“እስክሞት ልታገል”፡ የኩላሊት ህሙማን መርጃ ያቋቋመው የኩላሊት ታማሚ

የፎቶው ባለመብት, Eyob
የህክምና ምርመራ ውጤት! ሕይወታችንን ባላሰብነው፣ ባልጠበቅነው መንገድ ይገለባብጣል።
ለኢዮብ ተወልደመድኅን ያ ክፉ ጊዜ ጥቅምት 2006 ዓ.ም ነበር። የኩላሊት ታማሚ እንደሆነ ሐኪሞች ሲገሩት።
የሁለት ሴት ልጆች አባት የሆነው ኢዮብ ይህን ዜና ሲሰማ የሚገባበት ጠፋው። ባለቤቱ በድንጋጤ ከፍተኛ ሐዘን ተጫናት።
አዲስ አበባ ውስጥ የተክለሐይማኖት ሰፈር ልጅ ነው። ከ1979 ዓ. ም. ጀምሮ ግን ለአምስት ዓመታት አሰበ ተፈሪ ኖሯል።
ዘጠነኛ ክፍልን አብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት ተምሮ 10ኛ ክፍል ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት በማታ ፈረቃ ገባ። የግድ ታናናሾቹን ማሳደግ ስለነበረበት ከ11ኛ ክፍል በላይ መቀጠል አልቻለም።
ትምህርቱን አቋርጦ እንጨት ሥራ ያዘ።
በእንጨትና አልሙንየም ሥራ ተቀጥሮ ለሦስት ዓመታት ሠራ። ጥሩ ገቢ ያገኝ ስለነበር ታናናሽ ወንድሞቹን፣ እናትና አባቱንም ያስተዳድር ጀመር።
1991 ዓ.ም. ላይ ከብድርና ቁጠባ ተቋም አነስተኛ ገንዘብ ተበድሮ ቤቱ የእንጨት ሥራ ከፈተ። ገቢው እያደገ መጣ።
ንግዱ ሲጦፍ ከመንግሥት ቦታ ወስዶ እንጨት ሥራውን አስፋፋ። በልደታ ክፍለ ከተማ በከፈተው እንጨት ቤት ሙያውን ያስተምርም ነበር።
ጥቅምት 2006 ዓ.ም. ላይ የኩላሊት ህመም አለብህ ሲባል ግን ነገሮች መስመር ሳቱ።
ሥራውን ወዲያው አላቋረጠም። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከበደው መምጣቱ ግን አልቀረም።
ከታመመ ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከጥቃቅንና መካከለኛ የንግድ ሰዎች አንዱ ብሎ ሸልሞታል።
የኩላሊት ህመም አቅም ይነሳል። አካልን፣ ሥነ ልቦናን፣ ቤተሰብን፣ ጓደኛን፣ ሥራን ይፈትናል። ኢዮብ የገጠመውም ይኸው ነው።
የኩላሊት ህክምና እድሜ ልክ የሚወስድ፣ ገንዘብንም የሚያሟጥጥ እንደሆነ ሲገነዘብ የባለቤቱና የሕጻናት ልጆቹ እጣ ፈንታ እንቅልፍ ነሳው።
ቤተሰቤን ድሃ አድርጌ ከምሞት ምነው እኔው ቀድሜ ብሞት ሲል ያስብ እንደነበር ይናገራል።
በአንድ ወር ውስጥ የኩላሊት እጥበት [ዳያለሲስ] ካላደረገ እንደሚሞት ሲነገረው ቤተሰቡና ጓደኞቹ ተረበሹ።
በአፋጣኝ ኮርያ ሆስፒታል ወስደውት የኩላሊት እጥበት ጀመረ። ህመሙም ጋብ አለለት።
ያኔ ሆስፒታሉ ውስጥ ያየው ነገር የሕይወት አቅጣጫውን እንዲቀይር እንዳደረገው ያስታውሳል።
"አቅም የሌለው፣ መካከለኛ ገቢ ያለው፣ ባለ ሀብት ታካሚም አለ። ልዩነቱ በግልጽ ይታያል። በርካቶች ህክምናውን ለማድረግ አቅም አልነበራቸውም። እኔ ታክሜ ነጻነት ሳገኝ ለምኖ ያልሞላለት ሰው ግን ምን ያህል ነጻነቱን ያጣል? ስል አሰብኩ።"
ለወራት የኩላሊት እጥበት ሲያደርግ የህክምናው ወጪ ከብዷቸው የሚያቋርጡ እንዳሉ ይሰማ ነበር። ወጪው ከአቅማቸው በላይ ሆኖ የሚሞቱትንም ቤቱ ይቁጠራቸው።

