አነፍናፊ ውሾች ኮሮናቫይረስ ያለባቸውን እንደሚለዩ ተጠቆመ

አነፍናፊ ውሻ

የፎቶው ባለመብት, JOHN AKEHURST

አነፍናፊ ውሾች የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚችሉ የሳይንስ ሊቃውንት አስታወቁ፡፡

በተካሄደ አንድ ሙከራ መሠረት ውሾች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የሚያመነጩትን ልዩ የሆነ ሽታ እንዲለዩ ሰልጥነዋል። የሰው አፍንጫ ግን ይህን ሽታ መለየት አይችልም።

ይህም በአውሮፕላን ማረፊያዎች ወይም ብዙ ሰዎች በሚገኙበት ዝግጅቶች ቫይረሱ ያለባቸውን ለመለየት ሊረዳ ይችላል፡፡

ውሾቹ የሚለዩዋቸው ሰዎች በቫይረሱ ስለመያዛቸው በቤተ ሙከራ ምርመራ መረጋገጥ አለት ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡

ውሾቹ 88 በመቶ የኮሮናቫይረስን በትክክል ቢለዩምም 14 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች ኮቪድ-19 ሳይኖርባቸው ቫይረሱ እንዳለባቸው በስህተት በውሾቹ ተለይወተዋል።

የውሾች የማሽተት ችሎታ ከሰዎች እስከ 100,000 እጥፍ ይበልጣል። ለረዥም ጊዜም አደንዛዥ እጽና ፈንጂዎችን ሲለዩ ኖረዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ምርምሮች አንዳንድ የውሻ ዝርያዎች ካንሰር፣ ፓርኪንሰን እና ወባን ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎችን በጠረን መለየት እንደሚችሉ አሳይተዋል፡፡

ስድስት ውሾች ኮሮናቫይረስ ያለባቸው ሰዎች የለበሷቸውን ካልሲዎች፣ የአፍና አፍንጫ ጭንብሎች እና የተለያዩ ቲሸርቶችን ሽታ እንዲገነዘቡ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡

ውጤቱን በትክክል ሲገምቱም ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ውሾቹ ከለዩዋቸው እና ቫይረሱ ከሌለባቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ጉንፋን ያለባቸው ሲሆን ይህም የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች መለየት መቻላቸውን ለማረጋገጥ ነው ተብሏል፡፡

ውሾቹ የተለያዩ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎችን ከመለየት ባሻገር ምንም ምልክቶች የሌላቸውን እና በጣም አነስተኛ ቫይረስ በሰውነታቸው ውስጥ ያለባቸውንም ሰዎች ለይተዋል።

እንስሳቱን ያሠለጠኑት የሜዲካል ዲቴክሽን ዶግስ ዋና ሳይንቲስት የሆኑት ዶ/ር ክሌር ገስት፤ "ውጤቱ ውሾች የሰውን ልጅ ህመሞችን በማሽተት ለመለየት በጣም አስተማማኝ ከሆኑት የባዮሴንሰሮች አንዱ ስለመሆናቸው ተጨማሪ ማስረጃ ነው" ብለዋል፡፡

ውሾቹ 88 በመቶ የሚሆኑትን ቫይረሱ ያለባቸውን መለየት ችለዋል። ይህም 100 ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች 12ቱን ብቻ መለየት አልቻሉም ማለት ነው፡፡

ኮቪድ-19 ከሌለባቸው 100 ሰዎች መካከል አነፍናፊ ውሾቹ 14ቱ ቫይረሱ አለባቸው ሲሉ በስህተት ለይተዋል።

300 ተሳፋሪዎችን በጫነ አውሮፕላን ውስጥ አንድ ሰው ኮቪድ-19 ካለበት ውሾቹ ግለሰቡን በትክክል ለይተው ማወቅ ይችላሉ። ሆኖም በስህተት 42 መንገደኞች ቫይረሱ አለባቸው ሲሉም ይለያሉ።

ይህ ማለት አንዳንድ ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች የማይለዩ ሲሆን ቫይረሱ የሌለባቸው አንዳንድ ሰዎችም በውሾቹ አለባቸው ሊባሉ ይችላሉ፡፡

የተለያዩ መርመሪያ ዘዴዎች ተመሳሳይ ስህተት ይፈጽማሉ። ከተለመደው የአፍንጫ ወይንም የጉሮሮ ፈሳሽን በመጠቀም ከሚደረገው ምርመራ አንጻር ውሾቹ ብዙ ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው በተሳሳተ መንገድ ያሳያሉ።

በመሆኑም የምርምር ቡድኑ ውሾችን ብቻ በመጠቀም ቫይረሱን ለመለየት መሞከርን አይመክርም፡፡

ውሾቹ ከተለመዱት መርመሪያዎች ጎን ለጎን ተጨማሪ የማጣሪያ መመርመሪያ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ተመርማሪዎቹ ያምናሉ። የውሻ ምርመራን ከተለመደው የአፍና የአፍንጫ ምርመራ ጋር በማጣመር እስከ 91 በመቶ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ይለያሉ ይላሉ፡፡

ዋነኛው ጠቀሜታ ግን ፍጥነት ነው። በጣም ፈጣን በሚባሉት መመርመሪያዎች ውጤቱን ለማግኘት 15 ደቂቃዎችን ሲወስዱ፤ ውሾች ግን በሰከንዶች ውስጥ በማሽተት ቫይረሱን ሊለዩ ይችላሉ፡፡

ተመራማሪዎች እንደሚሉት ሁለት ውሾች 300 ሰዎችን በግማሽ ሰዓት ውስጥ መመርመር ይችላሉ፡፡

ጥናቱን ከዱራም ዩኒቨርስቲ ጎን ለጎን ባካሄደው የሎንዶን የንፅህና እና ትሮፒካል ሜዲካል ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሎጋን ዘዴው "የጅምላ ምርመራ ለማድረግ ተስማሚ ሊሆን ይችላል" ብለዋል፡፡

ሰዎች ለበረራ ወይም ለአንድ ዝግጅት በተሰለፉበት ውሾቹን በመጠቀም መመርመር እና ቫይረሱ እንዳለባቸው የተለዩትን በመደበኛው የፒ.ሲ.አር. ምርመራ በድጋሚ እንዲመረመሩ ማድረግ ይቻላል።

ይህም ወደ ሆቴሎች ለይቶ ማቆያ የሚገቡትን ሰዎች ቁጥር ለመቀነስ ያስችላል፡፡

ብዙ ምርመራ በማይደረግባቸው እንደ ባቡር ጣቢያ ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የቫይረሱ አሰራጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ውሾችን በመጠቀም መለየት ይቻላል ተብሏል፡፡

ጥናቱ ገና በመጀመርያ ምዕራፍ ላይ የሚገኝ ነው። በሳይንስ መጽሔቶች ላይ ከመታተሙ በፊት በሌሎች ሳይንቲስቶች መገምገም እና በመቀጠልም ከልብስ ይልቅ ቫይረሱ ባለባቸው ሰዎች ላይ ሙከራ ማድረግን ይጠይቃል፡፡