ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ሰው ኩላሊቱን እየታመመ ያለው ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኩላሊት ታማሚ የበዛ ይመስላል። በቅርብ የምናውቃቸው ሰዎችም የኩላሊት ህመም እንዳጋጠማቸውና ህክምና እደሚያስፈልጋቸው ወይም ህክምና እየተከታተሉ እንደሆነ እንሰማለን።
ምን አዲስ ነገር ተፈጥሮ ይሆን?
ይህን ቁልፍ ጥያቄ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንመለስበታለን።
ለዛሬ በኩላሊትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ዶ/ር ፍጹም ጥላሁንን ነው። ዶ/ር ፍጹም ነዋሪነታቸው በአሜሪካን አገር ሲሆን የኩላሊት ሕክምና ከፍተኛ ስፔሻሊስት ናቸው።
ከመሠረታዊ ነገር እንነሳ። የኩላሊትን ተግባር በአጭሩ እናውሳ።
ኩላሊት የተፈጠረው ለምንድነው?
ይህን ነጥብ አጭርና ቀላል አድርገው የሚነግሩን ዶ/ር ፍጹም የኩላሊት ዋናው ተግባር በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ተስተካክሎት መጠበቅ ነው ይላሉ።
ምን ማለት ይሆን?
ተስተካክሎት ማለት ሆሚዮስታሲስ "Homeostasis" የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል የሚወክል ነው።
"ብዙ ሰው ኩላሊትን ሲያስብ ሽንት ነው ትዝ የሚለው" የሚሉት ዶ/ር ፍጹም ኩላሊት ግን ከዚያ ባሻገር ብዙ ተግባራት አሉት ይላሉ።
ለምሳሌ በሰውነታችን ውስጥ የሆርሞን ምርት፣ የንጥረ ነገሮች ምርትና ምጣኔ፣ የሰውነት ፈሳሽን ምጣኔ እና ሌሎች በርካታ ተግባራት በኩላሊት አማካይነት የሚፈጸሙ ናቸው።
ታዲያ ኩላሊት ይህን የተስተካክሎት ሥራ ለመሥራት ተፍ ተፍ በሚልበት ጊዜ የሚከሰትን ተረፈ ምርት "ሽንት" ብለን እንጠራዋለን።
በአጭሩ ኩላሊት የሰውነታችን ሚዛን ጠባቂ ነው።
በተስተካክሎት የሥራ ሂደት ውስጥ የሚፈጠረው ተረፈ ምርት ምድነው አለን? ሽንት።
በሌላ መልኩ ሂደቱ ሲተነተን ይህን ይመስላል።
ተመገብን። ምግብ ኃይል ሆነ፣ ህዋሳት የሚያስፈልጋቸውን ያህል ወሰዱ፤ ኩላሊት የቀረው ተረፈ ምርት በአንድ መልኩ ይሰበስብና ማጣሪያዎቹን ተጠቅሞ ወደ ማስወገጃ ክፍል ይልካል።
ተረፈ ምርቱ በኩላሊት ሚሊዮን ወንፊቶች በኩል ተጣርቶ ያልፍና ከፈሳሽ ጋር ወደ ፊኛ ክፍል ይላካል።
እዚያ ከሌሎች ፈሳሾች ጋር ተደባልቆ ሲወጣ ጊዜ ሽንት ሸናን እናላለን።
ኩላሊት ሌላ ሥራ አለው?
