ኮሮናቫይረስ፡ በሕንድ ያጋጠመው የኮሮና ቀውስ የኮቫክስን ክትባት ጎትቷል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, UNICEF/KOKOROKO
በሕንድ ባጋጠመው ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ሥርጭት ምክንያት በመላው አለም የቫይረሱን ክትባት ለማዳረስ የሚደረገውን ርብርብ በ 140 ዶዝ ወደ ኋላ ጎትቷል ተባለ።
ኮቫክስ በተሰኘው ፍትሃዊ የክትባት ማከፋፋያ ጥምረት ሥር ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ክትባት የምታበረክተው ሕንድ የውጪ ንግዷ ላይ በጣለችው ክልከላ ምክንያት ላለፉት ሦስት ወራት አንድም ጭነት መላክ አልቻለችም።
ሕንድ ክትባቱን የምታመርተው ሲረም ኢንስቲትዩት ኢንዲያ በተባለ ተቋሟ አማካኝት ነበር።
የተመድ የሕፃናት ኤጀንሲ ዩኒሴፍ የኮቫክስን ክትባት የመግዛት እና የማከፋፈል ተግባሩን እያከናወነ ይገኛል።
ኤጀንሲው የቡድን ሰባት እና የአውሮፓ ሕብረት አገራት ከራሳቸው ድርሻ ላይ ክትባቶችን እንዲያካፍሉ እየጠየቀ ይገኛል።
ኃያላኑ አገራት በቀጣዩ ወር በእንግሊዝ ይሰበሰባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዩኒሴፍ እንዳለው አገራቱ የዜጎቻቸውን ፍላጎት ካሟሉ በኋላ 153 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት መለገስ የሚያስችል አቅም አላቸው።
ሲረም ኢንስቲትዩት በመላው አለም በኮቫክስ ሥር ይሰራጫል ተብሎ ከሚጠበቀው ሁለት ቢሊዮን ክትባት ግማሹን ይሸፍናል ተብሎ ነበር።
ሕንድ ለአራት ተከታታይ ወር ክትባቱን አምርታ ትጭናለች ተብሎ አይጠበቅም። ይህ ከሆነ ጉድለቱ አሁን ካለበት ወደ 190 ሚሊዮን ያሻቅባል።
የዩኒሴፍ ኮቫክስ የአቅርቦት አስተባባሪ ጂያን ጋንዲ "ቀጣይ ዶዞች መቼ ይጫናሉ የሚለውን የማናውቅበት ደረጃ ላይ ነው ያለነው" ብለዋል።
"ነገሮች በቅርቡ ተስተካክለው ወደ መስመራችን እንመለሳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ነገር ግን በሕንድ ያለውን ሁኔታ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፤ ይህ ከፍተኛ ስጋት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ዩኒሴፍ ክትባት አዋጡ ካላቸው ኃያላን አገራትም የተወሰኑት ከሕዝብ ብዛታቸው በላይ ብዙ እጥፍ ክትባት አዘዋል። እንግሊዝ፣ ካናዳ እና አሜሪካ ቀዳሚዎቹ ናቸው።
በየካቲት ወር የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቦሪስ ጆንሰን አገራቸው የሚተርፋትን ክትባት ለደሃ አገራት ለመስጠት ቃለ ገብተው ነበር። ነገር ግን እስካሁን ይህ የሚሆንበትን ጊዜ አልገለጹም።
አሜሪካም በተመሳሳይ ጊዜውን ባታስታውቅም ፈረንሳይ ግን ብቸኛዋ ክትባቶቿን ለመለገስ ቃል የገባች የቡድን ሰባት አገር ናት። ፈረንሳይ ግማሽ ሚሊዮን ክትባት ለመለገስ ቃል ገብታለች።












