ኮሮናቫይረስ ተጓዳኝ ህመሞችን የቀሰቀሰባቸው ኢትዮጵያውያን ታሪክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መኖሩ ከተረጋገጠ ጀምሮ አስካሁን ድረስ 280 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 4,381 ግለሰቦች በወረርሽኙ ሳቢያ ለሞት ተዳርገዋል።
ወረርሽኙ በተለያየ ደረጃ አንድ ጊዜ ጠንከር ብሎ ሲስፋፋ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋብ ሲል ቆይቶ አሁን በሦስተኛ ዙር እየተዛመተ መሆኑን የኢትዮጵያ የጤና ባለሥልጣናት እየተናገሩ ነው።
በሽታው በዓለም ላይ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የቫይረሱ የተለያዩ ዝርያዎች በተለያዩ አገራት መከሰታቸው የተነገ ሲሆን ዴልታ የተባለውና በበርካታ አገራት የተስፋፋው ቫይረስ ግን ከሁሉ ጠንከር ያለ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ በጽኑ ከታመሙና ለሞት ከተዳረጉ ሰዎች መካከል ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው አሊያም በእድሜ የገፉ ሰዎች ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ከተለያዩ አገራት የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይ ተጓዳኝ ህመም ያለባቸው ሰዎች በቫይረሱ ከተያዙ በቀላሉ ለማገገም ይቸገራሉ። ነገር ግን በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች አገራት ውስጥ በበሽታው ከተያዙት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ማገገማቸውን በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በኮሮናቫይረስ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች ለሌሎች ተጓዳኝ ህመሞች የመጋለጣቸው ነገር አነጋጋሪ እየሆነ ነው። ከዚህ አንጻር እኛም ተመሳሳይ የጤና ችግር ከገጠማቸው ሰዎች የሁለት ኢትዮጵያውያንን ተሞክሮ አቅርበናል።
"ቀኑን ሙሉ ሳሸት፣ ስቀምስ ነው የዋልኩት"
አብርሃም [ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሙ የተቀየረ] ነዋሪነቱ አዲስ አበባ ነው። ባለ አንድ መኝታ ክፍል ኮንዶሚኒየም ተከራይቶ በቅርቡ ነው ብቻውን መኖር የጀመረው።
አብርሃም በቤተሰቡ ውስጥ ስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች በመኖራቸው ምክንያት ራሱን ለመጠበቅ ከፍ ያለ ጥረት ያደርጋል።
በዚህም በተደጋጋሚ በደሙ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን እየለካ ያለበትን ሁኔታ ይከታተላል።
