ማርች 8፡ ከደረሰባቸው ጾታዊ ትቃት በኋላ በሁለት እግራቸው ለመቆም የሚታገሉት ሴቶች ምን ይላሉ?

ስንዱ እና አሰለፍ አዲስ አበባን የሚያውቋት በስም ብቻ ነበር።
በተወለዱበት እና ባደጉበት ስለመልከ ብዙዋ አዲስ አበባ በርካታ ነገሮች ሰምተዋል። ለጆሮም ለዓይንም የሚጥም ነገር ብቻ የሚገኝባት፤ ሰርተው የሚለወጡባት፣ ከራስ አልፎ አፈር ገፍተው የሚያድሩ ቤተሰቦቻቸውን ታሪክ የሚቀይሩባት ትልቅ ከተማ እንደሆነች አስበዋል።
እናም በጆሯቸው የገባው የወሬ ጮማ ልባቸውን አሸፈተው። አዲስ አበባ ለመሄድ ቀን ባይቆርጡም፣ አውቶቡስ ባይሳፈሩም ቀድሞ ልባቸው ሸፈተ።
በዚህ መካከል የአዲስ አበባን ነገር ለእኔ ተዉት የሚል የቅርብ ሰው ተገኘ።
የቤት አያያዝ ባለሙያዋ ስንዱ
ስንዱ በአሁን ጊዜ በቤት አያያዝ ሙያ ሰልጥና ተቀጥራ እየሰራች ነው።
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የነበረውን ታሪኳን መለስ ብላ ስታስታውሰው ግን ዛሬ ያለችበት ስፍራ ራሷን ቆማ የምታገኘው አይመስላትም ነበር።
በሕይወቷ ውስጥ ባይተዋር ወደ ሆነችነበት አዲስ አበባ መምጣቷ የሕይወቷን ታሪክ በአዲስ መልክ ጻፈው።
ስንዱ ጎዳኸኝ፣ ባለትዳር እና የአንድ ልጅ እናት ነበረች።
የአባቷ ልጅ፣ ወንድሟ ወደ አዲስ አበባ ብትሄድ የተሻለ ኑሮ የሚያኖራት ሥራ ሰርታ ጥሪት መቋጠር እንደምትችል ሲነግራት ልጇን ለቤተሰቦቿ ጥላ፣ ወንድሟን አምና ብዙ ወደ ተወራላት አዲስ አበባ በአውቶቡስ ተሳፈረች።
የሁለት መቶ ብር ትራንስፖርት ወንድሟ ሲልክላት፣ የሁለት ዓመት ልጇን ለእናቷ ጥላ ወደ አዲስ አበባ አቀናች።
አዲስ አበባ ስትደርስ ልጅ የመንከባከብ ሥራ በሩን ከፍቶ ተቀበላት።
ወንድሟ ሥራ ካስቀጠራት በኋላ የወር ደሞዟን በየወሩ እየተቀበለ ያስቀምጥላት ጀመር።
ስንዱ የምታገኘውን ደመወዝ አጠራቅማ ልጇን እና ቤተሰቦቿን ለመለወጥ እያሰበች ሳለ አንድ ክፉ ቀን ክፉ አጋጣሚ ላይ ጣላት።
የቤቱ ባለቤት፣ አባወራ ደፈራት።
ይኼኔ ስንዱ የተቀጠረችበትን ቤት ለቅቃ ሌላ አሰሪ ጋርተቀጠረች።
ነፍሰጡር መሆኗን እንዳወቀች ለአዲስ አሰሪዎቿ ያሳወቀችው ስንዱ፣ በሥራዋ እንድትቀጥል ፈቃደኛ አልሆኑም።
ወንድሟ ጋር ታስቀምተው የነበረው ደሞዟ ሁለት ሺህ ብር መሆኑን የምታስታውሰው ስንዱ፣ እንዲሰጣት ብትጠይቅም ፈቃደኛ ሊሆን አልቻለችም።
አማላጅ ብትልክም አሻፈረኝ አለ።
ከዚህ በኋላ የሰው እጅ ማየቷን ትናገራለች።
እፀድቅ ያለች አንዲት ሴት ገንዘብ ሰጥታት ተከራይታ መኖር ጀመረች።
መውለጃዋ ደርሶ ምጧ ሲመጣ በቀዶ ሕክምና ወለደች። በፊት አንድ ራሷን ለማኖር ያልከበዳት ስንዱ፣ አሁን ከጨቅላ ልጇ ጋር ሆና ኑሮን መግፋት ፈተና ሆነባት።

የአስራ አምስት ቀን አራስ ሆና ሳለች ወደ ሴቶች ማረፊያ እንድትገባ ሰዎች ረዷት።
