የደረሰባቸውን ጥቃት በመንገድ ላይ የሚጽፉት የኬንያ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, PLAN International
በአፍሪካ ዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች በጣም ትልቅ ከሚባሉት አንዱ የሆነው በኬንያ መንደር በሚገኘው 'ኪቤራ' መንደር የሚኖሩ ሴቶች ወንዶች ያደረሱባቸውን ጥቃቶች በመንገዶች ላይ እየጻፉ ነው።
ማስጠንቀቂያ: አንዳንድ አንባቢዎች በዚህ ጽሁፍ ያሉ ቃላት ሊያስደነግጧቸው ይችላሉ
ዙቤይዳ ዩሱፍ በኬንያዋ ዋና ከተማ በሚገኘው ኪቤራ ሙሉ ህይወቷን ያሳለፈች ሲሆን በሴትነቷ የሚደርስ ጥቃትና መዋረድ ሁሌም አብረዋት እንዳሉ ትገልጻለች።
''ወንዶች ሁሌም በጣም ወፍራም ነሽ፤ እናትሽ ስጋ ቤት ነው እንዴ የምትሰራው? መቀመጫሽን እና ጡቶችሽን ፈጣሪ ከምንድነው ሰራቸው? በጣም ትልቅ ናቸው'' እንደሚሏት ትገልጻለች።
የ 22 ዓመቷ ዙቤይዳ በኪቤራ መንደር መንገድ ላይ ለአንዲት ሴት ብቻዋን መራመድ በጣም አስፈሪ ነው ብላለች።
ከጊዜ ብዛት ዙቤይዳ ስትሰደብ ዝም ብሎ ማለፍን የምትቃወም ሲሆን በኪቤራ የሚገኙ ሴቶችም መፍራት እንዲያቆሙና ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በማበረታታት ላይ ትገኛለች።
ቾክና ማርከሮችን በመጠቀም 'ቾክ ባክ' የሚል ዘመቻ የጀመረች ሲሆን ዙቤይዳ እና መሰል ሴቶች በሴትነታቸው የደረሱባቸውን መዋረዶችና ጾታዊ ጥቃቶች በመንገድ ላይ እየጻፉ ነው።
ይህ ተግባርም ሰዎች ስለጉዳዩ እንዲወያዩበትና ሴቶች በነጻነት ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲጀምሩ ያደርጋል ብለው ያስባሉ።
''አሁን አሁን ወንዶች ስድብና መሰል ነገሮች ሲናገሩኝ ቆም ብዬ እጋፈጣቸዋለሁ፤ ለምን እንደሚሰድቡኝም እጠይቃቸዋለው። ነገር ግን ለታዳጊ ሴቶች ይሄ በጣም አስፈሪ ነገር ሊሆን ይችላል።''
''ለዚህም ነውእንደዚህ አይነት ዘመቻዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑት። ወንዶች እንዲህ አይነት ነገር ሲናገሩ ትክክል እንዳልሆነና መብትን የሚጋፋ መሆኑን ልናሳውቃቸው ይገባል።'' ብላለች።
''ለአካሌ ክብር ይኑራችሁ" ይላል በአንድ ጥግ በኩል የተጻፈ መልእክት። በስዋሂሊ የተፃፉ ሌሎች መልእክቶች ግን ሴቶቹ የተባሉዋቸውን ነገሮች ሲሆኑ በጣም አፀያፊና አስደንጋጭም ናቸው።

"ቹራ ሂ" የሚለው ሌላኛው ጽሁፍ ይታያል። በስዋሂሊ እንቁራሪት ማለት ሲሆን በወጣቶች ዘንድ ግን ሌላ ትርጉምም አለው፤ 'ሴተኛ አዳሪ' እንደማለት ነው።
ካሮሊን ምዊካሊ የ 20 ዓመት ወጣት ነች፤ በኪቤራ ተወልዳ ሲሆን ያደገችው ወንዶቹ የሚናገሩት ነገር አንዳንድ ጊዜ ለቀናት ከጭንቅላቷ እንደማይጠፋና በጣም እንደሚረብሻት ገልጻለች።
'' በእነዚህ መንገዶች ላይ የሆነ ወንድ መጥፎ ነገር ሳይናገረኝ አልፌ አላውቅም። አንዳንድ ጊዜ ከእንስሳት ጋር ሁሉ ሊያወዳድሩን ይችላሉ።"
'' በራስ መተማነኔን በጣም ነው የሚጎዳው። ብቻዬን ቁጭ ብዬ ሳስበው ግራ ይገባኛል። ይህን ያህል የማልረባና የማልጠቅም ሰው ነኝ ግን? ብዬ እራሴን እጠይቃለሁ'' ብላለች።
በያዝነው ዓመት ፕላን ኢንተርናሽናል የተባለው የተራድኦ ድርጀት ባወጣው መረጃ መሰረት የመንገድ ላይ ጥቃት ከደረሰባቸው 10 ሴቶች አንዷም እንኳን ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዳላደረገች ያሳያል።
ይህም የሚሆነው ሴቶቹ ወደ ሃላፊዎች ቢሄዱ ምን ሊያደርጉላቸው እንደሚችሉ እርግጠኛ ስላልሆኑ እንደሆነ መረጃው ይጠቁማል። ሌላው ቀርቶ እንደዚህ አይነት ትንኮሳና ጥቃቶች ወንጀል መሆናቸውን እንኳን የሚያውቁት በጣም ጥቂት ናቸው።
ዙቤይዳ ዩሱፍና ጓደኞቿ ያጋጠሟቸውን ስድቦችና ጥቃቶች በመንገዶች ላይ መጻፍ መጀመራቸው ደግሞ በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች እየተቀየሩ እንደሚመጡና ሀሳባቸውን ለመግለጽ የሚፈሩ ሴቶች ደግሞ ድፍረት እንደሚሰጣቸው ታምኖበታል።