"አይደለም ስኳር ሊኖርብኝ [ስለካ] የሚያሰጋ ቁጥር ኖሮኝ አያውቅም" ሲል ቀደም ሲል ነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።
የቅርብ ዘመዶቹ እና የሚስቱ አባት ስኳር ስላለባቸው "ለመጠንቀቅ ቀላል" እንደሆነለትም ይገልጻል።
"አመጋገቤ የተስተካከለ ነው። በተቻለኝ መጠን ስፖርት እሠራለሁ፣ ጣፋጭ ነገርም ብዙ አልጠቀምም" ይላል።
ባለፈው ታኅሣሥ ጠዋት ከእንቀልፉ ሲነቃ ጥሩ ስሜት አልነበረውም። ሊያመው እንደሆነ መንፈሱ አውቆታል። የጉንፋን ስሜት ቢኖረውም ሌላ ጊዜ የሚይዘው ጉንፋን ዓይነትም አልሆነም።
ማክሰኞ እና ረቡዕ አሞኛል ሲል ለአለቃው አሳውቆ ከሥራ ቀረ። ከቤት አልወጣም። አንዴ መጽሐፍ ሲያነብ አንዴ ደግሞ ፊልም ሲያይ አመሸ።
በሁለቱም ቀናት ግራ ያጋባው ስሜቱ ሄድ መለስ እያለ አብሮት ዘለቀ።
ሐሙስ ጠዋት ከተለመደው ከፍ ያለ ሙቀት ተሰማው፤ መገጣጠሚያዎቹን ያመው ጀመር። አሁን በዜና ብቻ የሰማው ኮሮናቫይረስ አጠገቡ የደረሰ መሰለው።
ልቡ ግን ያመነታል "አይ አልያዘኝም" ይላል። ቀጥሎ ደግሞ ምልክቱን ለማወቅ ስልኩን አውጥቶ ይጎለጉላል። "አይ አሁንስ ኮሮና ነው" ይላል።
"ኮሮና ነው አይደለም" ሲል መምሸት አይቀርም መሸ። እንቅልፍ የጣለው ለ30 ደቂቃ ገደማ ነበር። ከ30 ደቂቃ በኋላ ሲነሳ ሰውነቱ ከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ሆኖ ነው።
ይህን ለሰዓታት የዘለቀውን ሙቀት "በሕይወቴ የማላውቀው ነው ሲል" ይገልጸዋል።
አዲስ ሰፈር በመግባቱ ነው እንጂ ወደ አቅራቢያው ክሊኒክ ቢሄድ ምንኛ ደስ ባለው። "ቤተሰቦቼን ደውዬ ከማስጨንቅ ጓደኞቼ ጋር ብደውል ይሻላል" ሲል ራሱን ይጠይቃል። ከውሳኔም ሳይደርስ ሙቀቱ ትንሽ ቀዝቀዝ ሲልለት ወደ መኝታው ተመልሶ አቀና።
ጠዋት ወፍ ጭጭ ሳይል ነው ከእንቅልፉ የነቃው። ሙቀቱ ባይኖርም ሰውነቱ ደክሟል። ከደረቱ ላይ የማያቋርጥ ሳል ጀምሮታል።
ተነስቶ ፊቱን መታጠብ የሚችልም አልመሰለውም። እንደምንም ተነስቶ ታጠበ። ቁርሱን አዘጋጀ። ለመብላት ቢሞክርም እምቢ አለው።
በቀጥታ ወደ አካባቢው ጤና ጣቢያ በመሄድ ምልክቱን ተናግሮ የኮቪድ-19 ምርመራ አደረገ። በቀጥታ ወደ ቤቱ አመራ።
ማታ የነበረው ሙቀት ቢጠፋም የማያቋርጠው ሳል አንዳለ ነው። ከሳሉ ይልቅ ደረቱ ላይ የሚወጋ ህመም መኖሩ ይበልጥ አስጨንቆታል። አንዴ ግራ ደረቱን ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀኙ ሲብስ ደግሞ በሁለቱም ደረቱ በኩል ነበር ህመሙ።
"ከህመሙ የተነሳ ደሬትን ይዤ ነበር የምስለው" ይላል።
በሦስተኛው ቀን ኮሮናቫይረስ እንዳለበት ተነገረው። ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ቢኖረውም ሲነገረው ግን "የእውነት" አስጨነቀው።
