የኩላሊት ለጋሽ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ለለጋሾች ሊከፈላቸው ይገባል?

ዱዋን ዋትስ
የምስሉ መግለጫ, ዱዋን ዋትስ

የ56 ዓመቱ ዱዋን ዋትስ የኩላሊት ህመም እንዳለበት ያወቀው ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር። አሁን ላይ ከቀናቱ አብላጫውን ጊዜ የሚያሳልፈው አላስፈላጊ ፈሳሽ ከሰውነቱ ለማስወገድ የኩላሊት እጥበት በማድረግ ነው።

የኩላሊት እጥበቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰውነቱን እያዛለው መጥቷል። የኩላሊት ንቅለ ተከላ እንደሚያስፈልገው በሀኪሙ ቢነገረውም ኩላሊት የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ ስጋት ውስጥ ጥሎታል።

አሜሪካን ጨምሮ በበርካታ አገሮች ኩላሊት የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር ስለቀነሰ አንድ ታማሚ ኩላሊት ለማግኘት ወደ አስር ዓመት ገደማ መጠበቅ ሊኖርበት ይችላል። በአገሪቱ በየዓመቱ ለ22 ሺህ ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ይደረጋል። ኩላሊት የሚፈልጉ ሰዎች ቁጠር ግን ወደ 100 ሺህ ይጠጋሉ።

በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ክፍል የሚሠሩት ዶ/ር ኪት መላንኮን እንደሚሉት፤ ኩላሊት በመጠባበቅ ላይ ሳሉ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።

ከየትኛው አገር በበለጠ በኩላሊት ህክምና ላይ ከፍተኛ ገንዘብ የምታፈሰውና በርካታ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚከናወንባት አሜሪካ፤ በዘርፉ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቷ አሳሳቢ ነው ተብብሏል።

የኩላሊት ህመም ከሰባት ሰዎች አንድ ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን፤ በተለይ ጥቁር አሜሪካውያን በኩላሊት ህመም የመያዝ እድላቸው በሦስት እጥፍ የላቀ ነው።

ጥቁር አሜሪካዊው ዱዋን ዋትስ ለዚህ ችግር አንድ ማሳያ ነው። በግንባታ የሥራ ዘርፍ ተሰማርቶ የነበረው ዱዋን በሳምንት ለአራት ቀናት የኩላሊት እጥበት ስለሚደረግለት ሥራውን ለማቋረጥ ተገዷል።

"አንድ ሰው ኩላሊቱን ሲታመም ዙሪያው ገደል እንደሆነ ቢሰማውም እጅ መስጠት የለበትም" ሲል ዱዋን ይናገራል።

ዱዋን 'አንድ ቀን ኩላሊት ለጋሽ አገኝ ይሆናል?' ብሎ በተስፋ ከመጠበቅ ባሻገር 'ናሽናል ኪድኒ ፋውንዴሽን' የተባለ ተቋም ተቀላቅሏል። ተቋሙ ሰዎች ኩላሊታቸውን እንዲለግሱ እንዴት መጠየቅ እንደሚቻል አቅጣጫ ያመላክታል።

ከኩላሊት ህሙማን አንዱ "ኩላሊት እፈልጋለሁ" የሚል ጽሁፍና ስልክ ቁጥሩ ያለበት ካናቴራ አሠርቷል። ሌላ ታማሚ ደግሞ ፌስቡክ ላይ የተማጽኖ ጽሁፍ አስፍሯል። ህሙማን በተለያየ መንገድ ኩላሊት ቢጠይቁም በቂ ለጋሽ አለመኖሩ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል።

አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች የሞቱ ሰዎችን ኩላሊት መውሰድን እንደ አንድ አማራጭ መውሰድ ጀምረዋል።