ጎንና ጎናችን ሥር የተሸጎጡት ሁለቱ ኩላሊቶቻችን የባቄላ ቅርጽ ነው ያላቸው።
በመጠን ደግሞ የኮምፒውተር "ማውዝ" ያክላሉ።
ከታችኛው የጎድን አጥንቶቻችን ውሸቅ ብለው በግራና በቀኝ ጎናችን የሚገኙ ጉደኛ ፍጥረቶች ናቸው።
ፈሳሽ ከማመጣጠን እና ተረፈ ምርት ከማስወገድ ሌላ ኩላሊት ብዙ የምርት ክፍሎች አሉት።
ለምሳሌ ቫይታሚኖችን ማምረቻ ክፍል አለው። ሆርሞን ማምረቻ ክፍልም አለው።
ካልሺየምና ፎስፌት የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን ማምረትና ምጣኔያቸውን የመቆጣጠር ሥራም ይሠራል።
የአጥንት ጤና ክትትል ኃላፊነት የተጣለውም በኩላሊት ነው ማለት ይቻላል።
በአጠቃላይ ኩላሊት፣ የንጥረ ነገር ሚዛን ማስተካከል፤ ተረፈ ምርት ማስወገድ፣ የደም ማነስ ችግር እንዳይኖር ክትትል ማድረግ፣ የደም ግፊትና የስኳር መጠንም በተዘዋዋሪ የመቆጣጠር ብርቱ ሥራ የሚሠራ እጅግ ጠቃሚ ክፍል ነው።
ኩላሊት የደም ማጥራት ሥራ ይሠራል እንዴ?
ኩላሊት ባተሌ ነው ብለናል። ፋታ የለውም ብለናል። ቀን ተሌት ይደክማል ብለናል።
ልክ 24 ሰዓት የሚሠራ ላውንደሪ ማሽን አድርጋችሁ አስቡት።
ለምሳሌ በያንዳንዱ ኩላሊት ውስጥ በየ30 ደቂቃ ውስጥ ሙሉ ደማችን አንድ ዙር ይታጠባል።
በየ30 ደቂቃው ሰውነታችን ውስጥ ያለ ሙሉ ደም አጠባ ይገባል። የደም ላቪያጆ ልንለው እንችላለን።
ተረፈ ምርት የሚያስወግደው በዚህ የአጠባ ሂደት ነው።
በ30 ደቂቃ ስንት ሊትር ደም ይሆን የሚታጠበው? በ30 ደቂቃ 5 ሊትር ደም ይታጠባል።
ያለ እረፍት 24 ሰዓት ይሄን ሥራ መሥራት እጅግ ከባድ ነው።
ዶ/ር ፍጹም እንደሚሊት፣ ልባችን ከሚረጨው ደም ውስጥ 20 ከመቶ በቀጥታ ወደ ኩላሊታችን የሚሄደው ያለ ምክንያት አይደለም። ኩላሊት ከባድ ሥራ ስለሚሠራ ነው። ደም ይፈልጋል።
በሙሉ ሰውነታችን ከሚዞረው ደም 20 ከመቶ በቀጥታ ወደ ኩላሊት የመሄዱ ነገር የኩላሊትን ባተሌነትን ይጠቁማል።
ኩላሊት ስለመታመማችን የሚጠቁም ምልክት አለ?
ዶ/ር ፍጹም አጭር መልስ ሲሰጡ "በብዛት ምልክት የለም" ይላሉ።
ብዙ ጊዜ ጽኑ የኩላሊት ህመም ካልሆነ በስተቀር በጠቅላላው ኩላሊት ምልክት አያሳይም።
ኩላሊት ባህሪው ጥሩ አይደለም። ሕመሙን ስለማይናገር ሰዎችን ያልታሰበ ጣጣ ውስጥ ይከታል።
"ህመም አልተሰማኝም ብሎ ኩላሊቴ ጤነኛ ነው ማለት አይቻልም" ይላሉ ዶ/ር ፍጹም።
ታዲያ መታመማችን ልናውቅ የምንችለው እንዴት ነው?
ዶ/ር ፍጹም ቀላል የደምና ሽንት ምርመራ ሁሉን ይነግረናል ይላሉ።
የመደበኛ ኩላሊት ህመም ምልክት አልባ ነው አላልንም?