ወደ ሴቶች ማረፊያ ከመጣች በኋላ የደፈራትን ግለሰብ ከስሳ ለልጇ ማሳደጊያ እንዲቆርጥላት ማስደረግ ችላ ነበር።
ከሴቶች ማረፊያ ከወጣች በኋላ ግን የተወሰኑ ወራት ወርሃዊ ተቆራጩን ካደረገ በኋላ አቋረጠባት። እርሷም አድራሻውን አግኝታ ተከታትላ ማስቀጠል አልቻለችም።
በሴቶች ማረፊያ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎች ማግኘቷን የምትናገረው ስንዱ ከወጣች በኋላ በሰለጠነችበት ሙያ ትሰራ ነበር።
በአሁን ጊዜ ደግሞ በቤት አያያዝ ሙያ ሰልጥና ተቀጥራ እየሰራች መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ገልጻለች።
'ነጋዴ ብቻ ሳልሆን አስተማሪም ነኝ'
አሰለፍ (ለዚህ ታሪክ ሲባል ስሟ የተቀየረ) ሻይ ቡና እየሰራሁ ነው የምኖረው ትላለች።
በተወለደችበት የገጠር መንደር ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ብትፈልግም አካል ጉዳተኛ ስለሆነች ብቻ ከተወሰኑ ክፍሎች በላይ ማንም ሊያስቀጥላት አልፈለገም።
"ቤታቸውን እንድጠብቅ፣ እንዳጸዳ ብቻ ነበር የሚፈልጉት" ትላለች።
በውስጤ ብዙ አላማ ነበረኝ፣ እችላለሁ የሚል ጠንካራ ተስፋ በውስጤ ነበር የምትለው አሰለፍ ብዙ ወደ ሚወራላት አዲስ አበባ ጠፍታ መጣች።
የአካል ጉዳተኛዋ አሰለፍ፣ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣች መኖሪያዋ የሆነው ጎዳና ነበር።
ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ የ14 ዓመት ልጅ እንደነበረች የምትናገረው አሰለፍ፣ ጎዳና ላይ አንድ ዓመት ያህል ከቆየች በኋላ አንድ ለሊት ተደፈረች።
በዚያ የተነሳም ራሷን ስታ ያገኟት የከተማዋ ፖሊሶች አፋፍሰው ወደ ሆስፒታል ወሰዷት።
በሕክምና ተቋም ውስጥ ሕክምና ካገኘች በኋላ፣ ከሴቶች እና ከህጻናት ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር ወደ ሴቶች ማረፊያ እንድትገባ መደረጓን ታስታውሳለች።
ፖሊሶች ደፋሪዋን ለማግኘት ክትትል ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸውም።
ከጥቃቱ በኋላ በተደረገላት የኤችይቪ እና እርግዛና ምርመራ ነፍሰጡር መሆኗን አወቀች።
በሴቶች ማረፊያ ውስጥ ከሌሎች በተለየ ለሁለት ዓመት ያህል እንደቆየች የምትናገረው አሰለፍ፣ እስክትወልድ ድረስም ሆነ ከወለደች በኋላ በርካታ ድጋፎችን ማግኘቷን ገልጻለች።
ጎዳና እስክወጣ ድረስ ሁሉም የሚለኝ አትችይም ነበር የምትለው አሰለፍ፣ በሴቶች ማረፊያ ውስጥ ደግሞ እንደምችል ራሴን አይቼበታለሁ ትላለች።
ከዚያ በተረፈ ደግሞ የንግድ ክህሎት የምግብ ሥራ ሥልጠና እና ሌሎች ሥልጠናዎችን በመውሰድ ራሷን ብቁ ማድረጓን ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, Zelalem Abera (AWSAD)