"እስክሞት ልታገል"
ኩላሊት መሥራት ሲያቆም የኩላሊት እጥበት ማድረግ ግዴታ ነው። ህመሙ የሌለባቸው ሰዎች ሰውነታቸው ውስጥ የሚከማች ቆሻሻን ሽንት በመሽናት ያስወግዳሉ።
ታማሚዎች የኩላሊት እጥበት ካላደረጉ ቆሻሻው አይወጣም ማለት ነው። እናም ሰውነታቸው ይታፈናል፣ ያብጣል፣ ሲከፋም ሕይወታቸውን ያጣሉ።
በሳምንት ሦስቴ የኩላሊት እጥበት ማድረግ የሚጠበቅበት ሰው በሳምንት አንዴ ብቻ ቢያደርግ ወይም ቢያቋርጥ ይህ መታፈን ይገጥመዋል። ምግብ መብላትም አይችልም።
ኢዮብ በህመሙ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎችን ሲያይ በቀረኝ ሕይወት የአቅሜን መርዳት አለብኝ ብሎ ወሰነ።

የፎቶው ባለመብት, Eyob
ህሙማን የገንዘብ እርዳታ የሚያገኙበት እና መንግሥት ከህመሙ ጋር በተያያዘ የሚያወጣቸው ውሳኔዎች ላይ ጫና ማሳደር የሚቻልበት ማኅበር አቋቋመ።
'ሞት በኩላሊት ይብቃ' የተጀመረው በ2007 ዓ.ም. ነው።
በታመመበት ጊዜ በመንግሥት ሆስፒታሎች ውስጥ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት አልነበረም። በግል ሆስፒታልም በውስን ቦታ፣ በውድ ገንዘብ ይከናወናል። ህክምናውን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት አሁንም ድረስ ከባድ ነው።
በመንግሥት ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት በአንድ ዙር 500 ብር ያስከፍላል። በግል ሆስፒታሎች ደግሞ ከ1500 እስከ 3500 ብር ያወጣል።
"መሞቴ አይቀርም እስክሞት ልታገል ብዬ ወሰንኩ። ለመንግሥት አካላት እና ለአንዳንድ ተቋማት ድምጼን ማሰማት ጀመርኩ። በመኪና እየዞሩ መቀስቀስ፣ ብሮሸር መለጠፍም ቀጠልኩ። ይኸው 8 ዓመት ኖርኩኝ። በጥቂት ቦታም ቢሆን በመንግሥት ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ተጀምሯል። ይሄ በኩራት የምናገረው የልፋቴ ውጤት ነው።"
ማኅበሩ ከምስረታው ጀምሮ ባለፉት ስምንት ዓመታት ከ120 በላይ ህሙማንን ደግፏል። ቁጥሩ ለቀን፣ ለሳምንት፣ ለአንድ ወር ወይም ለሁለት ወር የኩላሊት እጥበት ገንዘብ የሚከፈልላቸውን ይጨምራል።
ወርሀዊ መዋጮ በማድረግ እና በጉልበት ሥራ የሚደግፉ የማኅበሩ አባላት አሉ።
ደበበ እሸቱ፣ ስዩም ተፈራ፣ ዳንኤል ተገኝ ታዋቂ የማኅበሩ አባላት ናቸው። ኢዮብ "አምባሳደሮቻችን" ይላቸዋል።
ከ2007 ወዲህ ድጎማ ከተደረገላቸው ህሙማን መካከል አምስቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ሞት በኩላሊት ይብቃ
የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር በምኒሊክ እና በዘውዲቱ ሆስፒታሎች ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ለሁለት ዓመት ነጻ የኩላሊት እጥበት ከሚሰጣቸው 105 ህመምተኞች አንዱ ኢዮብ ነው።
