የህንድ ሐኪሞች ከአንድ በሽተኛ 7.4 ኪሎ የሚመዝን ኩላሊት አወጡ

ሐኪሞች በቀዶ ህክምና ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የህንድ ሐኪሞች የሁለት አራስ ልጆች ክብደት ያለው 7.4 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኩላሊት ከአንድ ታማሚ ላይ ማስወገዳቸው ተነገረ።

ይህ ከፍ ያለ መጠን ያለው ኩላሊት ህንድ ውስጥ ከሰዎች አካል እንዲወጣ ከተደረጉት ሁሉ ትልቁ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን መጠኑም ከሰባት ኪሎ በላይ ነው።

የአንድ ጤናማ ሰው ኩላሊት በአብዛኛው ከ120 እስከ 150 ግራም ብቻ የሚመዝን መሆኑ ይህንን ክስተት ልዩ አድርጎታል።

ኩላሊቱ እንዲወጣ የተደረገለት በሽተኛ 'አውቶሶማል ዶሚናንት ፖሊሲስቲክ' በተባለና በኩላሊቱ ዙሪያ የመጠን መጨመር ባስከተለ የኩላሊት ህመም ሲሰቃይ መቆየቱ ተነግሯል።

በቀዶ ህክምናው የተሳተፉ አንድ ሐኪም እንዳሉት በዚህ አይነቱ በሽታ የተያዙ ሰዎች ላይ የኩላሊት መተለቅ ችግር ማጋጠም የተለመደ ነው።

ነገር ግን ዶክተሩ አክለውም እንዲህ አይነቱ ችግር ያጋጠመው ኩላሊት በተወሰነ ደረጃ በአካል ውስጥ ሆኖ የማጣራት ሥራውን ካከናወነና የመታመም አሊያም የመድማት ምልክቶች ካላሳየ እንዲወጣ አይደረግም።

ይህ በሽተኛ ግን በጸረ ተህዋሲያን ሊታከም ያልቻለ ህመም ስላጋጠመውና ከመጠን በላይ እየተለቀ የመጣው ኩላሊቱም የመተንፈስ ችግር በማስከተሉ አማራጭ በመታጣቱ እንዲወገድ መደረጉን ዶክተሩ ገልጸዋል።

የቀዶ ህክምናውን ያደረጉት ዶክተሮች ይህን ያህል መጠን ያለው ኩላሊት ከበሽተኛው አካል ውስጥ እናገኛለን ብለው ባለመጠበቃቸው በክብደቱ መደነቃቸውን ተናገረዋል።

ዶክትር ሳቺን ካቱሪያ፤ "በውስጥ አካላት የምርምር መጽሔቶች ላይ ከፍተኛ ክብደት ያላቸው ኩላሊቶች ቢመዘገቡም በጊነስ የዓለም ክብረ ወሰን መዝገብ ላይ በክብደቱ የተመዘገበው ኩላሊት 4.5 ኪሎ ግራም ነው። ከዚህ ቀደም ግን በአሜሪካ ውስጥ 9 ኪሎ፣ በኔዘርላንድስ ውስጥ ደግሞ 8.7 ኪሎ የሚመዝን ኩላሊት ተገኝቷል" ብለዋል።

ዶክተሩ አክለውም ይህንን ኩላሊት በጊነስ የዓለም ክብረ ወሰን መዝገብ ላይ እንዲሰፍር ለማድረግ ውሳኔ ላይ እንዳልደረሱ አመልክተው ነገር ግን "እያሰቡበት" እንደሆነ ገልጸዋል።

የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ድረ ገጽ እንደሚለው፤ ፖሊሲስቲክ የተባለው የኩላሊት በሽታ የተለመደ በዘር የሚተላለፍ ሲሆን፤ ህሙማኑ በ30 እና 60 የዕድሜ ክልል ውስጥ ሲሆኑ የጤና ችግርን የሚያስከትል ነው።

በሽታው ቀስ በቀስ የኩላሊት ተግባርን በማዳከም በመጨረሻም ሥራ እንዲያቆም ሊያደርገው ይችላል።