'በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ የምግብ ዋጋ ጣራ እየነካ ነው'

ጥራጥሬ እህል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም አቀፉ ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ ዴቪድ ቢዝሊ የዩክሬን ጦርነት የምግብ ዋጋን እንደሚያንረውና ያላደጉ አገራትን ምጣኔ ሃብት ሊያደቅ እንደሚችል አስጠነቀቁ።

ዩክሬን እና ሩሲያ የምግብ ምርቶችን በገፍ ከሚያመርቱ የዓለማችን አገራት መካከል ናቸው።

ኃላፊው እንደሚሉት ጦርነቱ አንዳንድ አገራትን ወደከፋ ረሃብ ሊገፋቸው ይችላል።

"ምድራችን ላይ ያለው ያለው ከፋ ሁኔታ ወደ ባሰ ሁኔታ አይሸጋገርም ብለን ተስፋ ብናደርግም እነሆ ይሄ ተፈጠረ" ብለዋል ኃላፊው።

ሩሲያና ዩክሬን በአንድ ወቅት የአውሮፓ የዳቦ ቅርጫት ይባሉ ነበር። የምድራችንን ሩብ የስንዴ ምርት አምራች አገራትም ነበሩ።

ይሄ ብቻ አይደለም ዓለማችን ግማሹን የሱፍ አበባ እና ከዚህ ሰብል የሚገኙት ዘይትና ሌሎች ምርቶችን የምታገኘው አሁን በጦርነት አረነቋ ውስጥ ካሉት ሁለቱ አገራት ነው።

ሩሲያ በነዳጇ ዩክሬን ደግሞ በበቆሎ ምርቷ የዓለማችን ትሩፋቶች ናቸው።

የዘርፉ ሙያተኞች ጦርነቱ የጥራጥሬ እህሎችን ዋጋ እንደሚያሻቅበውና የስንዴ ዋጋን እጥፍ ሊያደርገው እንደሚችል ይሰጋሉ።

ከቢቢሲ 'ቢዝነስ ዴይሊ' ጋር ቆይታ የነበራቸው ዴቪድ ቢዝሊ በዓለማችን የረሃብ ስጋት ተደቅኖባቸዋል የሚባሉ ሰዎች ቁጥር ከ80 ሚሊዮን ወደ 276 ሚሊዮን ማሻቀቡን ገልጠዋል።

ሰውዬው ይህ የሆነው የአየር ንብረት ለውጥና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ያወጀችው ጦርነት ሲታከልበት ነው ይላሉ።

ኃላፊው እንደሚሉት አንዳንድ አገራት አሁን ባጋጠመው ቀውስ ሳቢያ የከፋ አደጋ ፊታቸው ተደቅኗል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ እኒህ አገራት ከፍተኛውን ጥራጥሬ የሚያስመጡት ከጥቁር ባሕር አካባቢ በመሆኑ ነው።

"ሊባኖስ ለምሳሌ 50 በመቶ ጥራጥሬ የምታስመጣው ከዩክሬን ነው። የመን፣ ሶሪያ፣ ቱኒዚያ እና ሌሎች በርካታ አገራትን መጥራት እችላለሁ፤ ከዩክሬን በሚያስመጡት እህል ላይ ጥገኛ ናቸው" ይላሉ።

"ነገር ግን አሁን የዳቦ ቅርጫት ከመሆን ወደ ዳቦ ጠባቂነት ስትለወጥ በጣም የሚያስገርም የእውነት መመሰቃቀል ነው።"

"መሬታቸውን እየጠበቁ ነው"

የዓለም አቀፍ ንግድ ባለሙያዋ ዩክሬናዊቷ ጠበቃ ኢቫና ዶሪቼንኮ እንደምትለው ዩክሬን ያሉ አንዳንድ ገበሬዎች መሬታቸውን ጥለው ነፍጥ አንግበው የሩሲያን ጦር እየተዋጉ ነው።

"ቀድሞ ያርሱ የነበሩ እጆች አሁን የጦር መሣሪያ ጨብጠዋል። መሬታቸውን እየጠበቁ ነው። መሬታችንን ከጠላት ካልጠበቁ ኋላ የሚያርሱበት መሬት ያጣሉ" ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።

ጠበቃዋ እንደምትለው ጦርነቱ ሁሉን ነገር በማመሰቃቀሉ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ተበጣጥሷል።

የዩክሬን ጦር ከሩሲያ ወረራ በኋላ ድንበር ላይ ያሉ ሁሉም የንግድ መስመሮች እንዲቋረጡ አድርጓል።

"መርኮቦች መንቀሳቀስ አይችሉም። ጭነት አይጫንባቸውም። ቦታው የጦርነት ቀጣና ሆኗል። በሚያሳዝን ሁኔታ አሁን ከዩክሬን ተጭኖ የሚወጣ ምንም ነገር የለም።"

ኢቫና፤ ይህ ለንግዱ መስክ "ትልቅ ኪሳራ ነው" ትላለች። ከዚያ ሲብስም ለሰብዓዊ እርዳታ ቀውስም ምክንያት መሆኑን ትናገራለች።

ምክንያቱም አሁን ዩክሬን ወደ ደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ እንዲሁም ለዓለም ምግብ ፕሮግራም እህል መላክ አትችልም።

አንዳንድ አገራት ውስጥ ከዩክሬን ጦርነት አስቀድሞ የምግብ ዋጋ መናር ጀምሯል።

ደቡብ አፍሪካዊው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዋንዲሌ ሲህሎቦ አፍሪካ ውስጥ ያሉ ጥራጥሬ የሚያስመጡ አገራት በጦርነቱ ምክንያት ስጋት ላይ ናቸው ይላል።

የደቡብ አፍሪካ የግብርና ንግድ ምክር ቤት ዋና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆነው ዋንዲሌ ምንም እንኳ የምግብ ዋጋ መናር በቅርብ ጊዜ የምናየው ቢሆንም በረዥም ጊዜ የምግብ እህል እጥረት ሊከሰት እንደሚችል ይገምታል።

ትልቁ የማዳበሪያ አምራች የሆነው የኖርዌይ ኬሚካል ኩባንያ ያራ ኢንተርናሽናል በ60 አገራት ምርቱን ያከፋፍላል።

የዚህ ድርጅት ኃላፊ በዚህ ጦርነት ምክንያት የእህል ምርት ስለሚጎዳ "ዓለም አቀፍ የምግብ እጥረት" ይመጣል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።