ኢትዮጵያ፡ "ሴቶች በሚጥል በሽታ ሲወድቁ፣ ወንዶቹ ጠብቀው ይደፍሯቸዋል"

በሚጥል በሽታ የወደቀች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Tunatura

የሚጥል ሕመም የሚከሰተው ለምንድነው?

አጭሩ መልስ፡ በአንጎል ኤሌክትሪካዊ ንዝረት ጊዜያዊ መረበሽ ሲያጋጥም ነው፡፡

ይህን የሚለው ግን ሳይንሱ ነው፡፡ ማኅበረሰባችን የሚለው ሌላ ነው፡፡ የችግሩ ሥር መሠረትም ይኸው ነው፡፡

በጎጂ ባሕልና በአጉል እምነት የተተበተበ ማኅበረሰብ የሚጥል ሕመምን "መቅሰፍት" ይለዋል፡፡

"ኢፕለፕሲ" ለብዙዎች እርግማን ነው፡፡ ሸይጣን-ጂኒ ነው፡፡ እርኩስ መንፈስ ነው፡፡

ወ/ሮ እናት እውነቱ በእንግሊዝ ነዋሪ ናት፡፡ ይህን አመለካከት ለመጋፈጥ ‹ኬር ኢፕለፕሲ ኢትዮጵያን› መሥርታለች።

ይህን ማኅበር ለመመሥረት ያበቃት አጋጣሚ ብቻውን ይህ ሐተታ ሊያነሳቸው ያሰባቸውን ገሚስ አንኳር ጥያቄዎች ስለሚመልስ እሱን እናስቀድም፡፡

"ለ30 ዓመታት በሚጥል ሕመም መሰቃየት"

"ለ30 ዓመታት በሚጥል ሕመም ጋር በመኖር ብዙ የሕይወት ከፍታና ዝቅታ ውስጥ አልፊያለሁ፡፡

ከ18 ዓመቴ ነው የጀመረኝ፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ነበርኩኝ፡፡

ብዙ አካል ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ ልንገርህ አይደል? ከሕመሙ በላይ የሰው አመለካከት ያማል፡፡

ሰዎች አእምሮን የሚያስጨንቅ ነገር ይናገሩኛል፤ የሚያሳዩኝ ፊት ይረብሸኛል፡፡

እንግሊዝ ከሄድኩ በኋላ ግን ይህ ነገር ተለወጠ፡፡

እዚህ እንግሊዝ የሚጥል ሕመም በቃ አንድ ተራ በሽታ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡

አንጎል ውስጥ ያለ የነርቭ መዛባት ችግር ነው፣ አለቀ፡፡

በእንግሊዝ አገር የሚጥል በሽታ እርግማን አይደለም፡፡ በቃ ምን ልበልህ፣ ልክ እንደ ስኳር ወይም ደም ግፊት ነው የሚታየው፡፡

በዚያ ላይ ሕክምናም መድኃኒትም እንደልብ ነው፡፡ ምን ዋጋ አለው፡፡ እኔ ያገኘሁትን ዕድል የአገሬ ሰዎች አላገኙም፡፡ ይህ ነገር ይጎረብጠኝ ነበር፡፡

"ከሒልተን ሆቴል ደጅ ላይ ያየሁት ነገር"

ከዚያ ምን ሆነ መሰለህ?

የሆነ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ፣ ከጓደኞቼ ጋር ሒልተን ሻይ ጠጥተን ወደ ቤተ መንግሥት አቅጣጫ አቀበቱን በእግር ስንወጣ፣ አንድ ሰው በሚጥል ሕመም ወድቆ ሲሰቃይ ደረስን፡፡

