ባለፈው እሑድ በፍልስጤም-እስራኤል ግጭት ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር ተመዘገበ

የፎቶው ባለመብት, AFP
እስራኤልና ፍልስጤም ግጭት ከተጀመረ ወዲህ እንደ እሑድ ዕለት በርካታ ሞት የተመዘገበበት ዕለት የለም፡፡
የጋዛ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በትንሹ 40 ሰዎች እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት ተገድለዋል፡፡
የእስራኤል ባለሥልጣናት በበኩላቸው የፍልስጤም ተዋጊዎች በድምሩ ሦስት ሺህ ሮኬቶችን አስወንጭፈዋል ይላሉ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ግጭቱ ወደማያባራ ጦርነት እንዳይሄድ ፍርሃት አለኝ ብለዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ በጋዛ የነዳጅ እጥረት እየተከተለ መሆኑ አሳስቦኛል ብሏል፡፡ ምክንያቱም ሆስፒታሎች ኃይል የሚያገኙት ከዚሁ ስለሆነ ነው፡፡
በርካታ ቁስለኛ ባለበት ሁኔታ ሆስፒታሎች ኃይል ከተቋረጠባቸው ለብዙዎች ሞት ምክንያት እንዳይሆን ስጋት አለ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ማስተባበርያ ዴስክ ምክትል ኃላፊ ሊየን ሀስቲንግስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለጋዛ ነዳጅ ለማቅረብ የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዲፈቅዱ ጠይቀው ተከልክለዋል፡፡
ነዳጅ ለማቅረብ አካባቢው አስተማማኝ እንዳልሆነም ተነግሮናል ብለዋል፡፡

የፎቶው ባለመብት, EPA
የጋዛ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ትናንትና እሑድ ብቻ 16 ሴቶችና 10 ሕጻናትን ጨምሮ በድምሩ 42 ፍልስጤማዊያን እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት ተገድለዋል፡፡
ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ በድምሩ 10 ሰዎች ከእስራኤል ወገን ተገድለዋል፡፡ ይህ አሐዝ ግን ግጭቱ ካገረሸ ጀምሮ የተመዘገበ ነው፡፡
በጋዛ እስከ ትናንት ድረስ ብቻ ድምር የሟቾች ቁጥር 188 አልፏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 55ቱ ሕጻናት ናቸው፡፡ 33 የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡
በድምሩ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎችም ቆስለዋል፡፡
እስራኤል እንደምትለው ከሟቾቹ አብዛኛዎቹ ተዋጊዎች ናቸው፡፡
ትናንት እሑድ እኩለ ሌሊት ላይ እስራኤል በወሰደችው የአየር ጥቃት 3 ሕንጸዎች ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል፡፡ ሕንጻዎቹ የሚገኙት ደግሞ ሰው በሚበዛባቸው ጎዳናዎች ላይ ነበር፡፡
ሐማስ የአጸፋ ምላሽ የሰጠ ሲሆን ሮኬቶችን ወደ ደቡባዊ እስራኤል አስወንጭፏል፡፡
የማስጠንቀቂያ ደውሉን ተከትሎ ሚሊዮን የሚሆኑ እስራኤላዊያን ወደተዘጋጁላቸው ምሽጎቻቸው ተደብቀዋል፡፡
ፍልስጤማዊያንም በጥቃቱ ላለመሞት የሚቻላቸውን ቢሞክሩም በተጨናነቀው ጋዛ ወደየትም መሸሸግ አልቻሉም፡፡
ሐማስ የሚያስወነጭፋቸው ሮኬቶች አሽከሎን፣ አሽዶድ እና ኔቲቮት በሚባሉ ደቡባዊና መካከለኛ የእስራኤል ከተሞች ነው የሚወድቁት፡፡
እስከአሁን ይህ ነው የሚባል ጉዳት ስለማድረሳቸው የተዘገበ ነገር የለም፡፡
አብዛኛዎቹ የሐማስ የሮኬት ጥቃቶች በእስራኤል አይረን ዶም ዲፌንስ ሲስተም በሰማይ ሳሉ የሚመክኑ ናቸው፡፡












