ጤና፡ የወጣቶች የወገብ ህመም መንስዔ እና መፍትሔው

የፎቶው ባለመብት, Dr. Theodros W. Gebriel
አሁን አሁን የወገብ ህመም አጋጥሟቸው የህክምና ተቋማትን የሚጎበኙ ወጣቶች እየተበራከቱ ነው። በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ለወገብ ህመም የሚጋለጡ ወጣቶች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጥናቶች ያመለክታሉ። ለመሆኑ ለዚህ መንስዔው ምንድን ነው? መፍትሔውስ?
በዚህ ላይ በፓራጎን የፊዚዮቴራፒና ስፓርት ህክምና ስፔሻሊቲ ልዩ ክሊኒኮች ውስጥ ሥራ አስኪያጅ እና ሜዲካል ዳሬክተር ከሆኑት ዶ/ር ቴዎድሮስ ወ/ገብርኤል ጋር ቆይታ አድርገናል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ሦስቱንም ድግሪያቸውን የተከታተሉት በአሜሪካ ሲሆን በፊዚዮቴራፒ በተለይ በስፖርት ህክምና እና ኦርቶፔዲክስ ህክምና ዶክትሬታቸውን አግኝተዋል።
በሙያቸው በአሜሪካ ለ10 ዓመታት የሰሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ ላለፉት 12 ዓመታት እያገለገሉ ይገኛሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ትምህርት ቤት ውስጥ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። በጥቁር አንበሳ ህክምና ትምህርት ቤት በፊዚዮቴራፒ ዶክትሬት ፕሮግራም በመምህርነት ሠርተዋል።

ብዙውን ጊዜ ወጣቶች ለወገብ ህመም ያጋለጣቸውን መንስዔ በውል አያውቁትም። እንዲሁ በደፈናው ድንገት አመመኝ ሲሉ ነው የሚሰማው። ለመሆኑ የወገብ ህመም መንስዔዎች ምንድን ናቸው?
የሰውነት ማጎልመሻ እንቅስቃሴዎች፣ የምንጫማቸው ጫማዎች ፣ የምንተኛበት ፍራሽ ፣ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈፀምበት መንገድ ( Sex position) . . . ለወገብ ህመም ይዳርጉ ይሆን?
ወደዚህ ዝርዝር ከማለፋችን በፊት ስለወገብ እና የወገብ ህመም ምንነት እናንሳ።
ወገብ ቀበቷችን ወይም መቀነታችን የሚያርፍበት የሰውነታችን ክፍል ሲሆን በዚህ ላይ የሚከሰት ህመም የወገብ ህመም ይባላል።
የወገብ ህመም ጽንሰ ሃሳቡ ሰፊና ጥልቅ ቢሆንም በቀላል አገላለጽ በወገብ አካባቢ በሚገኙ ጡንቻዎች ፣ የነርቭ ሥሮች፣ የአከርካሪ አጥንቶች፣ የጎን አጥንቶች እና ጅማቶች ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው። ይህ ጉዳት ጊዜያዊ ወይም ዘለቄታዊ ሊሆን ይችላል።
የወገብ ህመም ዓይነቶች እንደ መንስዔያቸው ይለያያሉ። ዋና ዋናዎቹ ግን እነዚህ ናቸው፦
- የዲስክ መንሸራተትና መጎዳት፣
- የአከርካሬ አጥንት አንዱ በአንዱ ላይ መደራረቢያ ክፍል (facet joints) መቁሰልና መድረቅ፣
- ረዘም ላለ ጊዜ በመቆምና በመቀመጥ የሚፈጠር ከነርቭ መጨፍለቅ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ህመም እና
- የሰውነት በሽታ ተዋጊ ሂደት በመዛባት የሚከሰት የወገብ ህመም
ከመጨረሻው ነጥብ እንጀምር።
የሰውነት በሽታ ተዋጊ ሂደት በመዛበት የሚከሰተው የወገብ ህመም የሚያጋጥመው ሰውነት በሽታን የሚከላከልበት ሂደት ሌሎች የሰውነት አካላትን ሲያጠቃ ነው። በእንግሊዝኛ አጠራሩ Ankylosing spondylitis ይባላል።
የሰውነት የውስጥ ቁስለትን በመፍጠር ዘለግ ላለ ጊዜ የሚቆይ ህመም ነው።
የዚህ ህመም ምክንያቱ ምን እንደሆነ በውል አይታወቅም። በተለይ በመገጣጠሚያዎች እና በአከርካሪ አጥንቶች መጋጠሚያ መካከል ቁስለትን ያስከትላል።
ህመሙ እየጨመረ ሲሄድም የአከርካሪ አጥንቶች እንዲንቀሳቀሱ እንደ ሃዲድ የሚያገለግለው የሰውነት ክፍል ላይ አጥንቶቹ መንቀሳቀሳቸውን ትተው እርስ በእርሳቸው እንዲጣበቁ ያደርጋል። በዚህ ምክንያት አጥንቶቹ መንቀሳቀሳቸው ቀርቶ አንድ አካል ይሆናሉ።
በዚህ ህመም የተጠቃ ሰው ማጎንበስ፣ ወደ ኋላ አሊያም ወደ ጎን መንቀሳቀስ አይችልም።
የሌሎቹ የወገብ ህመም ዓይነቶች መንስዔዎችስ?
