የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተስፋውን የነጠቀው የኩላሊት ሕመምተኛ

የፎቶው ባለመብት, Mohammed Hamoud
አቶ ሲሳይ ተስፋዬ ሁለቱ ኩላሊቶቹ ሥራ ካቆሙ ከሦስት ዓመት በላይ ሆኖታል። የኩላሊት በሽታው የአልጋ ቁራኛ ሳያደርገው በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥሮ በመስራት ቤተሰቡን በአግባቡ ከመምራት ባለፈ ከሚያገኘው ደመወዝ ቆጥቦ የሪል ስቴት ቤት እስከመግዛት ደርሶ ነበር።
እርሱ እንደሚለው ከ26 ዓመት በፊት ታዲያ የስኳር በሽታ ጀምሮታል። የስኳር በሽታውን ለማስተካከል አስፈላጊ ያለውን ነገር እያደረገ ቆይቷል።
ይህንን ህመሙን አስተካክሎም ኑሮን በተሻለ መንገድ ለመምራት ትልቅ ተስፋ ሰንቆ ጥረት እያደረገ ነበር። ትዳር መስርቶ ሁለት ልጆችን አፍርቷል። የስድስት እና የአራት ዓመት ታዳጊዎች።
አቶ ሲሳይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ 14 ዓመታትን አገልግሏል። ከሦስት ዓመት በፊት ከሚሰራበት መሥሪያ ቤት ለእረፍት ብሎ ሲወጣ ከተለመደው የስኳር ህመም ውጪ የተለየ ተጨማሪ የጤና እክል አልነበረበትም።
ነገር ግን ያላሰበው ፈተና ገጠመው። ይህም ወደ ሥራው ተመልሶ የተለመደ ተግባሩን የሚከውንበት የጤና ሁኔታም ሆነ መፍትሄ የሌለው ክስተት ተፈጠረ። ሁለቱም ኩላሊቶቹ መሥራት ማቆማቸውን በህክምና አረጋገጠ።
ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኘውን ሥራ አቁሞ የአልጋ ቁራኛ ሆነ። ወዲያውኑ የኩላሊት እጥበት [ዲያሌሲስ] መጀመር ስለነበረበት ጤናውን ለመመለስ ጊዜ አላጠፋም።
የነበረውን ገንዘብ አሟጦ የቻለውን ሁሉ ነገር አደረገ። ሕክምናው ግን በዚህ የሚቆም ባለመሆኑ ተጨማሪ ገንዘብ አስፈለገው። በሚኖርበት አዲስ አበባ ገዝቶት የነበረውን ጅምር የሪል ስቴት ቤት ለመሸጥ ተገደደ።
አቶ ሲሳይ የሰው እጅ አላይም በማለት ቤቱን ሽጦ የጀመረውን የኩላሊት እጥበት ማድረጉን ቀጠለ። ነገር ግን ሕክምናው አንድ መቋጫ መፍትሔ ሳይገኝለት እጁ ላይ የነበረው ገንዘብ አለቀ።
'አለኝ' የሚለውን ሁሉ የጨረሰው አቶ ሲሳይ አሁን ያለው አማራጭ ወይ ሞትን መጣባበቅ አልያም ደግሞ እጅን ለእርዳታ መዘርጋት ነው።
ይህንን ተከትሎም የኩላሊት እጥበት ማቆም ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ወጭ የሚገዙ መድኃኒቶችን መግዛት አለመቻል እና መድኃኒቶችን መውሰድ እስከ ማቆም ደርሶ እንደነበር አቶ ሲሳይ ያስታውሳል።
"ያ ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ከመድኃኒት ባለፈ ከቤት የሚበላ እስከማጣት የደረስንበት ጊዜ ነበር" ይላል።
በመካከል ሰዎችን እንዲረዱት በመጠየቅ ሕክምናውን ለማስቀጠል ጥረት አድርጓል። ያም ሆኖ ግን ጫናው ቀላል የሚባል አልነበረም። "ዲያሌሲስ አድርጌ ደካክሞኝ ስለምመለስ ልጆቼ በጣም ይጨነቃሉ፤ እኔን ማየት ራሱ ይፈራሉ። ያ በራሱ ሌላ በሽታ ነበር" ይላል አቶ ሲሳይ።
አቶ ሲሳይ አልጋ ላይ ሲወድቅ ቤቱን የማስተዳደሩ ሙሉ ኃላፊነት በባለቤቱ ትከሻ ላይ ወደቀ።
"ባለቤቴ ሁሉንም ነገር ችላ ነው እየኖርን ያለነው፤ አንዳንድ ቀን በጣም ችግሩ ሲከፋ ለልመና ጎዳና ወጥታ አንድም ሁለትም ብር ይዛ የተመለሰችበት ጊዜ አለ" በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ይገልጻል።
በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ግን አቶ ሲሳይ አንድ ተስፋ ነበረው። በወቅቱ ሕክምናው ኢትዮጵያ ውስጥ ይሰጥ ስለነበር ኩላሊት የሚለግሰው ሰው ከተገኘ የኩላሊት ንቅለ ተከላውን በአገር ውስጥ የሚያደርግበት ዕድል በመኖሩ ለእርሱም ለቤተሰቡም ትልቅ ተስፋ ነበር። ይህንን ለመከወንም አስፈላጊ ያላቸው ሂደቶች ተከናውነው ነበር።
ባለቤቱ ኩላሊቷን ለመስጠት እና የባሏን ሕይወት ለመታደግ ፈቃደኝነቷን አሳይታለች። ሕክምናውን ለማድረግም ባለቤቱ ኩላሊቷን መለገስ እንደምትችል የሕክምና ምርመራ ማድረግ ስለነበረባት ያንንም በስኬት አጠናቅቃ ቀጣዩ ሂደት ይጠበቅ ነበር። በመካከል ግን ያልተጠበቀው ክስተት ተፈጠረ።
