ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የመንግሥታቱ ድርጀት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ተወያዩ

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ተነጋገሩ።
ጉቴሬዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት የአገሪቱን ወቅታዊ ጉዳዮችን አንስተው መክረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በድረ-ገፁ እንዳስታወቀው ዋና ፀሐፊውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግጭቱ በተጎዱ አካባቢዎች መደረግ ስላለበት ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም ስለፖለቲካዊ ውይይት አውርተዋል።
የዋና ፀሐፊው እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝርዝር ንግግር ባይገለጽም፤ የሁለቱ መሪዎች የተሰማው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሁኔታ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ነው።
ኮሚሽነሯ በመግለጫቸው ካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት 2021 ኅዳር ወር እስከ የካቲት 2022 ድረስ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን ዳስሰዋል።
ባሽሌት እንዳሉት በተጠቀሰው ወቅት በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል በተከሰተው ግጭት ሳብያ ሰብዓዊ መብትና የደኅንነት ጉዳይ ላሽቀዋል።
ኮሚሽነሯ መሥሪያ ቤታቸው በየጊዜው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሚጠቁም መረጃ እንደሚደርሳቸው አሳውቀዋል።
ሚሼል ባሽሌት እንዳሉት በኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደተፈፀሙ በሚታመኑ ጥቃቶች በትግራይና በአፋር ክልል 304 ሰዎች ሲገደሉ 373 ሰዎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ታኅሣሥ 2021 በኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደተፈፀመ በሚታመን ጥቃት ደግሞ 120 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ 145 ሰዎች ቆስለዋል ይላል የኮሚሽነሯ መግለጫ።
ኮሚሽነሯ አክለው ትግራይ ክልል ውስጥ ማይ ዓይኒ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በደረሰ የአየር ጥቃት 60 ሰዎች ሲገደሉ 169 ቆስለዋል ብለዋል።
ሚሼል በመግለጫቸው በአማራ እና በትግራይ ክልል በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት የፈፀመው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ብቻ ሳይሆን የትግራይ ኃይሎችና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር - ሸኔ ናቸው ብለዋል።
የትግራይ ኃይሎች በአፋር ክልል ኤሬብቲ፣ አባላ፣ በርሃልና መጋሌ በፈፀሙት ጥቃት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ ከሆስፒታሎች በተገኘ መረጃ ደግሞ 844 ሰዎች ቆስለዋል ብለዋል ኮሚሽነሯ።
ሚሼል የትግራይ ኃይሎች አፋር ክልል በፈፀሙት ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥርን እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም ብለዋል።
ኮሚሽነሯ በመግለጫቸው እንደገለጡት በተጠቀሰው ጊዜ የትግራይ ኃይሎች በአማራ ክልል 306 የመድፈር ጥቃቶች ፈፅመዋል።
አብዛኛዎቹ የጥቃቱ ሰለባዎች ሴቶች ሲሆኑ ጥቂት ወንዶችም መደፈር ተፈፅሞባቸዋል ሲሉ አክለዋል።
በተጨማሪ በአፋርና አማራ ክልሎች በርካታ ትምህርት ቤቶችና የሕክምና መስጫ ማዕከላት እንደወደሙ ጠቁመዋል።
የጤና ሚኒስቴር ቢያንስ በአፋርና አማራ ክልሎች ቢያንስ 36 ሆስፒታሎችና 2100 የጤና ማዕከላት እንደወደሙ ገልጧል።
ኮሚሽነሯ፤ የተፈፀሙት ጥቃቶች ዓለም አቀፍ ሕግጋት የሚጥሱ ስለሆኑ የግጭቱ ተሳታፊዎች ከመሰል ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ሚሼል እንዳሉት የሰብዓዊ መብት አያያዙ ከጊዜ ጊዜ እየላሸቀ ሲሆን በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል መግባት የነበረበት እርዳታ ከታኅሣሥ ጀምሮ አልተንቀሳቀሰም።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል 4.6 ሚሊዮን ሰዎች ማለትም ከአምስት ሰዎች አራቱ የምግብ እርዳታ ጠባቂ ሲሆኑ ከግማሽ በላይ ነፍሰ ጡርና ጡት የሚያጠቡ እናቶች አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ እንዳሉ አሳውቋል።
ኮሚሽነሯ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ የመጣው መፈናቀል እንዳሳሰባቸውም በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
በአፋር ክልል የትግራይ ኃይሎች በፈፀሙት ጥቃት 300 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውንም ገልጠዋል።
ኮሚሽነሯ እንዳሉት የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ከ15 ሺህ በላይ ሰዎች ያለአግባብ በመንግሥት ኃይሎች ታሥረዋል፤ አባዛኛዎቹ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች ናቸው።
ሚሼል፤ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳቱን አወድሰው ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ባደረጉት ውይይት አብዛኛዎቹ ታሣሪዎቹ እንደተፈቱ መስማታቸውን ጠቅሰዋል።
ኮሚሽነሯ አክለው መንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ያማከለ ከሚቴ ማቋቋሙን አንስተው አዲስ አበባ የሚገኘው ቢሯቸው ከዚህ ኮሚቴ ጋር አብሮ እየሠራ እንደሆነ ገልጠዋል።
አልፎም የኢትዮጵያ መንግሥት በአፋርና አማራ ክልሎች የተፈፀሙት ጥቃቶች የሚመረምር አካል መላኩን ያስታወሱት ኮሚሽነሯ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ መንግሥት የዚህን ምርመራ ውጤት በቅርቡ ይፋ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ኮሚሽነሯ በመግለጫው በቅርቡ የተቋቋመው የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ነፃና አካታች ውይይት ማካሄድ እንዲችል መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።