ያቋቋመው ማኅበር ከያዛቸው ፕሮጀክቶች አንዱ የኩላሊት ህሙማን ተደራጅተው ሥራ እንዲሠሩ ከክፍለ ከተሞች ጋር መነጋገር ነው። ይህም ለህክምና ገንዘብ ሲሉ ጎዳና ወጥተው ለመለመን የተገደዱ ወገኖችን ለመደገፍ ያለመ ነው።
ፕሮጀክቱን የጤና ሚንስትር እና የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ድጋፍ ሰጥቶት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ለአንድ ህመምተኛ የሥራ እድል ተፈጥሯል። በሌሎች ክፍለ ከተሞችም እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ወጋገን ባንክ ለህመምተኞች መርጃ ገንዘብ የሚሰበሰብበት ሳጥን ተቀምጧል።
በቋሚነት በሳምንት ለአንድ ህመምተኛ የኩላሊት እጥበት ክፍያ የሚያደርጉ የማኅበሩ አባላት አሉ።
ማኅበሩ በሰበሰበው ገንዘብ ሦስት ህሙማን የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው ሲሆን፤ ነጻ ህክምና የሚያገኙ እንዳሉም ይናገራል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ የኩላሊት እጥበት ክፍያ ከፍተኛ ስለሆነ ከ70 እስከ 80 በመቶ ያሚሆነው የኩላሊት ህመምተኛ በሳምንት አንዴ ወይም ሁለት ቀን ነው የሚያደርገው" ይላል።
ማኅበሩ በሠራው ስሌት መሠረት አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ከ700 ያላነሱ የኩላሊት ህመምተኞች በግል ሆስፒታል ነው ህክምና የሚከታተሉት።
ዝቅተኛ የሚባለውን የአንድ ዙር የኩላሊት እጥበት ወጪ 1500 ብር መክፈል የሚችሉ ውስን ናቸው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጎዳና ላይና በየሐይማኖት ተቋማት ከመለመን ውጪም አማራጭ የለውም።

የፎቶው ባለመብት, Eyob
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የኢዮብ ማኅበር የመዋጮ ፕሮጀክት ቀርጿል።
ሐሳቡ በወር 10 ብር፣ በዓመት 120 ብር የሚያዋጡ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን በማኅበሩ አባልነት መመዝገብ ነው።
ፕሮጀክቱ ከሦስት ዓመት በፊት ሲጀመር ከከፍተኛ ባለሥልጣናት ጀምሮ፣ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎች ሰዎችን ጨምሮ ወደ 3000 ሰዎችን መመዝገብ ተችሏል።
ከአባላቱ የሚሰበሰበውን ገንዘብ የሚከታተል መተግበሪያ እያሠሩ ነው። ኢትዮ-ቴሌኮም አጭር የጽሑፍ መልዕክት (ኤስኤምኤስ) እየላከ ገንዘቡን ሰብስቦ በቀጥታ ወደ ጤና ሚንስትር እንዲያስገባ ለማድረግ ወጥነዋል።
አንድ ሚሊዮን ሰዎች በወር 10 ብር፣ በዓመት 120 ብር ቢያዋጡ፤ በአንድ ዓመት በአጠቃላይ 120 ሚሊዮን ብር ይገኛል። ይህም ለነጻ የኩላሊት ህክምና እንዲውል እንደሚፈልግ ኢዮብ ይናገራል።
"ይህ ገንዘብ በመሀል ምንም ሂደት ሳይኖር ከቴሌ ወደ ጤና ሚንስትር በቀጥታ ስለሚገባ ተአማኒነት ይኖረዋል" ይላል።
ከጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጋር በጉዳዩ ላይ ከስድስት ወር በፊት እንደተነጋገረ ይገልጻል።
"ሚንስትሯ በሐሳቡ ደስተኛ እንደሆኑና ለመደገፍ ፍቃደኛ እንደሆኑ ነግረውኛል። ገንዘቡ ከቴሌ ወደ ጤና ጥበቃ በቀጥታ እንዲገባ እንደምንፈልግ ስነግራቸው የሕግ አግባቡን ልይ ብለዋል።"
የቀድሞው የጤና ሚንስትር ዶ/ር አሚር አማን ሐሳቡን ደግፈው የአባልነት መታወቂያ አውጥተዋል።
የኢዮብ ውጥን ተሳክቶ በአንድ ዓመት 120 ሚሊዮን ብር ማግኘት ከተቻለ እስከ 500 ሰዎች ለዓመት በመንግሥት ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት በነጻ ያገኛሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እንዲደግፏቸው ለማድረግ መልዕክት እንደላኩና እስካሁን እንዳላገኟቸው የሚናገረው ኢዮብ በድጋሚ ጥያቄ እንደሚያቀርብላቸው ገልጿል።
ሐሳቡ እውን ከሆነ "መዋጮው ኪስ አይጎዳም። ብንኖርም ባንኖርም ቋሚና ቀጣይ ይሆናል። ጤናማው ሰው የሚያዋጣው ገንዘብ ወደ ኋላ መገልገያው እንዲሆን የጤና መድኅን አካል ማድረግም ይቻላል" ሲል ተስፋውን ይናገራል።
እንደ ኩላሊት፣ ካንሰር እና ልብ ያሉ ህመሞች ህክምና ሊሰጥባቸው እየተገባ ብዙዎች የሚሞቱባቸው ናቸው። ምናልባትም እንዲህ ባሉ የረድኤት ፕሮጀክቶች ችግሩን መቅረፍ ይቻላል ብሎ ያምናል።

"ባለቤቴ- ጀግናዬ"
ኢዮብ ከመታመሙ በፊት ለራሱና ለቤተሰቡ ሕይወት መለወጥ የሚተጋ ሰው ነበር። አሁን ግን የብዙዎችን ኃላፊነት ለመሸከም መርጧል።
የማኅበሩ መስራች፣ ሥራ አስኪያጅ ብቻ ሳይሆን ሹፌር፣ ቀስቃሽ፣ ገንዘብ ሰብሳቢ የሆነባቸውን ጊዜያት ያስታውሳል።
ሥራውን "ፈጣሪ እና ህሊናዬ የተደሰቱበት ስለሆነ ኩራት እና ደስታ ይሰማኛል" ሲል ይገልጸዋል።
ለስምንት ዓመታት የኩላሊት እጥበት ሲያደርግ ወገቡ እና እግሩ ላይ ጉዳት ስለደረሰበት በድጋፍ ነው የሚንቀሳቀሰው። እንደ ቀድሞው የማኅበሩን ሥራዎች እንዳያከናውንም አድርጎታል። ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰውነት ክብደቱ ከ56 ወደ 46 ኪሎ ቀንሷል።
ብርታት ከሚሰጡት በዋነኛነት የሚጠቅሰው "ጀግናዬ" የሚላት ባለቤቱን ነው።
"በጤናማነቴ ጊዜ ያፈራሁትን ከ1.5 ሚልዮን ብር በላይ ለማኅበሩ ሳውል ነገ ይሞታል ብላ ቅር አላላትም። ብር አንሶን የልጆቼን መኖርያ ቤት ስሸጥ እሷ የነበረንን ንግድ ቤት በመሸጥ ሹፌር ሆና ልጆቹን አስተማረች። ለዛሬ አብቅታኛለችና ጀግናዬ ናት።"
ሲታመም የሩቅና የቅርብ ቤተሰብ፣ ጓደኛም በአብዛኛው እንደሸሸው ይናገራል። ከልጆቹ ጋር ሰፊ ጊዜ ባለማሳለፉ፣ እንዳሻቸው ባለማዝናናቱም ያዝናል።
ከኩላሊት ታማሚዎች ጋር ስቴድየም ዙርያ፣ ባዛሮች ላይ እንዲሁም ወደ መንግሥትና የግል ተቋማት እየሄደ እርዳታ ለማሰባሰብ ይሞክራል።
ህክምናውን ትቶ የማኅበሩን ጉዳይ የሚከታተልባቸው ጊዜያትም አሉ።
የኩላሊት ህመም "ሳቄን፣ ደስታዬን፣ እግሬን አሳጥቶኛል" ይላል። ከዚህ በተቃራኒው "እውነተኛ ታጋይና ለወገን ቶርቋሪ አድርጎኛል" ሲል ያለበት ሁኔታ ይገልጻል።