ቀናት ባለፉ ቁጥር ሳሉም ድካሙም እየቀነሰ ሄደ። የምግብ ፍላጎቱ ግን ከዕለት ወደ ዕለት ቀነሰ።
"በግድ ነበር የምበላው። መብላት ስላለብኝ በግድ እበላለሁ እንጂ ሳልበላ ብውል እመርጥ ነበር" ይላል። በዚህ መልክ ከቫይረሱ ጋር የጀመረውን ግብግብ ከዕለት ወደ ዕለት ቀጠለ።
አብርሃም "ለራሴ በቂ ጊዜ ሰጥቻለሁ። በቫይረሱ ይሁን በሌላ ምክንያት ረዥም ሰዓት እተኛ ነበር። እሱም ያገዘኝ ይመስለኛል። ከሦስት እና አራት ቀናት በኋላ እየተሻለኝ መጣ" ሲል ያስታውሳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አምስተኛው ቀን ላይ ብቸኛው ያልጠፋው ምልክት ሳሉ ብቻ ነበር። ለቀናት የሚወደውን ቡና ማፍላት እንኳን የደከመው አቅሙ ተመልሶ ቡናውን መጠጣት ጀምሯል።
ኮሮናቫይረስ እንዳለበት ካወቀ ከቀናት በኋላ ሲታጠብ ሳሙናው አልሸት አለው።
ቫይረሱ ሽታ እና የመቅመስ ስሜትን እንደሚያሳጣ ስለሚያውቅ በፍጥነት ነበር ከመታጠቢያ ክፍሉ የወጣው።
ሽቶዎቹን ሞከረ፤ ምንም አይሸተውም። ይሸቱኛል ያላቸውን ነገሮች በሙሉ እየቀያየረ ሞከረ- ምንም የለም። አንዱ ሽቶ ብቻ "የሚሰነፍጥ ጋዝ ስሜት ፈጠረብኝ" ይላል።
ጥርጣሬው ጨመረ። የሚወደው ቡናም ምላሱ ላይ ሲያርፍ ምንም አልመሰለው።
በድጋሚ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርጎ ቫይረሱ እንደሌለበት አረጋግጧል። "ማሽተት እና መቅመስ እንዳልቻልኩ የነገርኳቸው ሐኪሞች በቫይረሱ ምክንያት እንደሆነ ነግረውኝ በቅርቡ ይመለስልሃል ብለውኛል" ይላል።
"ሰዎች የሚናፍቀኝን ሽታ ወይም ጣዕም ይጠይቁኛል። ደስ ከሚለኝ ቡና ጀምሮ የሚናፍቁኝ ብዙ ሽታዎች እና ጣዕሞች ነበሩ። ወደ ሥራ ከማቅናቴ በፊት የምጠጣው ቡና፣ የምወደው ሽቶ ኧረ ብዙ ነገር. . ."
ሁሉም ነገር ምንም ዓይነት ጣዕምና ሽታ ሳይሰጠው ለቀናት ቆየ።
አንዳንዴ የተለየ ሽታ ይፈጠርበታል። "የገጠመኝን ሽታ ለመግለጽ ከባድ ነው ምክንያቱም ከዚህ በፊት ካሸተትኳቸው ነገሮች ጋር ማዛመድ አልቸልም።"
"ሁሌም ከእንቅልፌ ስነቃ የማሽተት እና የመቅመስ ችሎታዬ ስለመመለሱ ለማወቅ ብዙ እጥራለሁ። አለመሳካቱን ሳውቅ ለደቂቃዎች ባዝንም በሚቀጥለውም ቀን ከመሞከር ወደ ኋላ አልልም።"
አንድ ቀን ጠዋት ፊቱን ታጥቦ ጥርሱን ሲቦርሽ የጥርስ ሳሙናው ጣዕም ተሰማው።
"አላመንኩም። በፍጥነት ሊሸቱኝ የሚችሉ ነገሮችን በሙሉ ሞከርኩኝ። አፍንጫዬ በትክክልልም እየሠራ ነው።"
"ቤት ውስጥ ሊቀመስ የሚችል ነገር በሙሉ ቀምሻለሁ። ምላሴ ለአንዱ ሠርቶ ለሌላው አይሠራም የተባልኩ ይመስል ሁሉንም ነው የሞከርኩት" ሲል እየሳቀ ያስታውሳል።
"ቀኑን ሙሉ ሳሸት፣ ስቀምስ ነው የዋልኩት ማለት ይቻላል" ይላል።