ለወገብ ህመም የሚዳርጉን መንስዔዎች በርካታ ቢሆኑም ዶ/ር ቴዎድሮስ በ21 ዓመት የህክምና ልምዳቸው የተመለከቷቸውንና ዋና ዋና ያሏቸውን መንስዔዎች ያስረዳሉ።
ከባድ ነገር ማንሳት፡ ማንኛውም ሰው በዕለት ተዕለት ክንውኑ ጥንቃቄ ካላደረገ ወገቡን ሊታመም ይችላል። በባልዲ ውሃ ቀድቶ ፎቅ ላይ መውሰድ፣ ክብደት ያላቸውን ሰዎች ከአልጋ ማንሳት እንዲሁም ማንኛውንም ከአቅም በላይ የሆነ ክብደትን ማንሳት ለወገብ ህመም ሊዳርግ ይችላል።
ከልክ በላይ የሆነ የሰውነት ክብደት መኖር፡ በተለይ በአንድ ጊዜ የሚጨምር የሰውነት ክብደት የወገብ ህመም እንደሚያስከትል ዶ/ር ቴዎድሮስ ይናገራሉ። "በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት አካላዊ እንቅስቃሴ የሌለው ሥራ በመዘውተሩ በዚህ ሳቢያ የሚከሰት ህመም ተበራክቶ ነበር" ይላሉ።
ረዘም ላለ ጊዜ ቆሞ፣ ተቀምጦ ወይም ቆሞ ጎንበስ ብሎ መስራት፡ ረዘም ላለ ጊዜ ቆመው፣ ተቀምጠው አልያም ቆመው ከአንገታቸው ተጎንብሰው በሚሰሩ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች ለወገብ ህመም የመጋለጣቸው ዕድል ሰፊ ነው።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አንድ ሰው ቆሞ ከአንገቱ ጎንበስ ብሎ በሚሰራበት ጊዜ በሁለት አከርካሪ አጥንቶች መካከል ወደ 270 ኪሎ ግራም ግፊት እንዳለው ጥናቶችን ያጣቅሳሉ። ይህን በየቀኑ ማድረግ ደግሞ ከጊዜ በኋላ የከፋ ጉዳት ያስከትላል። ብዙ ጊዜ የቀዶ ህክምና ሐኪሞች በዚህ ሳቢያ ለሚከሰት የወገብ ህመም ሲጋለጡ ይስተዋላል።
ብዙ መንገጫገጭ ያላቸው የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን ማሽከርከር፡ ብዙ ንዝረት ያላቸው የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን ማሽከርከር ወይም ምቹ ባልሆኑ መንገዶች ላይ መኪና ማሽከርከር ከጊዜ በኋላ የወገብ ህመም ያስከትላል።
የዝላይ እና የሩጫ እንቅስቃሴዎች፡ በተለይ ከልክ በላይ የሰውነት ክብደት ያላቸው ሰዎች ሩጫ ወይም የመዝለል እንቅስቃሴ የሚያዘወትሩ ከሆነ ወገባቸው ሊጎዳ ይችላል።
እንደ አስፓልት ያለ ጠንካራ የሆነ ቦታ ላይ የሚሮጡ ሰዎችም መሬቱ ላይ እግራቸውን በጣሉ ቁጥር መሬትም በአጸፋው ስለሚመታቸው ለጉዳት ሊዳርጋቸው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ወጣ ገባ የሆነ መሬት ላይ የሚሮጡ ሰዎች እግራቸው በሚያርፍበት ሰዓት ሚዛናቸው እኩል ስለማይሆን ወገብ ላይ ጫና ይፈጠራል።
ሰውነት ሳይለምድ በአንድ ጊዜ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ መስራት፡ አሁን አሁን በወጣቶች ዘንድ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እየተለመደ መጥቷል። የሚሰሯቸው እንቅስቃሴዎችንም ዩቲዩብ በማየት የሚመርጡም አሉ።
