የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑት ወገኖች ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ጥሪ አቀረቡ።
ዋና ፀሐፊው ይህንን ጥሪ ያቀረቡት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት አመቺነት ግጭት ለማቆም ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የህወሓት መሪዎች እርምጃው በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆን መስማማታቸውን አስመልከተው ባወጡት መግለጫ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል የሚደርሰው ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍ በሚል ከመጋቢት 15/2014 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሚጸና ግጭት የማቆም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ፣ ህወሓትም በበቂ መጠን እና ተቀባይነት ባለው ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚደርስ ከሆነ ጥሪውን እንደሚቀበልና ተግባራዊ እንሚያደርግ መግለጹ ይታወቃል።
አንቶኒዮ ጉቴሬስ በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉም ወገኖች አሁን የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ በወሰዱት ግጭትን የማቆም አበራታች እርምጃ ላይ በመገንባት "ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም የሚያደርስ አስፈላጊ እርምጃ" እንዲወስዱና ጦርነቱ እንዲያበቃ እድል እንዲፈጥሩ በመግለጫቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃውን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ለሰብአዊነት ሲባል ግጭትን የማቆም ውሳኔው "በቀጣይ ያለ ተጨማሪ ደም መፋሰስ ለግጭቱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል" ተስፋ እንደሚያደርግ ጠቅሷል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ በኋላም የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ግጭት የማቆም ውሳኔን ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች በድርድር ላይ ወደተመሠረተ ዘላቂ ተኩስ አቁም እንዲያደርሱት ጥሪ አቅርቧል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ በመግለጫቸው በኢትዮጵያ ያለው ግጭት አስካሁን "በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ" ክልሎች ውስጥ በሚገኙ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ አስከፊ ስቃይን አስከትሏል ያሉ ሲሆን፣ አሁን የታየው አውንታዊ እርምጃ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በፍጥነት ወደ ሚያሻሽል ተግባር መተርጎም አለበት ብለዋል።
ዋና ፀሐፊው ጨምረውም የባንክ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶችን ጨምሮ በትግራይ ተቋርጠው የሚገኙት ሁሉም የሕዝብ አገልግሎቶች መልሰው እንዲጀመሩ ጠይቀዋል።
ሁሉም ወገኖች በራሳቸው ተነሳሽነት የእርዳታ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች በአፋጣኝ እንዲደርስ እንዲያግዙም ጥሪ አቅርበዋል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ የአፋርና የአማር ክልሎችን ያዳረሰው የእርስ በርስ ጦርነት 16 ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን አድርሷል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከዚህ ውስጥ በትግራይ ክልል ከሚኖረው ሕዝብ 90 በመቶው ሰብአዊ እርዳታን በአስቸኳይ ይፈልጋል።
በጦርነቱ ምክንያት ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ አቅርቦት ከተቋረጠ ወራት በመቆጠራቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች ገልጸዋል።
በዚህም ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከትግራይ ክልል በመውጣት ወደ አጉራባች ክልሎች እየተሰደዱ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።