እኔ ሰውዬውን ልረዳው ጎንበስ ስል ጓደኞቼ ጮኹ፡፡

'ይጋባብሻል ይቅርብሽ!' ብለው ጮኹ፡፡

'እንዴ! እየቀለዳችሁ መሆን አለበት መቼስ?!' ስላቸው ለካንስ ከልባቸው ነበር፡፡ ልቤ ተሰበረ፡፡

ምክንያቱም ጓደኞቼ ተማሩ ከምላቸው የኅብረተሰብ ክፍል የሚመደቡ ናቸው።

ተገረምኩ፡፡

ሆ!ሆ! ተማሩ የምላቸው ጓደኞቼ እንዲህ ካሰቡማ፣ ተርታው ሕዝቤ ምን ሊያስብ ይችላል? የሚለው ሐሳብ ብቻውን እንቅልፍ ነሳኝ።

አገር ቤት ገብቼ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ የወሰንኩበት ቅጽበትም ያ የሒልተን ጎዳና መጥፎ አጋጣሚ ነው፡፡

እናት እውነቱ

የፎቶው ባለመብት, Enat Ewnetu

የምስሉ መግለጫ, እናት እውነቱ

"የ8 ወር ነፍሰ ጡር ሳለሁ በአፍጢሜ ወደቅሁ"

እናት እውነቱ ማኅበሩን ከመሠረተችው በኋላ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍል ዞራለች፤ ብዙ ታሪክ ሰምታለች፡፡

የታማሚዎችን ሕመም በሁለት መንገድ ጨምቃ ትገልጸዋለች፤ አካላዊና ስሜታዊ በሚል፡፡

አካላዊ ሕመሟን ስትገልጽ ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት ነው፡፡

"ለምሳሌ እኔ ብዙ ጊዜ ክፉ አወዳደቅ ወድቂያለሁ። በተለይ የመጀመርያው አምስት ዓመታት በየመንገዱ እወድቅ ነበር።

በዚህ የተነሳ የእጅና የጥርስ መሰበር፣ እንዲሁም የአፍንጫ መመታት ደርሶብኛል። ያን ተከትሎ ብዙ ቀዶ ሕክምና አድርጊያለሁ፡፡"

እናት በአንድ ወቅት የተቦካ ትኩስ አሸዋ ግርፍ ላይ ወድቃ የፊቷ ቆዳ ግልብጥ ብሎ ተነሳ፡፡

የከንፈር መቆረጥና መሰንጠቅን ተከትሎ ብዙ ኦፕሬሽን አደረገች፡፡

"አንድ ጊዜ ደግሞ፣ ትዝ ይለኛል፣ ጓደኛዬ ቤት ሄጄ ድንገት ወደቅኩ፡፡ ለክፋቱ እጄ ራዲዮተር ውስጥ ገባ። ቤት ማሞቅያ ራዲያተር። እና ጓደኛዬ አላየችኝም፤ ስነቃ ግማሽ እጄ ተልጧል፤ ብረት ውስጥ ገብቶ።"

የእናት እውነቱ ታሪክ ብዙ ነው፡፡ ከሁሉ የከፋው ደግሞ ነፍሰ ጡር ሆና የደረሰባት ነገር ነው፡፡

"እርጉዝ ሆኜ፣ ለዚያውም የ8 ወር ነፍሰ ጡር፣ በአፍጢሜ ተደፋሁ፡፡ ስነቃ ልጄን ያጣሁ ነው የመሰለኝ። ጭንቀቱ ሊገድለኝ ደረሰ፡፡ ጤነኛ ልጅ ወልጄ እዚህ እደርሳለሁ ብዬ አላስብኩም ነበር። እግዚያአብሔር ነው የጠበቀኝ።"

"ጓደኞቼ ፊት እንዳልወድቅ በመፍራት ከቤት መውጣት ፈራሁ"

እናት ይህ ሁሉ በሷ የደረሰው አካላዊ ጉዳት የስሜት ያህል አያምም ትላለች፡፡

"እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ የስሜቱ ጉዳት ያይላል፡፡"

እንደሷ አተያይ በቅድሚያ የሚመጣው ለራስ የሚኖር አመለካከት መዛባት ነው፡፡

በአመዛኙ ለሚጥል ሕመም የሚሰጥ መድኃኒት የሚሠራው የአእምሮው ፍጥነትን በመቀነስ ነው።

በመድኃኒቱ ምክንያት ሰውነት ውሃ ሊቋጥር ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ክብድትን ይጨምራል፡፡