ይህ ብቻም ሳይሆን ስፖርቱን ለምን ዓላማ እንደሚሰሩ የማያውቁ በርካቶች ናቸው። በዚህ ሳቢያ ተጎድተው ወደ ክሊኒካቸው የሚመጡ ወጣቶች መኖራቸውን ዶ/ር ቴዎድሮስ ይናገራሉ።
"ችግሩ አካላዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ የተከሰተ ሳይሆን ሰውነት ሳይለማመድ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ መስራት ነው" ይላሉ።
"ጂምናዚየም ውስጥ ለአሰልጣኝ ጉርሻ መስጠት የተለመደ ሆኗል" የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አንዳንድ አሰልጣኞች ጉርሻዋን ለማግኘት ደንበኞቻቸው የሚፈልጉት የሰውነት ለውጥ ላይ ቶሎ ማድረስ ላይ ብቻ ትኩረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ። አሰልጣኞቹ ስለስፖርታዊ እንቅስቃሴው እንጂ ስለጤና እውቀት ላይኖራቸውም ይችላል።
አንዳንድ ሰልጣኞችም በአንድ ጊዜ በሰውነታቸው ላይ የሚፈልጉት ለውጥ እንዲመጣ ባልተገባ መልኩ ከልክ በላይ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ይህንን ሲገልጹት "ምንም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርጎ የማያውቅ ሰው ቅዳሜ እና እሁድ ጂምናዚየም ገብቶ አገር ይያዝልኝ እንደ ማለት ነው" ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዲስክ መንሸራተት፡ የዲስክ መንሽራተት ስሙ ለብዙዎቻችን ጆሮ እንግዳ አይደለም።
ዶ/ር ቴዎድሮስም የዲስክ መንሸራተት ያለ ስሙ ብዙ ስም የተሰጠው በሽታ ነው ይላሉ።
ዶ/ር ቴዎድሮስ እንደሚሉት የዲስክ ችግር ተብለው ወደ ክሊኒካቸው ከሚመጡት 100 ሰዎች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ችግራቸው ሌላ ነው።
በተለምዶ የህክምና ባለሙያዎች ህሙማንን ለዲስክ መንሸራተት ተዳርገዋል የሚሉት 'ኤምአርአይ' መመርመሪያ የሚያሳየው ውጤት ላይ ተመርኩዘው ነው።
ይሁን እንጂ ዶ/ር ቴዎድሮስ "10 ሰዎችን እንዲሁ ከመንገድ ላይ በግምት ተመርጠው ኤምአርአይ ቢነሱ ቢያንስ 7ቱ የዲስክ መንሸራተት ሊያሳዩ ይችላሉ" ይላሉ። ይህ ማለት ግን ህመም አለባቸው ማለት አይደለም።
"የዲስክ መንሸራተት ታይቷል ማለት የተዛባ ዲስክ አላቸው፤ ግን ዲስኩ ነርቩን ጨፍልቆ ህመም የሚያመጣበት ደረጃ ላይ አይደለም ማለት ነው" ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ።
በዚህ የምርመራ ውጤት ላይ ተመስርተው ቶሎ ቀዶ ህክምና አድርጉ ወደሚል ድምዳሜ የሚደርሱ የህክምና ባለሙያዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ይህ ግን ስህተት ነው ብለዋል።
ለመሆኑ ዲስክ ምንድን ነው? የሚገኘውስ የት ላይ ነው?
