በአማራ ክልል ባለሥልጣናት ግድያ የተከሰሱ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ አስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Amhara supreme court/fb
ከሁለት ዓመት በፊት፣ ሰኔ 15 2011 ዓ.ም፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በተገደሉበት ክስተት ጥፋተኛ በተባሉት ተከሳሾች ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ።
ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በአማራ ክልል መስተዳደር ጽህፈት ቤት ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት ፕሬዝዳንቱን ዶክተር አምባቸው መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ ባለሥልጣናት መገደላቸው ይታወሳል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነው ከኅዳር 23/2012 ዓ.ም ጀምሮ ጉዳያቸው በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲታይ ከነበሩት ተከሳሾች መካከል ጥፋተኛ በተባሉት 31 ግለሰቦች ላይ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ብይን ሰጥቷል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ ማክስኞ የካቲት 29/2014 ዓ.ም በተከሳሾቹ ላይ ከእድሜ ልክ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ የጽኑ እስር ውሳኔ አሳልፏል።
ቀደም ሲል በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያሳላፈው ችሎቱ የቅጣት ውሳኔውን ከመስጠቱ በፊት በተከሳሾች የቀረበውን የቅጣት ማቅለያ የተመለከተ ሲሆን፣ በዚህም በተለያየ ደረጃ የጥፋት ማቅለያዎችን በመቀበል ብይኑን ሰጥቷል።
በዚህም መሠረት በ28ቱ ተከሳሾች ላይ ከ15 ዓመት እስከ 18 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት ቅጣት ሲበይን፣ ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ በቆዩት በሻምበል መማር ጌትነት፣ በበላይሰው ሰፊነው እና በልቅናው ይኹኔ ላይ ደግሞ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወስኗል።
ቅዳሜ ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ በሆነችው ባሕር ዳር ውስጥ አንዳንዶች መፈንቅለ መንግሥት ነው ባሉት ጥቃት፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባር ከበደ እና የርዕሰ መስተዳደሩ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ መገደላቸው ይታወሳል።
ይህንን ጥቃት መርተዋል የተባሉትና የአማራ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ከክስተቱ ከቀናት በኋላ በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ከዚሁ ክስተት ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ በሻምበል መማር ጌትነት የክስ መዝገብ 55 ግለሰቦች ላይ ክስ ተመስርቶ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ሲመለከት የቆየ ሲሆን ባለፈው ዓመት 20ዎቹን በነጻ እንዲሰናበቱ ወስኖ ነበር።

