ከዚያ የማረፊያ ማዕከል ቆይታዋን አጠናቅቃ ከወጣች በኋላም ንግድ ላይ ተሰማራች።
መጀመሪያ ሶፍት ጎዳና ላይ ነበር የምሸጠው፣ "አሁን የሴቶች ማረፊያ ኮንቴይነር ሰጥቶኝ ሻይ እና ቡና እነግዳለሁ" ትላለች።
እስካሁን በርካታ ችግሮችን አልፌያለሁ የምትለው አሰለፍ፣ "ከአሁን በኋላ ያሰብኩትን ለማሳካት የሚያግደኝ የለም" በማለት በራሷ ያላትን መተማመን ትናገራለች።
አካል ጉዳተኛ ሆና ጎዳና መኖር፣ ከዚያም የመደፈር አደጋ ደርሶብኝ ከዚህ ሁሉ ራሴን አውጥቼ፣ በሁለት እግሬ መቆም ከቻልኩ ከራሴ አልፌ ለሌሎች አርዓያ እንደምሆን ሁሌም እምነት አለኝ ስትል ታክላለች።
'ማለዳ ወደ ሥራ ስወጣ፣ ነጋዴ ብቻ ሳልሆን አስተማሪም ነኝ ብዬ ነው የማስበው' ያለችው አሰለፍ 'ከቤቴ የምወጣው ሁለት ዓይነት ሥራ ለመስራት ነው። ራሴን ማሸነፍ እና ማስተማር' ስትል ከደረሰባት መደፈር እንዲሁም ከአካል ጉዳተኝነቷ ጋር ታግላ ራሷን መቻሏ ሌሎችን እንደሚያስተምር ትገልጻለች።
አሰለፍ ወደፊት ንግዷን አስፋፍታ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ቀጥራ ማሰራት ትፈልጋለች።
የሴቶች ማረፊያ
የቀድሞው ፆታዊ ጥቃት ተከላካይ ማኅበር የአሁኑ የሴቶች ማረፊያ ልማት ማኅበር በደረሰባቸው ጥቃት የተጎዱ እና ከጎናቸው የሚቆም አካል ያጡ በርካታ ሴቶችን ለመደገፍ ጥረት ያደርጋል።
ይህ ማኅበር ለተደፈሩ ሴቶች የሕግ ድጋፍና የሙያ ሥልጠናን በመስጠት ከ18 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
የሴቶች ማረፊያ ልማት ማኅበር ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ ከ6000 በላይ ለሚሆኑ ሴቶች ድጋፍ መስጠቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በአዲስ አበባ ከ18 ዓመት በፊት የተመሰረተው ማኅበሩ በአዳማ እና ሐዋሳ ሁለት ሁለት ማረፊያዎች፣ በደሴ፣ በሰመራ ከፍቶ የተለያዩ ፆታዊ ትቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ይደግፋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተለያዩ ጥቃቶች ያጋጠማቸው ሴቶችን ለመደገፍም በወልድያ ማረፊያ በመክፈት እየሰራ መሆኑን በድርጅቱ የማረፊያ አስተባባሪ የሆነችው ኑንያት ጎሳዬ ለቢቢሲ ገልጻለች።
ኑንያት ወደ ማኅበራቸው ጥቃት ደርሶባቸው የሚመጡ ሴቶች እንደ የፍላጎታቸው የተለያዩ የክህሎት ሥልጠናቸውን እንደሚያገኙ ትናገራለች።
ከዚህ በተጨማሪ ማኅበሩ የግንዛቤ ማስጨበጥ እና የድጋፍ አገልግሎት፣ የሥራ ፈጠራ እና ዕድል ማመቻቸት፣ የሥነልቦና እና የሕክምና ድጋፍ ይሰጣል።

