ዲስክ በአከርካሪ አጥንቶች መካከል የሚገኝ በውስጡ ፈሳሽ ያለው ለስላሳ የሆነ እንደ ጎሚኒ (ሾክ አብሶርቨር) የምንጠቀምበት የአካል ክፍል ነው።
ታዲያ ሰውነታችን ጫና በሚበዛበት ጊዜ በዲስኩ ውስጥ ያለው ፈሳሽ ሊወጣ ይችላል ወይም ደግሞ ፈሳሹ ሳይወጣ ዲስኩ ወደ አንድ በኩል አመዝኖ መውጣት ወደማይገባበት ቦታ ሊወጣ ይችላል።
ዲስክ ያለበት አካባቢ የተጨናነቀ በመሆኑ አፈትልኮ በሚወጣበት ጊዜ ከጭንቅላታችን በሚወርደውና ህብለ ሰረሰር በሚባለው የነርቭ ግንድ እና ቅርንጫፎች ላይ በመተኛት ጫና ይፈጥራል።
የዲስክ መንሸራተት በሚያጋጥምበት ጊዜ ቀዶ ህክምና ለማድረግ ከመጣደፍ በፊት ዲስኩ ተንሸራቶ ምን ሆነ? ወዴት አቅጣጫ ነው የተንሸራተተው? ምን ያህል ነው የተንሸራተተው? እየነካ ያለውስ ነርቭ የትኛውን ነው? ሊያስከትል የሚችለው የህመም ስሜት አለ ወይ? የሚሉትን ወሳኝ ጥያቄዎች መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ቴዎድሮስ ያሰምሩበታል።
ወጣቶችን ለወገብ ህመም የሚያጋልጣቸው የተለየ ምክንያት ይኖር ይሆን?
ከምንጊዜውም በላይ ብዙ ወጣቶች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ላይ እየተሠማሩ መሆናቸው አንዱ ምክንያት ነው ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ።
ወጣቶች ረዘም ያለ ጊዜ መቆምን፣ መቀመጥን አሊያም ጎንበስ ብሎ መቆምን እንዲሁም ከባድ ነገር ማንሳትን፣ መሸከምን የሚጠይቁ ሥራዎችን ይሠራሉ።
በሌላም በኩል ከዚህ ቀደሙ በተሻለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተርም ሌላኛው ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።
"ስለምንሰራው አካላዊ እንቅስቃሴ ጠለቅ ያለ እውቀት ከሌለን በስተቀር የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ጥቅም እንዳላቸው ሁሉ ጉዳት አላቸው።" ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ።
በተቃራኒው ደግሞ የሰውነት እንቅስቃሴ ማነስ ለወገብ ህመም መንስዔ ነው።
የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለወገብ ህመም ያጋልጣል?
የግብረ ሥጋ ግንኙነት በሳይንስ እንደ ወገብ ህመም መንስዔነት ወይም እንደ ወገብ ህመም መነሻነት አይታወቅም ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ።
ይሁን እንጂ የወገብ ህመም ያለባቸው ሰዎች የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚፈጽሙበት መንገድ ህመማቸውን ሊያባብስባቸው ወይም የተሻላቸውን ህመም እንደገና ሊያስነሳባቸው እንደሚችል ይናገራሉ።
"በተለይ በሴቶች ዘንድ ይህንን ለሐኪም የማስረዳት ልምድ የለም" የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አንዳንዶች ግን በስልክም ቢሆን ምክር የሚጠይቁ መኖራቸውን አልሸሸጉም።
"እንደ የወገብ ህመማቸው ዓይነትም ለተወሰነ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አደራረግ (Sex position) እንዲቀይሩ፣ እንዳያደርጉ ወይም ሊያደርጓቸው ስለሚችሉ የግብረ ሥጋ ግንኙነት አደራረግ ዓይነቶች ምክር የሚሰጣቸው ታማሚዎች አሉ" ይላሉ።
የምንጫማው ጫማስ?