"ሰውነቴ ክብደት ሲጨምር በራሴ ላይ ያለኝ አመለካከት ጥሩ አይሆንም፤ ድባቴ ውስጥ እገባ ነበር፡፡" ትላለች እናት፡፡

"የሚጥል ሕመም ሲኖርብህ የስሜት ስብራቱ ጥልቅ ነው፡፡ እኔ ትዝ ይለኛል የመጀመርያውን አምስት ዓመት ለምንድነው ግን በፈጣሪ የተረገምኩት? እያልኩ ነው የኖርኩት፤ በአጭሩ የፍርሃት ሕይወት ነበር የምኖረው፡፡"

እናት በዚያን ዘመን ከቤት መውጣት ሁሉ ያስፈራት ነበር፡፡

"ቀጠሮ ሲኖረኝ፤ እጨነቃለሁ፡፡ ቢያመኝስ? ጓደኞቼ ፊት አጉል አወዳደቅ ብወደቅስ? 'ሌሎች ስለኔ ምን ያስባሉ?' የሚለው በጭንቅላቴ ይመላለስ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ የብቸኝነት ሕይወትን ገፋሁ።"

እናት እንደምትለው ኅብረተሰቡ አይቀበለኝም የሚለው ስሜት በቀላሉ ከጭንቅላት አይወጣም።

የሆነ ሰዓት ላይ ቆረጠች፡፡ በሕይወቷ ሁለት ምርጫ እንዳላት ተገለጠላት፡፡

"በ6ኛው ዓመት ይመስለኛል፣ በቃ ወሰንኩ፡፡ 'ወይ ኢፕለፕሲ ያጠፋኛል ወይ እኔ አሸንፈዋለሁ' አልኩ። ከዚያ ሕይወቴ ተቀየረ። ትምህርት ቤት ገባሁ፣ በቢዝነስ ማኔጅመነት ማስተርሴን ሠራሁ፤ ልጅ ወለድኩ፡፡"

አሁን ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን ከሌላው ያነሰ ሕይወት ኖርኩ ብዬ አላስብም።

ከዚህ ድል ተነስቼ ነው የወንድም እህቶቼን ሕይወት ለመለወጥ ኢትዮጵያ የመጣሁት።

እናት ኢትዮጵያ መጥታ፣ ማኅበሩን መሥርታ፣ በሌሎች ወገኖቿ የደረሰውን ስታይ ግን በሷ የደረሰው ምንም እንዳልሆነ ገባት፡፡

"ብዙ ሴቶችን ሕመሙ ሲጥላቸው፣ ወንዶች ጠብቀው ይደፍሯቸዋል"

"በገጠር በሚጥል ሕመም የሚሰቃዩ እህቶቼ ብዙዎቹ የሚደርስባቸው ነገር ልብ ይሰብራል፡፡ በተለይ እንጀራ ሲጋግሩና ምግብ ሲያበስሉ ቃጠሎ ይደርስባቸዋል። የአንዳንዶቹ ግማሸ ፊታቸው በእሳት ተለብልቦ አይቻለሁ።"

የበሽታው አስከፊነት፣ ታማሚው የትና መቼ እንደሚወደቅ አለማወቁ ነው፤ ሕይወት ደግሞ መቀጠል አለበት፡፡

በገጠር የሴቶች ሕይወት ጓዳ ነው የሚያልፈው፡፡ እዚያ ደግሞ እሳት አለ፡፡ ሲጥላቸው እሳት ላይ ይወድቃሉ፡፡

በገጠር ሆስፒታሎች ስትዘዋወር በእሳት መለብለብ ደርሶባቸው የቀዶ ሕክምና ክፍል ውስጥ የገቡት ብዙዎቹ የሚጥል ሕመም ታማሚዎች ናቸው፡፡

ያውም እነዚህ ዕድለኛ ታማሚዎች ናቸው፡፡ ቤተሰባቸው የተማረና ንቃት ኖሮት፣ በሽታውን ከእርግማን ጋር ሳያይዙት ሆስፒታል ለመውሰድ የደፈሩ ናቸው፡፡

