ሳዑዲ ምግብ ቤቶች በጾታ የተለየ መግቢያ በሮችን መጠቀም የለባቸውም አለች

በሳዑዲ በምግብ ቤቶች ሴቶችና ወንዶች አንድ በር እንዳይጠቀሙ በሚያግደው ሕግ ምክንያት ወንዶችና ሴቶች በማክዶናልድ ለየብቻቸው ሲገበያዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሳዑዲ በምግብ ቤቶች ሴቶችና ወንዶች አንድ በር እንዳይጠቀሙ በሚያግደው ሕግ ምክንያት ወንዶችና ሴቶች በማክዶናልድ ለየብቻቸው ሲገበያዩ

የሳዑዲ መንግሥት ከአሁን በኋላ በምግብ ቤቶች ውስጥ ወንዶችና ሴቶች የተለያየ መግቢያ እንዲጠቀሙ የሚያስገድደውን ሕግ ማስቀረቱን አስታወቀ።

ከዚህ በፊት በምግብ ቤቶች ውስጥ ለሴቶችና ለቤተሰቦች አንድ በር፣ ለወንዶች ደግሞ ለብቻቸው ሌላ በር ማዘጋጀት የግድ ነበር።

ይህ ዕገዳ በበርካታ ምግብ ቤቶች፣ ካፌዎች፣ እንዲሁም ሌሎች የሕዝብ መሰብሰቢያ ሥፍራዎች ከአሁን በኋላ ተግባራዊ አይሆንም ተብሏል።

በሳዑዲ አረቢያ የተለያዩ ለውጦች እየተካሄዱ ቢሆንም የተቃውሞ ድምጻቸውን የሚያሰሙ ዜጎችንም ማፈኑን ቀጥሏል ብለው የሞሞግቱ የመብት ተሟጋቾች አሉ።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የሳዑዲ ሴት ያለ ወንድ ፈቃድ ወይም አጃቢነት ከሀገር ውጪ መሄድ እንደምትችል ንጉሡ ባስተላለፉት ትዕዛዝ አስታውቀው ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2018 ደግሞ በሴት አሽከርካሪዎች ላይ ለአስርታት ተጥሎ የነበረው የማሽከርከር እገዳ መነሳቱ ይታወሳል። አሁንም ግን የመብት ተሟጋቾች በርካታ ሴት አግላይ የሆኑ ሕጎች እንዳሉ መሆናቸውን በማንሳት የተቃውሞ ድምጻቸውን ያሰማሉ።

መንግሥት ይህንን ለውጥ እያካሄደ ባለበት ወቅት እንኳ በርካታ የሴት መብት ተሟጋቾች በእስር ላይ እንደሚገኙ አክለው ተናግረዋል።

እሁድ እለት የሳዑዲ ከተሞች ሚኒስትር ምግብ ቤቶች በጾታ የተለየ መግቢያ በሮችን መጠቀም እንደማይገባቸው ተናግረዋል። ይህን ውሳኔ የንግድ ተቋማቱ ራሳቸው እንዲወስኑ ተትቷል ሲሉም አክለዋል።

መሐመድ ቢን ሳልማን በ 2017 የልዑሉነቱን ዘውድ ከደፉ በኋላ እጅግ ወግ አጥባቂ የሆነውን የሳዑዲ አረቢያ ማህበረሰብ ክፍት ለማድረግ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ ናቸው።

እያደረጉ ያሉት ለውጥ ከበርካታ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አድናቆትን ቢያገኝም አሁንም ግን ጭቆና እንዳለ የሚገልፁ አልጠፉም።

እ.ኤ.አ. በ2018 ቱርክ በሚገኘው የሳዑዲ ኢምባሲ ውስጥ የተገደለው ጋዜጠኛ ጃማል ኻሾግጂ ጉዳይ የዓለም አቀፍ መንግሥታት በአንድነት ያወገዙት ተግባር ሆኖ ይጠቀሳል።

ጃማል ኻሾግጂ የሳዑዲ መንግሥትን የሚተቹ ጽሑፎችን በመጻፍ ይታወቅ ነበር።