ለዚህም ይሆናል፣ እጅግ በርካታ ሰዎች ኩላሊታቸው መታመሙን የሚያውቁት ለሌላ በሽታ ሕክምና ሆስፒታል ሲመጡ ብቻ የሚሆነው።
ሥር የሰደደ ወይም ጽኑ የኩላሊት ህመም ደረጃ ላይ ሲደረስ ግን ኩላሊት በጎ እንዳልሆነ በምልክቶች ማየት ይቻላል።
ለምሳሌ እግራችን ሊያብጥ ይችላል። ጠዋት ጠዋት ስንነሳ ዓይናችን ይወፍራል፤ ፊታችን ተነፋፍቶ ልናገኘው እንችላለን።
ቶሎ ይደክመኛል፣ ይጫጫነኛል፣ እግሬ ያብጣል ልንል እንችላለን። የአጥንት መሳሳት ሊኖርም ይችላል።
ይህ የሚሆነው ብዙውን ጊዜ ኩላሊት ፈሳሽ ማመጣጠን ሥራው ስለተስተጓጎለ ነው።
ይህ የሚሆነው ፈሳሽ ከመውጣት ይልቅ በሰውነታችን ስለሚጠራቀም ነው።
የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ የድካምና የማቅለሽለሽ ስሜትም ሊታይ ይችላል።
ደም ግፊታችን መጨመር ሊኖር ይችላል። የደም ማነስ ምልክትም ሊኖር ይችላል።
እነዚህ ምልክቶች ከታዩ ኩላሊት የከፋ ደረጃ እየደረሰ ነው ማለት ነው።
ዶ/ር ፍጹም ኩላሊት በብዛት ምልክት አልባ እንደሆነ ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ "እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገር ይቅርና እዚህ አሜሪካ ራሱ ወደ 40 ከመቶ የሚደርሱት ታማሚዎች ኩላሊታቸው የከፋ ደረጃ ሲደርስ እንጂ ከዚያ በፊት ሕመሙ እንዳለባቸው ፈጽሞ አያውቁም።"
ለዚህ ዋናው ምክንያት ኩላሊት ዝምተኛ መሆኑ ነው። በብዛት ምልክት አያሳይም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኩላሊት ህመም ምልክት ካላሳየ መታመማችንን እንዴት እንወቅ?
ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ዶ/ር ፍጹምም እንዳመላከቱት፣ የኩላሊትን ጤንነት በጣም በቀላሉ በደምና በሽንት ምርመራ ቶሎ ማወቅ ይቻላል።
ችግሩ ካልታመምን ሐኪም ዘንድ ስለማንሄድ ነው።
እውነት ነው። ኩላሊት ዝምተኛ ነው። ወዲያው አክሙኝ አይልም። ይህ ሁኔታው ያዘናጋል።
ስለዚህ አቅሙ ያለው ሰው ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ኩላሊቱን ቢታይ ጥሩ ነው ይላሉ ዶ/ር ፍጹም።
"እርግጥ ነው ሁሉም ሰው ዛሬውኑ ተነስቶ ልመርመር ቢል በሕክምና መዋቅሩ ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል።"
ነገር ግን ለምሳሌ የደም ግፊት ያለበት ሰው፣ ስኳር ያለበት ሰው፣ ቅጥ ያጣ ውፍረት ችግር ያለበት ሰው፣ ሌላ ተጓዳኝ ህመም ያለበት ሰው፣ ከሌላው ሰው ይልቅ ለኩላሊት ህመም ተጋላጭ መሆኑን መጠርጠር አለበት።
እነዚህ ሰዎች ኩላሊታቸውን ባይታመሙ ራሱ ቶሎ ቢታዩት ጥሩ ነው ይላሉ ዶ/ር ፍጹም።
ሌሎች ጤነኛ ነን የሚሉ ሰዎች ደግሞ ምንም ዓይነት ምልክት ባያሳዩም፣ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ ሆን ብሎ ኩላሊትን መመርመር እጅግ ጠቃሚ ነው።
አለበለዚያ ኩላሊታችን ብዙ ከተጎዳ በኋላ ዘግይተን ነው መታመሙን የምንረዳው። ያ ደግሞ ሕክምናውን ከባድ ያደርገዋል።
ሽንት ለረዥም ሰዓት መቋጠር ለኩላሊት በሽታ ያጋልጣል?
ልጆች ሳለን ጨዋታ ይዞን፣ በተለምዶ ሽንት ስንቋጥር፣ "ኩላሊት ትታመማላችሁ!" እንባል ነበር።
ይሄ ነገር እውነት ይሆን? ለመሆኑ ሳይንስ ያውቀዋል?