ከቻይና ተነስቶ ዓለምን ያጥለቀለቀው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታውን ቀየረው። ይህም እነ ሲሳይ ተስፋ አድርገውበት የነበረው ሕክምና በኢትዮጵያ መሰጠቱን እንዲያቆም ምክንያት ሆነ።
ይህ ለሲሳይ እና ቤተሰቦቹ ከባድና አስደንጋጭ መጥፎ ዜና ነበር። የሕክምናው መቆም በራሱ አስደንጋጭ ሆኖ ሳለ በቋፍ ላለው የሲሳይ ሕይወት የቫይረሱ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባት ደግሞ ሌላ አሳሳቢ ጉዳይ ሆነ።
"ስለቫይረሱ የሚወራው ሁሉ በጣም አስፈሪ ስለነበር፣ እንደማልተርፍ የተረዳሁበት ጊዜ ነበር" ይላል አቶ ሲሳይ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ።

የፎቶው ባለመብት, Sisay Tesfaye
በተለይ "እኔ ዲያሌሲስ በማደርግበት ሆስፒታል እንደእኔ ዲያሌሲስ የሚያደርጉ ሁለት ሰዎች በኮሮናቫይረስ ታምመው ስለሞቱ ስጋቴ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ ነበር" ይላል።
ቫይረሱ ኢትዮጵያ ከገባ ከአንድ ዓመት በኋላ አቶ ሲሳይ በሳምንት ሁለት እና ሦስት ጊዜ ከሰዎች እርዳታ በመጠየቅ ዲያሌሲሱን እያደረገ ነው። ሆኖም ግን የጤንነቱ ሁኔታ እየተዳከመ መሆኑን እና ሲንቀሳቀስም በሰው ተደግፎ መሆኑን ተናግሯል።
የ39 ዓመቱ አቶ ሲሳይ "ከዓመታት በፊት ብዙ ተስፋዎችን ሰንቄ የተሻለ ኑሮን እያለምኩ ነበር፣ አሁን ግን ያ ሁሉ ቀርቶ ሕይወቴን ለማቆየት እንኳ ተስፋዬ በሰዎች እጅ ሆኗል" ይላል።
አሁን ሁሉንም ነገር ከሰዎች እርዳታ በመጠየቅ ኑሯቸውን እየገፉ እና ሕክምናውንም እያደረገ መሆኑን ይናገራል። በጣም አስከፊ ጊዜ ሲገጥመው በተለይ የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቹ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ከደመወዛቸው በማዋጣት እንደሚደጉሙት ገልጿል።
በሽታው በአሁኑ ወቅት የአንድ ዓይኑን እይታ ሙሉ በሙሉ አጥፍቶታል። "አሁን አንድ ዓይኔ በዚሁ ምክንያት ስለጠፋ ቦርድ ተጽፎልኝ የተወሰነ ጡረታ እየከፈሉኝ ነው" የሚለው አቶ ሲሳይ በየቦታው ጎፈንድሚ ተከፍቶ ከክረምቱ በፊት እናደርስልሃለን ብለውኝ እነሱን እየጠበቅኩ ነው" ብሏል።
ሕክምናው የሚከናወነው ታይላንድ፣ ባንኮክ ነው። ሙሉ ሕክምናውን ለማከናወን የጉዞ እና ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር እስከ 40 ሺህ ዶላር እንደሚያስፈልገው መረጃ አሰባስቧል።
ለዚህ የሚሆን ከጎፈንድሚ በተጨማሪ በግል የባንክ ሂሳቡ ሰዎች እንዲያግዙት እየጠየቀ ቢሆንም እስካሁን የታሰበውን ያክል እንዳልተሳካለት ገልጿል።
"አንደኛው ዓይኔ ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል፤ አይመለስም። አንደኛው ግን ባለበት ሁኖ ሳይጎዳ ሊቆይ ይችላል። ይህ የሚሆነው ግን የታሰበው ሕክምና በፍጥነት ከተሳካ ነው። ካልሆነ ሁለቱንም አይኔን የማጣበት እድል ይፈጠራል" ብሏል አቶ ሲሳይ።
የጤናው ሁኔታ በዚህ ወቅት በጣም አስቸጋሪ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚናገረው አቶ ሲሳይ "አሁን ላይ ኢንፌክሽን ተብሎ የእርሱን መድኃኒት እየወሰድኩ ነው" ብሏል።
ምናልባት ከዓመታት በፊት ቅድመ ምርመራ አድርጎ ቢሆን ኖሮ በሽታው አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ላይደርስ እንደሚችል ሲሳይ ይገምታል። ይህ ደግሞ በእርሱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሰዎች ላይም በብዛት የሚያጋጥም ነው። እናም ማንኛውም ሰው ምርመራ ለማድረግ የግድ የሕመም ስሜት እስኪሰማው መጠበቅ እንደሌለበት ሲሳይ ይመክራል።
ቅድመ ምርመራ ማድረግ ከእንደዚህ አይነት አስከፊ በሽታ ለመጠበቅ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑንም ያስቀምጣል።