በእሱ ማኅበር ውስጥ ይረዱ ከነበሩ ህሙማን መካከል ኋላ ላይ በራሳቸው ማኅበር መስርተው መንቀሳቀስ የጀመሩ ሰዎች መኖራቸው ያስደስተዋል።
ህሙማንን ሲረዳ ከሚያገኘው እፎይታ በተጨማሪ ቤተሰቡ ሐሴት ይሰጠዋል። "ሁሌም ሚስቴና ልጆቼ የተቃጠልኩትን ማቀዝቀዣዎቼ ናቸው" ይላቸዋል።
ሐኪሞች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማድረግ እንዳለበት ነግረውታል። ኩላሊት የሚሰጠው የቤተሰብ አባል ቢያገኝም የወጪው ነገር አሳሳቢ ነው።
የማኅበሩ ስኬት ከሚላቸው መካከል ብዙ ገንዘብ ባይኖራቸውም ለህሙማን ገንዘብ ለመለገስ የሚፈቅዱ ሰዎች ማግኘታቸውን ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎችን የሚያስደነግጥ ምስል ወይም የተጎዳ ሰው ቁስል ካልታየ በስተቀር በማኅበረሰቡ ዘንድ እምብዛም ሰዎችን የመርዳት ተነሳሽነት እንደሌለ አስተውሏል።
የተጎዱ ሰዎችን ለይቶ በቀጥታ የመርዳት ልማድ ባለመኖሩ ማኅበረሰቡ እርዳታ የሚሰጠው ባገኘው አጋጣሚ፣ በየመንገዱ ለሚያገኘው ገንዘብ ጠያቂ ነው። ይህም በእርዳታ ስም የሚያጭበረብሩ እንዲበራከቱ መንገድ እንደከፈተም ያምናል።
ሰዎች ባላቸው አቅም ተጎጂዎችን በእቅድ የመርዳት ባህል እንዲዳብሩ ይመኛል።

የኩላሊት ህክምና በኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ሕግ አንድ ሰው ኩላሊቱ መሥራት ካቆመ ከቤተሰቡ ውጪ ኩላሊት ከሌላ ሰው መውሰድ አይችልም ይላል።
ይህ ሕግ ቤተሰብ የሌላቸው ወይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር የደም አይነታቸው የማይመሳሰል ሰዎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ ጥሏል ይላል።
ዘመድ፣ አብሮ አደግ ወይም ሌላ ለጋሽ ኩላሊት የሚሰጥበት አሠራር እንዲዘረጋ ለጤና ሚንስቴር ማሳሰቡንም ኢዮብ ይናገራል።
ሌላው ክፍተት የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚከናወነው በጳውሎስ ሆስፒታል ብቻ መሆኑ ነው። ይህ አገልግሎት ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሳት ወዲህ መቋረጡም ሌላ ችግር ነው።
በሌላ በኩል ንቅለ ተከላ ያደረጉ ሰዎች የመድኃኒት እጥረት ይገጥማቸዋል። የኩላሊት እጥበት የሚያደርጉ ሰዎችም እንዲሁ ተጓዳኝ የሰውነት መጠገኛ መድኃኒቶች ያጣሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ መድኃኒቶቹን ማግኘት ከባድ ነው። ያሉትም በጣም ውድ ናቸው።
ኢዮብ ከታመመበት ከስምንት ዓመታት ወዲህ ብዙ ነገሮች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን አይክድም። "ትላንት የነበረውን ጨለማ ስለማውቀው የዛሬው የተሻለ ነው እላለሁ" ይላል።
ሆኖም ግን አሁንም ያሉ ክፍተቶች እንዲሸፈኑ ይጠይቃል።

የፎቶው ባለመብት, Eyob