እናት ብዙ ሴቶችን እሳት ላይ ወድቀው ፊታቸው ተለብልቦ ጎብኝታቸዋለች፡፡

ፊታቸውን እሳት ሲበላው ደግሞ የሚጥለው በሽታ ላይ ሌላ የሕይወታቸው ምስቅልቅሎሽ ይከተላል።

እናት፣ በአንድ ወቅት ጅማ አካባቢ ያጋጠመቻት ልጅ እስከዛሬም ከአእምሮዋ ጓዳ አልተፋቀችም፡፡

"ልጅቷ የሚጥል በሽታ ነበረባት፤ እሳት ላይ ወደቀች፡፡ ፊቷ ጨርሶውኑ ተለብልቦ ማንነቷን መለየት እስኪያቅት ድረስ መልከ-ልውጥ (disfigured) ሆነች፡፡

ልጅቷ ታሪኳን ስትነግረኝ 'አውቶቡስ ላይ ሁሉ አይጭኑኝም' አለችኝ፡፡

'ተሳፋሪ እየለመነልኝ ነው እንጂ ፊቴ በጣም ስለሚያስፈራ አውቶብስ ላይ አይጭኑኝም' አለችኝ።

የሷ ሁኔታ ልቤን ሰበረው፡፡

በሚጥል በሽታ ሆነው፣ በሕይወት ከተረፉ እንኳ የዘላለም ቁስል ይዘው ነው የሚኖሩት፡፡ ከዚህ በላይ ምን ልብ የሚሰብር ነገር አለ?

እናት እውነቱ የጅማዋ ልጅ ጉዳት የመጨረሻው ስቃይ መስሏት ነበር፡፡

ወደ ገጠር ስትጓዝ ከዚህም የባሰ እንዳለ አወቀች፡፡

"ሚዛን አካባቢ ልናስተምር ሄደን እዛ ያሉ ነርሶች አንድ የሚያስደነግጥ ነገር ነገሩኝ፡፡ የሚጥል ሕመም ያለባቸው ሴቶች፣ የወሊድ መከላከያም አብሮ መውሰድ አለባቸው አሉኝ፡፡

"ለምን?" ብዬ ብጠይቅ ጊዜ ምክንያቱም እኛ ጋ የሚመጡት ብዙዎቹ ማን እንዳስረገዛቸው እንኳን አያውቁም፤ ወንዶች ሕመሙ ሲጥላቸው ጠብቀው ይደፍሯቸዋል" አሉኝ፡፡

"ተደፍረው ያረግዛሉ፤ ሲጨንቃቸው ወልደው መንገድ ላይ ይጥሏቸዋል።"

የሚጥል በሽታ ያለባቸው የጎዳና ተዳዳሪ ሴቶች ይደፈራሉ?

አቶ ዐቢይ አስራት ‹የኬር ኢፕለፕሲ ኢትዮጵያ› ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡

ከተመሠረተ 7 ዓመታት የኾነው ይህ ማኅበር ወደ 1ሺህ የሚጠጉ አባላት አሉት፡፡

በበጎ ፈቃድ የሚሠሩ የነርቭ ስፔሻሊስት ሐኪሞችም ያግዟቸዋል፡፡

ከኒውሮሎጂስት አሶሲየሽን ጋር በጥምረት ይሠራሉ፡፡ በሕጻናት ስፔሻሊስት ሐኪሞችም ይታገዛሉ፡፡

"ያለ ምንም ክፍያ በበጎ ፈቃድ የሚያግዙን ደጋግ ሐኪሞችን ከማመስገን ውጭ ውለታቸውን አንመልሰውም" ይላል ዐቢይ፡፡

ማኅበሩ አቅም ያጡ ታማሚዎች ሲመጡ ከመድኃኒት ጀምሮ የኢሜጀሪ ሕክምና ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

"የሚጥል በሽታ ያለበት አንድ ሰው ብቻውን አይደለም የሚታመመው፡፡ መላ ቤተሰቡ ነው የሚታመመው፡፡ አቅም ያጡትን ቤታቸው ድረስ ሄደን እናግዛቸዋለን፡፡ ዱቄት፣ ፓስታ፣ ዳይፐር ይዘን ሄደን እንጠይቃቸዋለን፡፡"