የወገባችንን ጤንነት ለመጠበቅ የምንጫማው የጫማ ዓይነት ወሳኝነት አለው።
ይህ ግን በአብዛኛው የሚገናኘው ከሴቶች ጋር ነው። ምክንያቱም በተለይ በፋሽንና መዝናኛ ኢንደስትሪው ሴቶች መንቀሳቀስ እስከሚቸገሩ ድረስ ረጃጅም ታኮ ያላቸውን ጫማዎች ተጫምተው ማየት የተለመደ ነው። ይህ ደግሞ በሰውነት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። እንዴት?
ዶ/ር ቴዎድሮስ ለዚህ ሳይንሳዊ ምላሽ አላቸው።
ሰውነት የራሱን ሚዛን የሚጠብቅበት መንገድ አለው። ይህ የስበት ማዕከል (Center of gravity) ይባላል።
ስንራመድ የማንወድቀው ወይም ደግሞ ቁጭ ብለን ስንነሳ ከግድግዳ ጋር የማንጋጨው ይህ የመሬት ስበት ማዕከል ሚዛናችንን ስለሚጠብቅልን ነው።
ታዲያ ከፍ ያሉ ታኮዎች ያሏቸውን ጫማዎች ስንጫማ ሰውነት ተፈጥሯዊ የሆነውን የሰውነት ሚዛን ይለቃል። የሰውነታችን የመሬት ስበት ማዕከልም ይቀየራል። በመሆኑም ሰውነት ይህንን የስበት ማዕከል መልሶ ወደ ማዕከሉ ላይ ለማምጣት (ሚዛኑን ለመጠበቅ) የሚያደርጋቸው ማስተካከያዎች ወገብ ላይ ጫና ይፈጥራሉ።
ጫናው ወገብ ላይ ብቻ ሳይሆን ጉልበት፣ እግርና የእግር መዳፍ ላይም ነው።
ከዓመታት በፊት በዩናይትድ ኪንግደም በፖዲያትሪ ኮሌጅ የተሠራ ጥናት ሴቶች ህመም እንደተሰማቸው ሳይናገሩ ከፍ ያለ ታኮ ጫማ ተጫምተው መቆየት የሚችሉት በአማካይ ለአንድ ሰዓት ያህል ነው ይላል።
በዚህ ጥናት ተሳታፊ የነበሩ ሴቶች ጫማውን ከተጫመቱ ከ10 ደቂቃ በኋላ በእግራቸው ላይ ህመም እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሌላ በኩል ደግሞ ሰው የተፈጠረው በባዶ እግሩ ለመሄድ ነው በማለት ሰዎች በባዶ እግራቸው እንዲሄዱ የሚያበረታታ ሳይንስ አለ። በዚህም ምክንያት ሆነ ብለው በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ሰዎች አሉ።
በእርግጥ ዶ/ር ቴዎድሮስ በባዶ እግር መሄድ አሊያም በጣም አነስተኛ ታኮ ያላቸው ጫማዎች ማድረግ ጉዳት አለው ብለው አያምኑም።
ይሁን እንጂ በተፈጥሮ 'የእግራቸው ቅርጽ ለየት ያለ' ሰዎች ከተረከዝ ሁለት ሴንቲ ሜትር ከፍ ያለ ታኮ ያለው ጫማ እንዲያደርጉ ይመክራሉ።
"ተረከዝ በጫማ መሄድ ከለመደ በኋላ በባዶ እግር በብዛት መሄድ በተረከዝ ላይ አጥንት መብቀልን (Bone Spur) ሊያስከትልም ይችላል" ይላሉ። ይህ አጥንት የተረከዝን ስጋ እንደ ጩቤ የሚወጋ ነው።
በመሆኑም በተለይ በባዶ እግር መሄድ ያልለመደ እና ተረከዝ ላይ በቂ የስብ ንጣፍ (Fat pad) የሌለው ሰው በባዶ እግሩ ቢሄድ ለእንዲህ ዓይነት ችግር ሊጋለጥ እንደሚችል ያሳስባሉ። ይህ ግን በስፋት የሚከሰት አይደለም።
የወገብ ህመም እንዳጋጠመን እንዴት ማወቅ እንችላለን?