ዶ/ር ፍጹም፣ "አዎ ያውቀዋል" ብለውናል።
ሽንታችን መጥቶ በጊዜው የማንሸና ከሆነ በገዛ እጃችን ችግር እየፈጠርን ነው።
ኩላሊት የሚያጣራው ፈሳሽ ወደ ፊኛችን ተወስዶ ከተጠራቀመ በኋላ ነው ሸንት ሆኖ የሚወገደው።
ሽንቱን ለረዥም ጊዜ ይዘነው የምንቆይ ከሆነ ማጠራቂሚያ ላይ ባክቴሪያ እንፈጥራለን።
ወይም ከኩላሊት ወደ ማጠራቀሚ ፊኛ የሚወስደው ትቦ ላይ ኢንፌክሽን ይፈጠራል። ቀጥሎ ደግሞ ኩላሊት ላይ ኢንፌክሽን ይፈጠራል።
በአጠቃላይ ሽንት ስንቋጥር ኩላሊት ላይ አላስፈላጊ ጫና እንፈጥራለን።
ጫናው እየበዛ ሲሄድ ደግሞ የኩላሊት መድከምንም ሊያመጣ ይችላል።
ይሄን ሽንት መቋጠርን በየጊዜው የምናዘወትረው ልማድ ከሆነ መጥፎ ነው። ቆይቶ፣ ቆይቶ የኩላሊት ህመም ይዞብን ሊመጣ ይችላል።
ዶ/ር ፍጹም እንደሚያስረዱት ለዚህ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በተለይ ነገሩን ሊያስቡበት ይገባል ይላሉ።
ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች በሥራ ባህሪያቸው የተነሳ ቶሎ ቶሎ መሽናት ላይችሉ ይችላሉ።
የአውቶቡስና የታክሲ ሾፌሮችን በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ። እነዚህ ሰዎች በየጊዜው ከመኪና ወርደው መሽናት ይቸገራሉ።
በኋላ እሸናለሁ ብለው ይዘውት ሲቆዩ ለብዙ አደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ።
አንዱ ቀደም ሲል እንዳልነው፣ በሽንት ማጠራቀሚያ ፊኛ ውስጥ ባክቴሪያ እንዲራባ ዕድል ይከፍታል።
ለኩላሊት ኢንፌክሽን ሊጋለጡም ይችላሉ። እና ሽንትን በተቻለ አቅም ቶሎ መሽናት ጥሩ ነው።
ፕሮቲን መመገብ ለኩላሊት ህመም ያጋልጣል?
የከፋ የኩላሊት ህመም ሲኖር የሚመከሩ የአመጋገም ዓይነቶች አሉ። ምክሩ መምጣት ያለበት ግን ከሐኪም ነው።
በደፈናው ፕሮቲን ለኩላሊት ጥሩ አይደለም የሚባለው ነገር ግን ትክክል አይደለም ይላሉ ዶ/ር ፍጹም።
ከፍ ያለ ፕሮቲን ያላቸው እንደ ዕንቁላል፣ ቦሎቄ፣ ቀይ ሥጋ አትብሉ የሚባለው ነገር የተሳሳተ ነው።
ምክንያቱም አንድ ሰው ፕሮቲን በማጣቱ ብዙ ጉዳት ላይ ራሱን ይጥላል።
ሰዎች የኩላሊት ህመም ሲኖራቸው እንዲያውም ተገቢውን የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ነው የሚኖርባቸው የሚሉት ዶ/ር ፍጹም ሐኪማቸው መርጦ እነዚህን ምግቦች አትመገቡ እስካላላ ድረስ በደፈናው ፕሮቲን ለኩላሊት መጥፎ ነው ብሎ ፕሮቲን ከመመገብ መታቀብ ስህተት ነው ይላሉ።
"እንቁላል፣ የሥጋ ተዋጽኦዎች አትብሉ እየተባለ ድሮ ምክር ይሰጥ ነበር። እሱ ምክር ትክክል አይደለም። የፕሮቲን መጠኑ መገደብ ካለበት ሐኪም ያንን ሊገልጽ ይችላል።"
ሽንታችን ቢጫ ከሆነ አሳሳቢ ነው?
