን በትግራይ አድርጎ ለሌሎች አካባቢዎችም የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ መሆኑን አምባሳደር ሳተረፊልድ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

"ከዚህ በላይ ትልቅ ትኩረት ሊያገኝ የሚችል ጉዳይ የለም. . . የምናደርገውና እያልነው ያለው ይህን ዓላማ [የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ] ማሳካት እና ማስቀጠል ማስቻል ነው" ብለዋል።

አምባሳደር ሳተርፊልድ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በተገናኙበት ወቅት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥታቸው ያልተቋረጠ የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስ ቁርጠኛ መሆኑን ስለመናገራቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ይሁን እንጂ አቶ ደመቀ በህወሓት ታጣቂዎች ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ እክል እየገጠመው መሆኑን ለልዩ መልዕክተኛው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አመልክቷል።

ባለፈው ሳምንት መዳረሻቸውን አፋር ያደረጉ እና ለአፋር ማኅብረሰብ አባላት የተላከ የሰብዓዊ እርዳታ ማለፈ እንዳይችል መከልከሉን ልዩ መልዕክተኛው ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ማለትም መጋቢት 10 እና 11 2014 ዓ.ም. መዳረሻቸውን አፋር ክልል ያደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች የታሰበላቸው ስፍራ ሳይደርሱ አፋር ውስጥ እክል እንደገጠማቸውና ከእነጭነታቸው ወደ ሰመራ መመለሳቸውን ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ከሌሎች የሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን ወደ ትግራይ ልኳቸው የነበሩ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች በህወሓይ ኃይሎች ጥቃት ወደ አፋር ለመመለስ መገደዳቸውን አስታውቋል።

በህወሓት እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተቀስቀሰው ጦርነት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ሰብአዊ እርዳታን ይፈልጋል።

ልዩ መልዕክተኛው ዴቪድ ሳተርፊልድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Min of Foreign Affairi of ETH

የምስሉ መግለጫ, ልዩ መልዕክተኛው ዴቪድ ሳተርፊልድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር

ኤችአር6600 እና ኤስ3199

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት አሜሪካ እያረቀቀች ያለቻቸው ኤችአር6600 እና ኤስ3199 የተባሉት ረቂቅ ሕጎች የሁለቱን አገራት ረዥም እና ታሪካዊ ግነኙነት የሚያንጸባርቁ አይደሉም ስለማለታቸው የውጭ ጉዳይ አስታውቋል።

ረቂቅ ሕጎቹ በኢትዮጵያ ሰላም እና ዴሞክራሲን ከመገንባት ይልቅ ተራ ዜጎችን ስለሚጎዱ የአሜሪካ መንግሥት ረቂቅ ሕጎቹን ውድቅ ያደርጋቸዋል የሚል እምነት አለኝ ሲሉ አቶ ደመቀ ለሳተርፊልድ መናገራቸውን መሥሪያ ቤታቸው ገልጿል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መንግሥታት ላይ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ ለደረሱ በደሎች ተጠያቂ ናቸው በተባሉ ግለሶች ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችሉ ኤችአር6600 እና ኤስ3199 የተባሉ ረቂቅ ሕጎችን አስተዋውቃለች።

እነዚህ ረቂቅ ሕጎች በፕሬዝደንት ባይደን የሚጸድቁ ከሆነ አሜሪካ በደኅንነት፣ በፋይናንስ/በኢንቨስትመንት እና በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ላይ በሁለቱ አገራት እና ግለሰቦች ላይ ማዕቀቦችን ትጥላለች።

የኢትዮጵያ የሰላም ጥረት

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከልዩ መልዕክተኛው ጋር በነበራቸው ውይይት የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት ለማስፈን ስላደረገው ጥረት ተናግረዋል ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግሥታቸው ሰላም ለማስፈን እና መግባባትን ለመፍጠር ፖለቲከኞችን ከእስር መልቀቁን፣ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጠናቀቂያው ጊዜ በፊት ማንሳቱን እንዲሁም ብሔራዊ ውይይት ለማካሄድ የሚደረገውን ጥረት አብራርተዋል።

ዴቪድ ሳተርፊል አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱን ለማረጋገት የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ታደንቃለች እንዲሁም ትረዳል ስለማለታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አንድ ዓመት ከስድስት ወር ያስቆጠረው በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና የአጋር ክልሎች የተስፋፋው ጦርነትን ተከትሎ ልዩ መልዕክተኛ ሰይማ ጉዳዩን ስትከታተል የቆየችው አሜሪካ ተኩስ አቁም እንዲደረግና ግጭቱ በድርድር እንዲቋጭ ስትገፋ ቆይታለች።

ከዚህ ባሻገርም በጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች በተለይም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያነጣጠሩ የጉዞና ምጣኔ ሀብታዊ እርምጃዎችን መውሰዷ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካንን እርምጃ ተገቢነት በመቃወም በተደጋጋሚ ቅሬታውን አሰምቷል።