እንደማንኛውም ህመም የወገብ ህመም ሲያጋጥም የሚታዩ ከቀላል እስከ ከባድ ምልክቶች አሉ።
የህመም ማስታገሻ መድሃኒት የማያስወስዱ፣ ቁጭ ስንል የሚያስታውሱን፣ መድሃኒት እስከ መውሰድ የሚያደርስ የማቃጠልና መቆጥቆጥ ስሜት፣ ጎንበስ ብሎ ቀና ለማለት መቸገር፣ ለመነሳት ድጋፍ መፈለግ፣ የጡንቻ መኮማተር፣ ለመንቀሳቀስ መቸገር፣ ተኝቶ ለመገላበጥ ማቃት የተወሰኑት ምልክቶቹ ናቸው።
የሚታዩት ምልክቶች ግን እንደ ህመሙ መንስዔዎች ይለያያሉ።
ለምሳሌ ረዘም ላለጊዜ በመቆም ወይም በመቀመጥ የሚመጣ ህመም ከሆነ ተቀምጠን ቆይተን ድንገት ስንነሳ የሰውነት መያዝ ፣ ስንቀመጥ ወይ ስንቆም ህመም መሰማት፣ የመቀመጫ አካባቢ ህመም፣ መጠዝጠዝና ንዝረት ያጋጥማል።
ንዝረቱ ከመቀመጫ አለፍ ብሎ ቁርጭምጭሚት ፣ ጣቶች እና የእግር መዳፍ ድረስ የሚሰማ የመደንዘዝና የማቃጠል ህመሞች እየባሰ ሲመጣም የእግር መክዳትና ደረጃ ለመውጣት አቅም እስከማጣት ሊደርስ ይችላል።
እግርን ማዘዝ፣ ጣቶችን ወደ ላይ ቀና ማድረግ ካቃተን ግን ህመሙ የከፋ ደረጃ ደርሷል ማለት ነው። ምን አልባት ይህ ቀዶ ሕክምና የሚያስፈልግበት ደረጃ ሊሆን ይችላል።
ያጋጠመንን የወገብ ህመም ለማስታገስ በቤት ውስጥ ምን ማድረግ እንችላለን?
በአቅራብያ የህክምና ተቋም ከሌለ ለጊዜው የህመም ማስታገሻዎችን መውሰድ ይመከራል። ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን ሌላ የሚወስዱት መድሃኒት ከሌለ እና ከሚወስዱት መድሃኒት ጋር የማይጋጭ ከሆነ ነው። ዘላቂ መፍትሔ ግን አይደለም።
የወገብ ህመሙ የተከሰተው በድንገተኛ አደጋ [መውደቅ] ከሆነ ደግሞ በመጀመሪያ ህክምና እርዳታ በረዶ ማድረግ ጥሩ ነው።
"የቁስለት ሂደቱን ለመቀነስ፣ እብጠት እና ውስጥ የደም መፍሰስ እንዳይኖር ይረዳል" ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ። ከዚህ በኋላም የጡንቻ መኮማተር የሚኖር ከሆነ ሙቀት ሰውነትን የማፍታታት ባህርይ ስላለው ሙቀት ማድረግ የተሻለ መሆኑን ይመክራሉ።
እረፍት ማድረግም ህመማችንን በተወሰነ ደረጃ ሊያስታግስልን ይችላል።
ይህን ሁሉ አድርገን የማይሻል ከሆነ ግን ሥር ሳይሰድ እንደ ምንም ወደ ህክምና ቦታ ሄዶ ትክክለኛ ህክምና ማድረግ አስፈላጊ ነው።
"አንዳንድ ሰዎች ባህላዊ ቦታ ሄደው ባልተገባ ሁኔታ ህክምና ወስደው ተጎድተው የሚመጡ አሉ" ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ። እንደዚህ ያሉ ቦታዎችን ከሚያዘወትሩ ሰዎች መካከል የተማሩ ሰዎችም ጭምር እንደሚገኙበት በመግለጽም ይህ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ።
ህመሙን ለማስወገድ ሲባል ያልተገባ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግም ጉዳቱን ሊያባብሰው እንደሚችል ዶ/ር ቴዎድሮስ ያስጠነቅቃሉ።
ወገባችንን በህክምና ቀበቶ ወይም በመቀነት ብንደግፈውስ?
