ኮሮናቫይረስ፡ የሕንዱ ድርጅት በኮቪድ-19 ለሞቱ ሠራተኞቹ ቤተሰቦች ካሳ ሊከፍል ነው

ታታ ስቲል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሕንድ አንድ የብረት ማምረቻ ድርጅት በኮቪድ-19 ሳቢያ ለሞቱ ሠራተኞቹ ቤተሰቦች ካሳ እንደሚከፍል አስታወቀ።

ይህን ያለው በሕንድ ከትላልቅ የብረት ፋብሪካዎች አንዱ የሆነው ታታ ስቲል ነው።

ድርጅቱ የሞቱ ሠራተኞቹ የጡረታ እድሜ [60 ዓመት] እስከሚደርስ ደመወዝ፣ የቤትና የሕክምና ጥቅማ ጥቅም እከፍላለሁ ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ለግንባር ቀደም ሠራተኞቹ ልጆች እስከሚመረቁ ድረስ የትምህርት ክፍያ እንደሚከፍል ቃል ገብቷል።

ሕንድ ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ 300 ሺህ ሰዎችን በቫይረሱ አጥታለች። ባለሙያዎች ግን ቁጥሩ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ይናገራሉ።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ታታ ስቲል በዚህ አስፈሪ ወረርሽኝ ወቅት በተቀጠፉ ውድ ሠራተኞቹ ማዘኑን ገልጾ ከቤተሰቦቻው ጎን እንደሚቆም ገልጿል።

በእርግጥ ታታ ስቲል ይህን ያለ የመጀመሪያው ድርጅት አይደለም።

ባለፈው ሳምንት የሆስፒታል ግሩፕ ኦዮ ሩምስ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የሞቱ ሠራተኞቹን ቤተሰቦች በተለያየ መንገድ እንደሚረዳ ገልጾ ነበር።

ኦዮ ሩምስ ቃል የገባው ድጋፍ የስምንት ወር ደመወዝ ክፍያን እና የአምስት ዓመት የልጆቻቸውን የትምህርት ክፍያ ይጨምራል ብሏል።

የድርጅቱ መሥራች ሪተሽ አጋርዋል በትዊተር ገጻቸው ላይ በተከታታይ ባሰፈሩት ጽሁፍ "ኮቪድን ለመከላከል የሚደረገው ትግል ከአቅም በላይ ሆኗል፤ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት በጎ ተግባራት የቤተሰቦቻቸውን ችግር ያስወግዳሉ" ብለዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ብርጭቆ አምራች ድርጅቱ- ቦሮሲል በኮቪድ-19 ለሞቱ ሠራተኞቹ ለሁለት ዓመታት ደመወዝ እንደሚከፍል ቃል ገብቷል።

የድርጅቱ ዳሬክተር ሽሪቫር ኬሩራ በሊንክድን ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ድርጅቱ በኮቪድ-19 በሞት ለተለዩዋቸው ሠራተኞቻቸው ልጆች የትምህርት ወጪ እንደሚከፍል ገልጸዋል።

እነዚህ ድርጅቶች ይህንን ያስታወቁት አገሪቷ በበሽታው በርካታ ዜጎቿን በማጣቷ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ነው።

ሁለተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በአገሪቷ የጤና ሥርዓት ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል።

ከአቅማቸው በላይ የተጨናነቁት የሕክምና ተቋማትም በቫይረሱ ተይዘው ወደ ተቋማቸው የሚመጡ ህሙማንን ለመመለስ ተገደዋል።

በበርካታ ቦታዎች ወሳኝ የሆኑ መድሃኒቶችና የኦክስጅን አቅርቦት የለም። የአስክሬን ማቃጠያ ቦታዎችም ሞልተዋል።

በዚህ ሳምንት ሕንድ በአጠቃላይ ከ300 ሺህ በላይ ሞት በመመዝገብ ከአሜሪካና ከብራዚል ቀጥሎ ከዓለም ሦስተኛዋ አገር ሆናለች።

በሕንድ 26 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን ከአሜሪካ ቀጥላ በሁለተኛነት ተቀምጣለች። አሁን ላይ ሕንድ የዓለማችን የወረርሽኙ ማዕከል ሆናለች።