ዓለም ለነዳጅ እና ለጋዝ ፍላጎቱ ሩሲያ ላይ ምን ያህል ጥገኛ ነው?

ነዳጅ የሚቀዳ መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና (ዩኬ) የአውሮፓ ሕብረት ከዚህ በኋላ ከሩሲያ ነዳጅ አናስገባም ብለዋል።

ይህ የሆነው ሩሲያ የነዳጅ ማዕቀብ ከተጣለብኝ ለአወሮፓ አገራት የምሸጠውን የጋዝ አቅርቦት እገታለሁ ብላ ከዛተች በኋላ ነው።

ለመሆኑ ሩሲያ ላይ የተጣሉት የነዳጅና ጋዝ ማዕቀቦች የትኞቹ ናቸው?

ዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ በሙሉ ነዳጅ የሚባል ነገር ከሩሲያ አላስመጣም ብላለች። ጋዝና የከሰል ምርቶችም ከሞስኮ ምድር ወደ አሜሪካ እንዳይላክ ዕግድ ጥላለች።

ዩኬ ከሩሲያ ገዝታ ያከማቸችው ነዳጅ በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ ያልቃል።

የአውሮፓ ሕብረት ደግሞ ከሩሲያ የሚያስመጣውን ነዳጅ በሁለት ሦስተኛ ለመቀነስ ቆርጧል።

የዩኬ መንግሥት እንደሚለው ከሩሲያ ተገዝቶ የተከማቸው ነዳጅ ሌላ አቅራቢ እስኪያገኙ ድረስ የሚያዘልቅ ነው።

የሩሲያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሳንደር ኖቫክ ከሩሲያ ነዳጅ አናስገባም ማለት "ወደከፋ መከራና የዓለም አቀፍ የንግድ ውጥንቅጥ ይከተናል" ብለዋል።

የነዳጅና የጋዝ ዋጋ ከወዲሁ በበርካታ አገራት እየናረ ይገኛል። ሩሲያ ነዳጅ ወደ ውጭ አልክም የምትል ከሆነ ደግሞ ሁኔታው መባባሱ አይቀሬ ነው።

ሩሲያ ምን ያህል የነዳጅ ክምችት አላት?

ሩሲያ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዑዲ አረቢያ በመቀጠል በዓለማች ሦስተኛዋ ትልቅ የነዳጅ አምራች አገር ናት።

በየቀኑ ቢያንስ አምስት ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ወደ ሌሎች አገራት ትልካለች። ከዚህ ውስጥ ግማሹ የሚጓዘው ወደ አውሮፓ አገራት ነው።

አሜሪካ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር ሩሲያ ላይ እምብዛም ጥገኛ አይደለችም። ዩኤስ ከውጭ ከምታስገባው ነዳጅ 3 በመቶ ብቻ ነው ከሩሲያ የሚመጣው።

ወደ ምዕከላዊና ምሥራቃዊ አውሮፓ የሩሲያ ጋዝ የሚተላለፍበት መስመር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ወደ ምዕከላዊና ምሥራቃዊ አውሮፓ የሩሲያ ጋዝ የሚተላለፍበት መስመር

አማራጭ የነዳጅ አቅርቦቶችስ?

ተንታኞች ለነዳጅ አማራጭ አቅራቢዎችን ማግኘት ይቀላል፣ ለጋዝ ግን በጣም ከባድ ነው ይላሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ የነዳጅ ምርቷን እንድታጧጡፍ ሳዑዲ አረቢያን እየጎተጎተች ትገኛለች።

ሳዑዲ አረቢያ ኦፔክ ከተሰኘው የነዳጅ አምራች አገራት ማኅበር ቁጥር አንድ አምራች ስትሆን በየዓመቱ ከሚደረገው የነዳጅ ንግድ 60 በመቶውን ድርሻ ትይዛለች።

ሩሲያ የኦፔክ አባል አይደለችም። ነገር ግን ከማኅበሩ ጋር ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ እየሠራች ትገኛለች።

አሜሪካ፤ ቬንዝዌላ ላይ ጥላ የነበረውን ማዕቀብ ቀለል ለማድረግ እያሰበች ነው። ቬንዝዌላ በአንድ ወቅት የአሜሪካ ቁጥር አንድ ነዳጅ አቅራቢ ነበረች። አሁን ግን ብዙዉን ምርቷን ወደ ቻይና ነው የምትልከው።

የአውሮፓ ገራት ምን ይሆናሉ?

ሩሲያ ምርቷን ለአውሮፓ አገራት የማትሰጥ ከሆነ ከወዲሁ የናረው የነዳጅ ዋጋ ጣራ ይነካል።

የአውሮፓ ሕብረት ከውጭ ከሚያስመጣው ነዳጅ 40 በመቶው ከሩሲያ የሚመጣ ነው።

ይህ የነዳጅ አቅርቦት ከተቋረጠ ጣልያንና ጀርመን ነዳጅ አልባ ይሆናሉ።

አውሮፓ ፊቷን ወደ ካታር ልታዞር ትችላለች። አልጄሪያና ናይጄሪያም ሌሎች አቅራቢዎች ናቸው። ነገር ግን እኒህ አገራት ምርታቸውን ለማሳደግ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከሩሲያ የምታስገባው የነዳጅ ምርት ብዙ አይደለም። ከአጠቃላዩ 5 በመቶ ቢሸፍን ነው።

ለሩሲያ ነዳጅ አማራጭ ማግኘት እንዲሁ ቀለል ተደርጎ የሚታይ አይደለም።

"ጋዝን መተካት ቀላል ነገር አይደለም። እኛ የሩሲያን ጋዝ ወደ አውሮፓ የሚያስተላልፍ ቱቦ አለን" ይላሉ የኢነርጂ ፖሊሲ ተመራማሪው ቤን ማክዊሊያምስ።

የሩሲያ ጋዝ በማዕከላዊና ምሥራቅ አውሮፓ አድርጎ ለሕብረቱ አባላት በቱቦ ይከፋፈላል።

የአውሮፓ ሕብረት ወደ ሌሎች የኢነርጂ አማራጮች ፊቱን ሊያዞር ቢችልም ፈጣንም ቀላልም አይሆንለትም።

ሕብረቱ በፈረንጆቹ 2030 ከሩሲያ የነዳጅ ምርቶች ጥገኝነት ለመላቀቅ ዕቅድ ይዟል።

የጦርነቱ ትሩፋት ለማነው?

በዚህ ጦርነት ምክንያት በጄሪካን ቀድቶ የሚጠቀመው ሰው ይጎዳል።

ዩናይት ኪንግደም ውስጥ ብቻ አንድ ቤተሰብ ለኃይል አቅርቦት የሚከፍለው ገንዘብ ከ700 ፓውንድ ወደ 2 ሺህ ሊያድግ ይችላል።

አሜሪካ ውስጥ የፔትሮል ዋጋ በ16 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጨምሯል።

ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ገፈት ቀማሹ በችርቻሮ ገዝቶ የሚጠቀመው እንደሆነ አያጠራጥርም።