ዐቢይ በማኅበራቸው ውስጥ በጣም ሕጻናት የኾኑ የሚጥል በሽታ ታማሚዎች እንደሚገኙ ይገልጣል፡፡ ሊስትሮዎች፣ የጎዳና ልጆች…፡፡

በተለይ በሴት ታማሚዎች ዘንድ የሚታየውን ስንክሳር ሲያስረዳ ወ/ሮ እናት ቀደም ብሎ ያነሳችውን ሐሳቦች ይጋራል፡፡

ወደ ማዕከላቸው ለእርዳታ የሚመጡ በርካታ ሴቶች እንዳሉ ያወሳና፣ ከነዚህ መሀል ደግሞ የተደፈሩ የጎዳና ልጆች እንደሚገኙበት ይጠቅሳል፡፡

"የሚጥል በሽታ ያለባቸው ከጎናዳ ወደኛ የመጡ ሴቶች አሉ፡፡ የደረሰባቸውን ይነግሩናል፡፡

ጎዳና ሲኖሩ ራሳቸውን ስተው በሚንቀጠቀጡ ሰዓት እነሱን ከመርዳት ፋንታ ወንዶች አጋጣሚውን ተጠቅመው ይደፍሯቸዋል፡፡ ወንዶቹ በሱስ ስለሚደነዝዙም ጭምር ነው ይህን ፀያፍ ተግባር የሚፈጽሙት፡፡"

"ከ1.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያን በላይ በሚጥል በሽታ ይሰቃያሉ"

ኬር አፕለፕሲ ኢትዮጵያ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ያለው አንዲት ቢሮ ተከራይቶ ነው፡፡

ያቺ ቢሮ ደግሞ ፎቅ ላይ ነው ያለችው፡፡

አባላት እዚያች ቆጥ ላይ እየወጡ ነው የሚረዱት፡፡

ቢሯቸው ፎቅ ላይ በመሆኑ ሊረዱ የመጡ ታማሚዎች የመውደቅም እጣ ፈንታ ሊገጥማቸው ይችላል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት ግምት ከሆነ በኢትዮጵያ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ የሚጥል በሽታ ተማሚዎች ይገኛሉ፡፡

አንዳንድ ጥናቶች ይህን ቁጠር እስከ 5 ሚሊዮን ያስጠጉታል፡፡

"ሕዝባችንን፣ ወገናችንን የምናገለግለበት ማዕከል እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡ ቦታ እንዲሰጠን ጠይቀን ምላሽ አላገኘንም፡፡ መንግሥት ነገሩን ትኩረት እንዲሰጠው እንሻለን፡፡" ይላል ዐቢይ፡፡

"ሰርጌ ሳምንት ሲቀረው ሙሽራው ጠፋ"

የሚጥል በሽታ ያለባቸው ሴቶች ስቃያቸው የበዛ ነው፡፡ የስንክሳሮቹ መዘርዝር የትየለሌ ነው፡፡

ለምሳሌ የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ሦስት ጉልቻ መመሥረት የዋዛ አይሆንም፡፡

ወልዶ መክበድ የማይታሰብ ነው፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ ካለው የተንሸዋረረ አመለካከት የተነሳ ለፍቅር ወዳጅነት የሚፈቅዳቸው እምብዛምም ነው፡፡

የዘር እርግማን ነው የሚለው አስተሳሰብ ሥር ስለሰደደ ከነርሱ አብራክ ልጅ ማፍራት ለብዙ ‹የተማሩ› ወንዶች ጭምር አስፈሪ ነው፡፡

ወ/ሮ እናት በዚህ ረገድ የሰማችው አንድ አስረጅ ለቢቢሲ አጋርታ ነበር፡፡ ሐተታችንን በሱ እናሳርገው፡፡

"አንድ እኛ ማኅበር የምትመጣ ልጅ ነበረች፡፡ ልታገባ ሁሉ ነገር ጨርሳ፣ ሰርጉ ሳምንት ሲቀረው አመማት፡፡ እጮኛዋ እንደሚያማት ያውቃል፡፡ ግን ከዚያ በፊት ስትወድቅ አይቷት አያውቅም ነበር፡፡ ካያት በኋላ ሰርጉን ሰረዘው። ልትሞሸር አንድ ሳምንት ሲቀራት ሙሽራው ጠፋ።"