ከቀናት በኋላ እክስቱን ለመጠየቅ ቤትዋ ሄዶ ሳለ ስለ ጤናው እያወሩ በመሃል የእግሩ ጣቶች እየደነዘዙት መሆኑን ይነግራታል።
"ጥቂት ስለ ጉዳዩ አውርተን የስኳር መመርመሪያ አምጥታ በደሜ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለካችው። ያሳየን ቁጥር አስደንጋጭ ነበር።"
"በፍጥነት ወደ ክሊኒክ ሄጄ ያለውን ነገር ተናግሬ ተመረመርኩኝ። ቁጥሩ ብዙም ልዩነት የለውም።"
ለጥቂት ቀናት አመጋገቡን አስተካክሎ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስኳሩን መመርመሩን ቀጠለ። ምንም ለውጥ የለም።
"የማስታውሰው ኮሮናቫይረስ እንዳለብኝ ከማወቄ ከሦስት ሳምንት በፊት ስኳሬን ተመርምሬ ትክክል እንደነበረ ነው" ይላል።
አሁን ከሐኪም ጋር ተነጋግሮ በየዕለቱ የስኳር መድኃኒት መውሰድ ጀምሯል።
"ራሴን ለማሳመን አልከበደኝም። የቤተሰቦቼ አባላትም ስኳር ስላለባቸው ለእኔ ቀላል ነበር። ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ። ከባዱ ነገር የማልወደውን መድኃኒት በየቀኑ መውሰዱ ላይ ነው" ሲል ሐሳቡን አጠናቋል።
አብርሃም የስኳር መድኃኒት መውሰድ ከጀመረ አንድ ወር አልፎታል።

"ማመን አይደለም ለመቀበል ተቸግሬ ነበር"
ሁለተኛው ታሪኩን የሚነግረን ግለሰብም በተመሳሳይ ስሙ እንዳይጠቀስ በመፈለጉ ተሾመ እያልን ታሪኩን እንቀጥላለን።
ተሾመ በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በነበረበት በየካቲት ወር እግሩን ያመው እንደጀመረ ያስታውሳል።
የተለያዩ የህክምና ተቋማትን ጎብኝቷል። የነርቭ ችግር መሆኑን ነግረው መድኃኒት ሰጥተውታል።
"መድኃኒት ወስጄ ይሻለኛል ብዬ ወደ ቤት ብመለስም ህመሙ ከባድ ነበር" ይላል።
"ማታ ማታ የነበረኝ ህመም ከባድ ነበር። መቀመጥም መተኛት አልችልም። ችግሩ የነርቭ መሆኑን እየነገሩ ህመሙ ከባድ መሆኑን ሐኪሞች ይነግሩኛል።"
"እግሬ ሊንቀሳቀስ አልቻለም። ቁርጥማቱም አላስተኛ አለኝ። ሐኪሞች መድኃኒቱን መውሰዴን እንድቀጥል ስለሚነግሩኝ" ከህመሙ ጋር ትግል መቀጠሉን ይናገራል።
መድኃኒቱ ግን ለውጥ አላመጣም።
በዚህ ምክንያት አጠቃላይ ምርመራ ለማድረግ ከሐኪሞቹ ጋር ተነጋግሮ ይወስናል።
ከምርመራዎቹ አንዱ የኮሮናቫይረስ ነበር እና ውጤቱ ሲመጣ ፖዘቲቭ እንደሆነ ይነገረዋል።
በኮሮናው ብቻ ቢበቃ ጥሩ ነበር። ቀደም ሲል እንዳለበት ካወቀው የነርቭ ህመም በተጨማሪ ስኳር እና ደም ብዛት እንዳለበት ተነገረው።
በቤተሰቡ ውስጥ ስኳር እና ደም ብዛት ያለባቸው ዘመዶች እንዳሉት ቢያውቅም ከዚያ በፊት ይኖርብኛል ብሎም ሆነ ምልክቱን አስተውሎት አያውቅም።
"የስኳር መጠኔ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ስኳር እንዳለብኝ እንደማላውቅ ስነግራቸው ሐኪሞቹ አላመኑኝም ነበር።"