ዶ/ር ፍጹም በዚህ ረገድ ስጋት ሊገባን አይገባም ካሉ በኋላ፣ ነገር ግን የሽንት በጣም ቢጫ መሆን የኩላሊት ችግር ምልክት የሚሆንበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማሉ።
"የሽንት ቀለም መቀየር በተወሰነ መልኩ የኩላሊትን ህመምን የሚያመላክትበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ቀይ ሲሆን ደም ውስጡ አለ ማለት ነው።"
ይህ ደግሞ የቀለም መቀየሩ ከየት መጣ ብሎ ቶሎ ወደ ህክምና መሄድ እንዳለብን የሚጠቁም ነው። የሌሎች የጤና እክሎች ምልክት ሊሆንም ይችላል።
ሽንት ቢጫ ነው። በደንብ ውሃ የምንጠጣ ከሆነ፣ በቂ ፈሳሽ ከወሰድን ደግሞ ነጣ እያለ ይመጣል።
ፈሳሽ በበቂ የማንወስድ ከሆነ ደግሞ ጠቆር ያለ ቢጫ ሊሆን ይችላል።
ዶ/ር ፍጹም እንደሚሉት የቀለሙ መቀያየር የሚጠቁመን ፈሳሽ በበቂ እየወሰድን ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ነው።
"ሁልጊዜ ጠቆር ያለ ቢጫ ቀለም ያለው ሽንት የምንሸና ከሆነ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን 'በቂ ውሃ እየጠጣን ነው ወይ?' የሚለውን ነው።"
ሽንታችን ሽታው ጠንከር ካለ ኩላሊት ታመናል ማለት ነው?
ከምንሸናው ሽንት የሚመጣው ጠረን ከወትሮው የተለየ ከሆነና ጠንከር ካለ ምናልባት የአንዳች ኢንፌክሽን ምልክት ስለሚሆን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል።
በተለይ ሴቶች በዚህ ረገድ ለኢንፌክሽን ስለሚጋለጡ ሽታውን በተለየ ትኩረት ሊያጤኑት ይገባል ይላሉ ዶ/ር ፍጹም።
ውሃ አይጠማኝም፤ ኩላሊቴ ላይ ችግር ያመጣል?
ውሃ የማይጠማቸው ሰዎች አሉ። ስለዚህ በቃ ካልተገደዱ አይጠጡም።
በሌላ አንጻር ደግሞ ውሃ አብዝተው የሚጠጡ ሰዎች አሉ። ኧረ ውሃ ማብዛት ጥሩ አይደለም ይላሉ አንዳንድ ሰዎች።
ዶ/ር ፍጹም ግን ይህን አይቀበሉትም።
"ብዙ ሰው ውሃ ባለመጠጣት ይታመም ይሆናል እንጂ ብዙ ውሃ በመጠጣቱ ችግር ላይ የሚወድቅ ሰው እምብዛም ነው" ይላሉ።
ዞሮ ዞሮ በአማካይ በቀን ምን ያህል ውሃ ነው መጠጣት ያለብን?
ዶ/ር ፍጹም ከ2 እስከ 3 ሊትር ውሃ ብንጠጣ ይመክራሉ።
ይህን መጠን በአንድ ጊዜ መጠጣት ላይኖርብን ይችላል።
እንደ አመጋገባችንና አዋዋላችን አጠጣታችንም ሊለያይ ይችላል።
ዞሮ ዞሮ ነጥቡ ሰውነታችን ለሥራ ማስኬጃ የሚያስፈልገውን የውሃ መጠን ከማወቃችን ላይ ነው።
"በአጠቃላይ በቀን ውስጥ ከ2 አስከ 3 ሊትር ንጹህ ውሃ ብንጠጣ ግን በጣም አሪፍ ነው" ይላሉ ዶ/ር ፍጹም።
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በቂ ውሃ እየጠጣን ስለመሆኑ አንዱ የምናውቅበት መንገድ የሽንታችን ቀለም ራሱ ነጣ ያለ ሲሆን ነው።
ይህ ቀለም ውሃ በበቂ እየጠጣን እንደሆነ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, SPL
ብዙም ውሃ የማይጠጡ ሰዎች ታዲያ ምን ያድርጉ?
