አሜሪካ ሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ምርቷን እንድትጨምር ልትጠይቅ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ወዳጇ ሳዑዲ አረቢያ የነዳጅ ዘይት ምርቷን በከፍተኛ መጠን እንድትጨምር ለማድረግ የማግባባት ጥረት ልታደርግ መሆኗ ተዘገበ።
የአሜሪካ መንግሥት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን ወደ መካከለኛ ምሥራቋ ግዙፍ የነዳጅ ዘይት አምራች አገር ሳዑዲ በመላክ አስካሁን እያመረተችው ያለውን የነዳጅ ዘይት መጠን ከፍ እንድታደርግ እንዲጠይቁ ለማድረግ እያሰበ መሆኑ ተዘግቧል።
'አክሲዮስ' የተባለው የአሜሪካ የፖለቲካ ጉዳዮች ዜና ተቋም እንደዘገበው፣ የባይደን አስተዳደር ሩሲያ በዩክሬን ላይ ከፈጸመችው ወረራ ጋር ተያይዞ ለተከሰተው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዘይት አቅርቦት ቀውስ መፍትሄ ለመፈለግ ጥረት እያደረገ ነው።
ነገር ግን የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ እንዲህ አይነት ጉዞ ፕሬዝዳንቱ ስለማድረጋቸው የተገለጸ ነገር የለም በማለት "የተባለው ነገር ገና ጊዜው ያለደረሰ ግምት ነው" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ እና የቬንዙዌላ ባለሥልጣናት በቬንዙዌላ ላይ የተጣለውን የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ማዕቀብን በማላለት ላይ መወያየታቸወ ተዘግቧል።
በርካታ የአሜሪካ ምክር ቤት አባላትም በቬንዙዌላ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ቢነሳ ከዚያ የሚገኘው የነዳጅ ዘይት ምርት ከሩሲያ የሚገኘውን ለመተካት ያስችላል ማለታቸውን ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ ወደ አገሯ ከምታስገባው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት እና የነዳጅ ዘይት ምርቶች ውስጥ 10 በመቶ የሚሆነውን የምታገኘው ከሩሲያ ነው።
እሁድ ዕለት የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት ናንሲ ፔሎሲ ባወጡት መግለጫ ላይ፣ የምክር ቤቱ አባላት ከሩሲያ ወደ አሜሪካ የሚገቡትን ነዳጅና የነዳጅ ምርቶችን ሙሉ ለሙሉ ማገድን ጨምሮ ሩሲያን ለመነጠል "ጠንካራ ሕግ ለማውጣት እየተዘጋጁ ነው" ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት የነዳጅ ዋጋ ከፈረንጆቹ 2008 ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ጭማሪ አሳይቷል፣ ከሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ የዓለምን ምጣኔ ሀብት ያናጋዋል ተብሎ ተሰግቷል።
በአሁኑ ጊዜ የአንድ በርሜል የነዳጅ ዋጋ ወደ 139 ዶላር የናረ ሲሆን ይህም ከ14 ዓመታት ወዲህ ከፍተኛው እንደሆነ ተገልጿል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመቸው ወረራ ምክንያት ከሩሲያ ምትገዛውን ነዳጅና የነዳጅ ምርት ለማቆም እንዳሰበች የተነገረ ሲሆን፣ የሚፈጠረውን የአቅርቦት ክፍተት ለማካካስ ሌሎች አምራች አገራት የነዳጅ ምርታቸውን እንዲጨምሩ ለማድረግ ጥረት እያደረገች ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሩሲያ ዩክሬንን መውረር ተከትሎ የነዳጅ ዘይት ገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ አለመረጋጋት ተከስቷል።
ትናንት እሑድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አስተዳደራቸው ከአጋር አገሮች ጋር በሩሲያ ነዳጅ ላይ እቀባ ለማድረግ ንግግር ላይ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ይህ የሩሲያ ወረራ ከተጀመረ ወዲህ የነዳጅ ገበያ መለኪያ የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በ20 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በአሜሪካም የነዳጅ ዘይት ዋጋ በ11 ከመቶ መጨመሩንም የአሜሪካ አውቶሞቢል ማኅበር አስታውቋል።
