ስኳሩ ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር "እንዴት ምንም ምልክትም ሳታሳይም ሆነ ሳትወድቅ እዚህ ደረስክ" እያሉ ጠይቀውኛል" ብሏል።
"ሐኪም ቤት ስደርስ የስኳር መጠኔ በጣም ከፍተኛ ነበር። ትንሽ ብቆይ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተነግሮኛል።"
ሁለተኛው ዓይነት የስኳር ህመም እንዳለበትም ባለሙያዎች ነግረውታል።
ተሾመ በአንድ ጊዜ ብዙ ህመሞች እንዳሉበት ያወቀው እግሩ ላይ የህመም ስሜት ብቻ ተሰምቶት ነው። ሌሎች ህመሞች እንዳሉበት ቢታወቅም ኮሮናቫይረሱ ግን ምንም ምልክት አላሳየም።
"ትኩሳት፣ ራስ ምታትም ሆነ ሌላ የኮሮና ምልክት ለአንድም ቀን አልነበረኝም" ይላል።
ሐኪሞቹ በኮሮናቫይረስ ምክንያት እነዚህ ህመሞች ተባብሰው ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው ነግረውታል።
"በመገናኛ ብዙኃን በተለያዩ አገሮች ከኮሮና በኋላ በሌሎች ዘላቂ በሽታዎች የተያዙ ሰዎች እንዳሉ አንብቤያለሁ" ቢልም አብዛኛዎቹ በከባድ የኮሮናቫይረስ ህመም የተሰቃዩ እና ሆስፒታል የገቡ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንግሊዝ ውስጥ ብቻ በከባድ ኮሮናቫይረስ ምክንያት ሆስፒታል ከገቡ ሰዎች መካከል አምስት በመቶ ያህሉ ስኳር ህመም እንዲጀምራቸው ምክንያት ሆኗል ተብሏል።
ተሾመ አሁን በየቀኑ ስድስት መድኃኒቶችን በመውሰድ ላይ ይገኛል።
"መጀመሪያ ላይ በጣም ከባድ ነበር። እግሬ ላይ በጀመረኝ አነስተኛ ህመም ምክንያት አይደለም ዕድሜ ልኬን፣ በየቀኑ ስድስት መድኃኒት እየዋጥኩኝ እኖራለሁ ብዬ አይደለም ሐኪም ቤት እሄዳለሁ ብዬም አስቤ አላውቅም። ማመን አይደለም ለመቀበል ተቸግሬ ነበር" ይላል።
"መድኃኒት መዋጥ የማልወደው ሰውዬ በየዕለቱ መድኃኒት ከመዋጥ ባሻገር የሕይወት ዘይቤዬን ለመቀየርም ተገድጃለሁ። የምበላውም ሆነ የምጠጣው ነገር በጥንቃቄ ነው" ሲልም ይገልጻል።
በቅርብ የሚያውቃቸው ሰዎች ሕይወት በኮሮናቫይረስ ሲያልፍ እና ቤተሰብ ሲበተን መመልከቱ ሐሳቡን እንዲቀይር እንደረዳውም ይገልጻል።
"በቅርብ የማውቃቸው ሰዎች በኮሮና ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ልጆች ያለ አባት እና እናት ሲቀሩ ተመልክቻለሁ። አንድ ባልደረባዬም በዚሁ ምክንያት ሕይወቱ አልፏል"
"ይህንን ስመለከት ከማማረር አምላክ ለልጆቼ ነው ያተረፈኝ እላለሁ።"
"ሐኪሞች [ተደራራቢና ተጓዳኝ በሽታ ካለባቸው ሰዎች አንጻር] 'ዕድለኛ ነህ' ይሉኛል። እኔም ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ሰዎች የደረሰባቸውን ጉዳት እያየሁ ዕድለኛ ነኝ እላለሁ" ይላል።