ውሃ አይጠጣልኝም የሚሉትን ሰዎች በተመለከተ ዶ/ር ፍጹም የልምድ ጉዳይ ነው ይላሉ።
"ውሃ መጠጣት እንደማንኛውም ነገር ልምድ ነው። በአንድ ጊዜ ተነስተን 3 ሊትር ልንጋት አንችልም። ቀስ በቀስ ሰውነታችንን ካለማመድነው ግን ውሃ መጠጣት ልምዳችን ይሆናል። ሰውነታችንም መቀበል ይጀምራል" ይላሉ።
ዛሬ በቀን አንድ ብርጭቆ ከጠጣን፣ የዛሬ ሳምንት ደግሞ ሁለት ብርጭቆ እንደዚህ እያልን ቀስ በቀስ መለማመድ ነው የሚኖርብን።
ይህን ማድረግ ራሱ በጣም አስቸጋሪ የሚሆንባቸው፣ በፍጹም ውሃ መጠጣት የማይሆንላቸው ሰዎችስ ምን ያድርጉ?
እነዚህ ሰዎች ትንሽ ጣዕም ያለው የተበረዘ ውሃ እየጠጡ ሊለማመዱ ይችላሉ ይላሉ ዶ/ር ፍጹም።
ለምሳሌ እንደ አምቦ ዓይነት የማዕድን ውሃ ሊጠጡ ይችላሉ።
ጣዕም ያላቸው ውሃዎች ግን በውስጣቸው ስኳር መኖር የለበትም።
የኩላሊት ህመምተኞች ብዛት የጨመረው ለምንድን ነው?
በአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኩላሊት ህመምተኞች ይታያሉ።
በቤተሰብ፣ በጓደኛ ደረጃ በቅርብ የምናውቃቸውም የኩላሊት ታማሚዎች በዝተዋል።
ምን አዲስ ነገር ተከስቶ ይሆን እንዲህ ኩላሊት ህመም የተስፋፋው?
ሰፊ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ቢሆንም ሁለት ምክንያቶች እንዳሉ ነው የምገምተው ይላሉ ዶ/ር ፍጹም።
አንዱ የአኗኗር ዘይቤያችን መቀየሩ ሊሆን ይችላል።
"አብዛኛው ሰው ወደ ከተማ ገብቶ መኖር ጀምሯል። ቢሮ ነው የሚሠራው፤ ቢሮ ስንቀመጥ እንቅስቃሴ ይቀንሳል። ይህ ደግሞ የሰውነት ክብደት እንዲጨምር ያደርጋል።"
የሰውነት ክብደት ሲጨምር የስኳርና የደም ግፊት በሽተኞችም እየጨመሩ ይመጣሉ።
እነዚህ ደግሞ በዋናነት የኩላሊት በሽታን የሚያመጡ ነገሮች ናቸው።
የከተሜ የአኗኗር ዘይቤ መበርከት አንዱ ምክንያት ከሆነ ሌሎች ምክንያቶች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
ምናልባት የኩላሊት ህመም ታማሚ በዝቶ የታየን ምርመራ በመስፋፋቱ ምክንያትም ሊሆን ይችላል ብለው ይጠረጥራሉ ዶ/ር ፍጹም።
"በፊት ሰው 'ታመመና ሞተ' ይባላል እንጂ በምን ሞተ? የሚለው ጥያቄ አልነበረም። ወይም መልስ አልነበረመው። አሁን ግን ምርመራ ስላለ ሰዎች በኩላሊት ህመም መሞታቸውን በስፋት ማወቅ ጀምረን ሊሆን ይችላል።"
ዶ/ር ፍጹም አንድ ሌላ መላምት አድርገው የሚያስቀምጡት የምርመራ አቅም መጨመር ነው።
ለምሳሌ በፊት የኩላሊት ዕጥበት (ዳያሊሲስ) አይታወቅም ነበር። የታመመ ሰው ይሞታል። አሁን በኩላሊት ዕጥበት ላይ ያሉ ብዙ ሰዎችን እናውቃለን።
ይህም ኩላሊት ህመም የበዛ እንደሆነ እንዲሰማን አድርጎም ይሆናል።
መድኃኒት በብዛት እየቃምን መሆኑ ኩላሊት ታማሚን አብዝቶብን ይሆን?