የወገብ ህመም የተለያዩ ደረጃዎች አሉት። መጀመሪያ አካባቢ ችግሩ እንደተፈጠረ፣ ከዚያ ከሁለት እስከ ሦስት ወር እና ከሦስት ወር በላይ የቆየ ህመም ናቸው። ህመሙ ከሦስት ወር በላይ የቆየ ከሆነ ሥር የሰደደ ችግር ይባላል።
በመሆኑም ህመሙ እንደ ጀመረ አካባቢ እረፍት ማድረግን ጨምሮ በመቀነት ማሰር ወይም በቀበቶ መደገፍ ያገዘን ስለሚመስል በሥነ ልቦናም ሆነ አካላዊ በሆነ መልኩ ሊደገፍ ይችላል ይላሉ- ዶ/ር ቴዎድሮስ።
ሆኖም ይህ ለረዥም ጊዜ የሚደረግ ከሆነ ችግር እንደሚያስከትል ይናገራሉ። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም "ቀበቶ ተደረገ ወይም መቀነት ታሰረ ማለት እዚያ አካባቢ ያሉ ጡንቻዎች እረፍት ወጡ ማለት ነው።" ይላሉ።
በዚህ ሳቢያም የጡንቻ መክሳት ችግር ይከሰታል። በመሆኑም ጡንቻችን ያለ ድጋፍ ሥራውን መሥራት ይቀንሳል፤ አልያም ያቆማል። ይህም ሰዎች በቀበቶ አሊያም በመቀነት ላይ ጥገኛ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
"በኢትዮጵያ በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ የአንገት መደገፊያ [ኮላር] እና የወገብ መደገፊያ ቀበቶ የማዘዝ ችግር ጎልቶ እየታየ ነው" የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ የችግሩ መንስዔ ሳይታወቅ እነዚህን ቁሶች ማዘዝ ተገቢ እንዳልሆነ ይናገራሉ።
አንዳንድ ጊዜ ሐኪሞች ቀበቶ ማዘዛቸውን ሊዘነጉት የሚችሉበት አጋጣሚም ስለሚኖር ታማሚዎቹ ለረዥም ጊዜ ቀበቶውን ሊያደርጉት ይችላሉ። ይህ ደግሞ ጉዳት ያስከትላል ይላሉ ዶ/ር ቴዎድሮስ።
ምን ዓይነት ፍራሽ እና ትራስ ላይ እንተኛ ?
መቼም በወገብ ህመም ሳቢያ ፍራሽ ያልቀያየረ፤ ከአልጋ መደብ ፣ ከመደብ አልጋ ያላለ አይኖርም። ትራስም ቢሆን እንዲሁ። ምን ዓይነት ፍራሽ ላይ እንተኛ ? ምን አይነት ትራስ እንጠቀም የበርካቶች ጭንቀት ነው።
ለወገብ ህመም ፍቱን ናቸው የተባሉ ፍራሾችም ይቸበቸባሉ።
በሰለጠነው ዓለም የተለያዩ ዓይነት ዘመናዊ ፍራሽና ትራሶች እየተመረቱ ነው። በአንድ አልጋ ላይ ባልና ሚስትን በመረጡት ፍራሽ ላይ የሚያስተኛ ቴክኖሎጂም ተፈልስፏል።
ታዲያ የትኛው ላይ ብንተኛ የተሻለ ነው?
ዶ/ር ቴዎድሮስ "ታማሚዎቹ ተመቸን ያሉትን ፍራሽ ትክክል አይደለም ማለት አስቸጋሪ ነው ምክንያቱም ሰውነታቸው ከመረጡት ፍራሽ ጋር ተመቻችቶ ሊሆን ይችላል" ይላሉ። ቢሆንም ግን ደረቅ ፍራሽ ላይ መተኛትን አይመክሩም።
እርሳቸው የሚመክሩት ሰውነት ቅርጹን በጠበቀ መልኩ የሚያሳርፍን ፍራሽ ወይም ትራስ ነው።
"ራቁታችንን በመስታዎት ብንመለከት ሰውነታችን እጥፋቶች (Curves) አሉት። ስንተኛ እነዚያ እጥፋቶች ቅርጻቸውን ጠብቀው በትክክል ማረፍ አለባቸው" ይላሉ።
ለዚህም ነው በሰለጠነው ዓለም 'ሚሞሪ ፎም' የተመረተው። ሚሞሪ ፎም ስንተኛ የሰውነትን ቅርጽ ይዞ ስንነሳ ወደ ነበረበት መመለስ የሚችል ፍራሽ ነው።
'ስሊፕ ነምበር ቤድ' የሚባልም ባልና ሚስት አልጋቸውን ሳይለዩ ለየራሳቸው የሰውነት ቅርጽ በሚመቻቸው መልኩ ማስተካከል የሚችሉት ሳይንሳዊ ፍራሽም ተሰርቷል።
በኢትዮጵያ ለወገብ ህመም ተብለው የሚሸጡ ፍራሾችስ?
