የኢትዮጵያን የግጭት ማቆም ውሳኔ አሜሪካ እና ዩኬ ተቀባይነት ያለው ነው አሉ

ምዕራባውያን እና የረድኤት ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ግጭት ለማቆም መወሰኑ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ነው አሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሚደርሰው ሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍ በሚል ከሐሙስ መጋቢት 15/2014 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚጸና ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት የማቆም ውሳኔን ይፋ መድረጉን ተከትሎ አዎንታዊ ምላሽ ከሰጡት መካከል የዩናይትድ ኪንግደም እና የአሜሪካ መንግሥታት ይገኙበታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭት ለማቆም መወሰኑ እና የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ ከረድኤት ድርጅቶች ጋር ለመስራት ያሳየው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።
አሜሪካ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ ደግሞ መንግሥት በአስቸኳይ ተግባራዊ የሚሆን ግጭት የማቆም እና ሰብአዊ እርዳታ ያለ ችግር እንዲደርስ ለማድረግ ከረድኤት ድርጅቶች ጋር ለመሥራት ያሳለፈውን ውሳኔን አድንቃለች።
ይህ ውሳኔ ድጋፍ ለሚሹ ኢትዮጵያውያን በፍጥነት ለማቅረብ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው ለአገሪቱ ደኅንነትና ብልጽግና ሁሉን አካታች የሆነ ፖለቲካዊ ሂደት ለማስጀመር መሠረት እንደሚሆንም ጠቅሷል።
ጨምሮም በሁሉም ወገኖች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲቆሙና ከዚህ በፊት ለተፈጸሙ በደሎችና ጭፍጨፋዎች ተጠያቂነት እንዲኖር ጠይቋል።
ይህንን ግጭት የማቆም ውሳኔን በመከተልም ተፋላሚ ወገኖቹ አስፈላጊ የደኅንነት ሁኔታዎችን ማመቻቸትን ጨምሮ በድርድር ላይ ወደ ተመሠረተ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲደርሱ መክሯል።
ዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደውን ግጭት የማቆም እርምጃ አድንቃ አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የዩናይትድ ኪንግደም የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ለሰብዓዊ አቅርቦት ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰነው ውሳኔ አጥብቀን እንደግፋለን ብለዋል።
በተመሳሳይ የአውሮፓ ሕብረትም የኢትዮጵያን ውሳኔ በአዎንታዊ እንደሚቀበለው እና የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያሻቸው አስቸኳይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) አስተዳዳሪ ሳማንታ ፓዎር በአስቸኳይ ተፈጻሚ የሚሆነው ግጭት የማቆም ውሳኔ በበጎ ጎኑ እናየዋለን ብለዋል።
ሳምንታ በትግራይ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ንሑሃን አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውሰዋል።