ይህቺ ሴት ቢሮ መጥታ እንዴት ታለቅስ እንደነበረ ወ/ሮ እናት እውነቱ ልክ እንደ ትናንትና የሆነ ያህል ታስታውሳታለች፡፡

"የሚያሳዝነው እሱ አይደለም፡፡ ልጅቷ ታለቅስ የነበረው ለሷ አልነበረም፡፡ ከኔ በላይ እናቴን አሳፈርኳት እያለች ነበር የምታነባው።"

ወ/ሮ እናት የዚህችን እህቴን ስብራት ለመጋራት ነው ወደ አገር ቤት የተመለስኩት ትላለች፡፡

"አውቃለሁ፣ አንድ ሰው ነኝ፤ አውቃለሁ፤ አንድ ሰው ሁሉን መቀየር አይችልም፤ ግን እኔ ጀምሬዋለሁ፤ ማን ያውቃል- ደግሞ ሌላው ይቀጥለዋል፡፡"

የሚጥል በሽታ ምንድነው?

የሚጥል በሽታ በጥቅሉ የሥርዓተ ነርቭ ችግር ነው፡፡ ተገቢው ሕክምና ክትትል በማድረግ ግን መቆጣጠር ይቻላል፡፡

ይሁንና የሕክምና ሒደቱ ዘለግ ያለና ጥብቅ ክትትልን የሚሻ ነው፡፡ መድኃኒቶቹም ዘለግ ላለ ጊዜ የሚወሰዱ ናቸው፡፡

ብዙውን ጊዜ ኮርቴክስ የአእምሮ ክፍል ላይ ችግር ሲከሰት፣ በጭንቅላት የተወሰነ ክፍል የደም መዘዋወር ሲስተጓጎል፣ አልያም በዚያው ክፍል ጠባሳ ወይም እጢ ሲኖር ይህ በሽታ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል እንዳለ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ይህን ተከትሎ የነርቭ መታወክ (Seizure) ይከሰትና ታማሚው ለደቂቃዎች ያለበትን የመርሳት፣ ጡንቻው የመገታተር እና የሰውነትን እንቅጥቃጤ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡

ይህ የሚሆነው በአእምሮ ውስጥ ያለው የኤሌክትሪክ ስርጭት ለተወሰነ ደቂቃ ስለሚታወክ ነው፡፡

ሕክምናው የት ይሰጣል?

ለሚጥል በሽታ ሕክምና በአገራችን ቀደም ብሎ በአማኑኤል ሆስፒታል ይሰጥ ነበር፡፡

ይህ መሆኑ ምናልባት ለበሽታው አሉታዊ አተያይ እንዲኖር አንድ ምክንያት ፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ አልጠፉም፡፡

ይሁንና ከጊዜ በኋላ ኒውሮሎጂ ዲፓርትመንት ባለባቸው የግልና የመንግሥት ሆስፒታሎች ሁሉ ሕክምናው ይገኛል፡፡

አቶ ዐቢይ እንደሚሉት ደግሞ ማኅበራቸው ለኢፕሌፕሲ ሕክምና ታች ከጤና ጣቢያ ጀምሮ አቅርቦት እንዲኖር ጉትጎታና ድጋፍ አድርጓል፡፡

ታማሚዎች ከፍ ላለ ሕክምና የኢኢጂ (EEG) እና ኤምአርአይ (MRI) ምርመራዎች ሲያስፈልጓቸው ደግሞ ይህን ምርመራ ለማድረግ አቅም ላጡ ዜጎች ትብብር ያደርጋሉ፡፡

‹‹የኢኢጂ ማሽን በበጎ አድራጊዎች ከውጭ ገብቶልናል፡፡ አቅም ላጡ ሰዎች በኛ በኩል ከበጎ ፈቃደኛ ኒውሮሎጂስት ስፔሻሊስቶች ጋር በመተባበር የዚህ ምርመራ ክትትል እንዲደረግላቸው እናደርጋለን፡፡›› ይላሉ አቶ ዐቢይ፡፡