ዶ/ር ቴዎድሮስ እነዚህ ፍራሾች ሳይንሳዊ አይደሉም ይላሉ። "ሱቅ የተሰቀለን ልብስ በግምት አንስቶ ግባ ብሎ እንደመታገል ነው" ሲሉም በምሳሌ ያስረዳሉ።
"በሰለጠነው ዓለም 30 ደቂቃ ፍራሹ ላይ እረፍት ወስደን ነው ፍራሽ የምንገዛው" የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ አንዳንድ መሸጫዎች ውስጥ 'ፍራሾቹ ላይ መተኛት ክልክል ነው!' የሚልም ማስታወቂያ በመለጠፍ ምቾቱን ሞክሮ ለመግዛት የሚደረገውን ክልከላንም ተችተዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስ ትራስን በተመለከተም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው ያላቸው። ትራስ በጭንቅላታችን እና በአንገታችን ሥር መካከል ያለውን ክፍተት የሚሞላ መሆን አለበት ይላሉ።
ነገር ግን ሰዎች ትራሳቸውን በአግባቡ ሲጠቀሙበት አይስተዋልም።
በእርግጥ የሚመቸንንና ልካችንን ለማወቅ አዳጋች ነው። ገንዘባቸውን ትራስ በመግዛት የሚጨርሱም ጥቂት አይደሉም።
ይህንን ችግር ለመፍታትም ይመስላል በሰለጠነው ዓለም 'ዎተር ፒሎው' [በውሃ የሚሞላ ትራስ] የተሰራው። ይህ የውሃውን መጠን በመቀነስ ወይም በመጨመር ትራሱን በልክ ለማሳነስና ለማተለቅ ያስችላል።
በመሆኑም የምንጠቀመውን ትራስ ልክ ማወቅ እና በተገቢው መንገድ መጠቀም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይመክራሉ።
የአኗኗር ዘይቤያችን ምን ይምሰል?
የሰውነት ክብደታችንን መቆጣጠር ወሳኝ ነው። ይህን ማድረጋችን ከወገብ ብቻም ሳይሆን ከሌሎች በሽታዎችም ራሳችንን ለመጠበቅ ያስችለናል።
"በሰውነታችን ላይ አንድ ኪሎ በጨመርን ቁጥር በእያንዳንዱ ኪሎ አንዱ ጉልበታችን ላይ 4 ኪሎ ጫና ይፈጠራል" የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ የሰውነታችንን ክብደት መቆጣጠርን ቸል ልንለው እንደማይገባ ይመክራሉ።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን በአቅማችን ልክ እና ቀስ በቀስ በተደረገ የሰውነት ልምምድ መስራት ሌላኛው ነው። የውሃ ዋና እና በሳምንት ለአራት ወይም ለሦስት ቀናት ለ45 ደቂቃ ያህል በእግር ፈጠን ያለ እርምጃ መሄድም ጥሩ ነው።
የሥራ ሁኔታን ምቹ ማድረግም አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም። ቆመው የሚሰሩ ሰዎች እቃ ሲያነሱ እንዴት መጠንቀቅ እንዳለባቸው ማወቅ፣ የሚመች ጫማ ማድረግ እንዲሁም ብዙ የሚቆሙ ሰዎች አንድ እግራቸውን አንድ ነገር ላይ አሳርፈው (ሰቅለው) መቆም ለወገብ ህመም የመጋለጥ እድላቸውን ይቀንሳል።
ከዚህም ባሻገር የወገብ ህመም መንስዔ ከሆኑ ድርጊቶች ራስን መጠበቅ እንደሚገባ ዶ/ር ቴዎድሮስ ይመክራሉ።