ዶ/ር ፍጹም ይህ ነገር በብርቱ ያሳስባቸዋል።
"በተለይ ትልቁ ችግር በእኛ አገር ሐኪም ሳይሆን በሽተኛው ራሱ ነው ለራሱ መድኃኒት የሚያዘው" ይላሉ።
ይህ እንዴት ችግር እንደሆነ ሲያብራሩ ብዙ ሰው የኩላሊት ህመም እንዳለበት አለማወቁን ያነሳሉ።
ሰዎች ሌላ ህመም ሲታመሙ ነው ኩላሊት የሚመረመሩት። እስከዚያ ድረስ ግን ጤነኛ ኩላሊት እንዳላቸው ነው የሚገምቱት።
በዚህ ሁኔታ ላይ ሳሉ ታዲያ እንደልባቸው መድኃኒት ይወስዳሉ።
ለሌላ በሽታ መድኃኒት ሲወስዱ የኩላሊታቸው ጤና ስለማይታወቅ የመድኃኒት ምጣኔ ሳይሠራላቸው መድኃኒት ይወስዳሉ።
ያለ ኩላሊት ምርመራ መድኃኒት በፈቃዳችን ስንወስድ ደግሞ ኩላሊት ላይ ጫና ይፈጠራል።
"ስለዚህ በእኛ አገር ሁኔታ መጀመሪያ ማስቆም ያለብን ሐኪም ሳያዝ መድኃኒት መውሰድን ነው" ይላሉ።
ሁለተኛ በብዛት ገበያ ላይ ካሉ መድኃኒቶች ውስጥ ሰው በራሱ ተነሳስቶ የሚወስዳቸው የራስ ምታት፣ የቀርጥማት ማስታገሻ መድኃኒቶች ችግር እየሆኑ መጥተዋል።
እነዚህን መድኃኒቶች ሰው ዝም ብሎ ነው የሚገዛቸው። መድኃኒቶቹ ተደጋግመው በሚወሰዱበት ጊዜ ኩላሊታችን ላይ ጫና ይፈጥሩበታል።
የጨጓራ መድኃኒቶችም ተመሳሳይ ችግር ኩላሊት ላይ ይፈጥራሉ።
ያለ ሐኪም ትዕዘዝ የምንወስዳቸው ከሆነ በተለይ ኩላሊታችን ሊጎዱ ይችላሉ።
መድኃኒትን ሐኪም ሲያዝልን ብቻ ብንወስድ ጥሩ ነው።
ለምን ከተባለ አንደኛ ሐኪማችን ትክክለኛውን መጠን ይነግረናል።
ሁለተኛ ደግሞ የኩላሊታችንን ሁኔታ መርምሮ መውሰድ የሌለብንን መድኃኒት ያሳውቀናል።
ዶ/ር ፍጹም እንደሚሉት በተለይ የህመም ማስታገሻ መድኃኒቶች በቀላሉ ተገኙ ተብሎ በየጊዜው እያነሱ መቃም አደጋ አለው።
ታዲያ ኩላሊታችንን እንዴት እንንከባከበው?
ቁልፍ ተግባራትን የሚያከናውነው ባተሌው ኩላሊት አንድ ጊዜ ከታመመ ብዙ ጣጣ ይዞ ይመጣል።
ብዙ ነገሮች ይስተጓጎላሉ። ብዙ ነገሮች ይወሳሰቡብናል።
ምን ተሻለ ታዲያ ሲባሉ ዶ/ር ፍጹም አጭር ምክር ሰጥተው ያልፋሉ።
ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን መከተል፣ እና ደግሞ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የኩላሊት ምርመራ ማድረግ።
"ኩላሊታችንን አልታመምንም ማለት ኩላሊታችን ጤነኛ ነው ማለት አይደለም።"