አንድ ሰው "ከሞትኩ በኋላ ኩላሊቴ አይወሰድ" ብሎ ካልተናዘዘ በስተቀር ሕይወቱ ሲያልፍ ኩላሊቱ ለንቅለ ተከላ ይውላል። ይህ ማለት ሰዎች ከሞቱ በኋላ ኩላሊታቸው እንዲወሰድ ቃል ባይገቡም ሂደቱን የሚቃወም ኑዛዜ እስካላስቀመጡ ድረስ ሲሞቱ ኩላሊታቸው ይወሰዳል ማለት ነው። ሆኖም ሂደቱ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ እያመጣ እንዳልሆነ ጥናቶች ያሳያሉ።

በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ክፍል የሚሠሩት ዶ/ር ኪት እንደሚሉት፤ አሜሪካ ውስጥ ይህ ሥርዓት ቢዘረጋ አንጻራዊ ለውጥ ሊያመጣ ቢችልም የኩላሊት ለጋሾች እጥረትን እስከወዲያኛው የሚቀርፍ አካሄድ አይሆንም።

ኩላሊት ለጋሾች ገንዘብ ሊሰጣቸው ይገባል?

በአሜሪካን ኢንተርፕራይዝ ኢንስቲትዩት የምትሠራው ሳሊ ስቲል የኩላሊት ህመም የገጠማት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2004 ነበር። ብቸኛ ልጅ በመሆኗ ኩላሊት የሚሰጣት የቅርብ ዘመድ አልነበራትም።

ብዙ ጓደኞቿ ኩላሊት ሊለግሷት ፍቃደኛነት ቢያሳዩም የትዳር አጋሮቻቸው ስላልተስማሙ ሀሳባቸውን መቀየራቸውን አሳወቋት። 2006 ላይ ህመሙ እየባሰባት ሳለ ነበር ከቨርጂንያ ፖስትራል ጋር የተዋወቀችው።

የፖለቲካ ተንታኟ ቨርጂንያ ስለ ሳሊ ህመም የሰማችው በአንድ ድግስ ላይ ነበር። መርሀ ግብሩ ተጠናቆ ቤቷ ገብታ ስለ ኩላሊት ልገሳ ካነበበች በኋላ ኪላሊቷን ለሳሊ ለመለገስ ወሰነች።

ኩላሊት ለጋሿ ፖስትራል እና ሳሊ

የፎቶው ባለመብት, Virginia Postrel

የምስሉ መግለጫ, ኩላሊት ለጋሿ ቨርጀንያ እና ሳሊ

በወቅቱ በርካቶች በቨርጂንያ መልካም ተግባር ልባቸው ተነክቶ ነበር።

"በዓለም ቀላሉ በጎ ተግባር ነው። ሰዎች ከዚህም በላይ መልካም ነገር ያደርጋሉ" ስትል ቨርጂንያ ትናገራለች።

ሳሊ በቨርጂንያ ኩላሊት ለ10 ዓመታት ኖራለች። የተለገሳት ኩላሊት ልክ በስልሳ ዓመቷ አገልግሎት መስጠት ሲያቆም ሌላ ኩላሊት ለጋሽ አገኘች።

ሳሊ እድለኛ ሆና ሁለት ጊዜ ኩላሊት የሚሰጣት ብታገኝም፤ አብዛኛው ሰው በቀላሉ ኩላሊት ለማግኘት መቸገሩ ያሳስባታል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1984 ኩላሊት ለሚለግሱ ሰዎች ገንዘብ መክፈል መከልከሉ ደግሞ ነገሮችን የበለጠ አክብዷቸዋል።

ኩላሊት ለሚለግሱ ሰዎች ገንዘብ የሚሰጠው ኢራን ውስጥ ብቻ ነው።

ሳሊ ልክ እንደ ኢራን ለኩላሊትና ሌላም የሰውነት ክፍል ለጋሾች ገንዘብ መከፈሉን ሙሉ በሙሉ ባትደግፍም፤ ለጋሾች የገንዘብ ማበረታቻ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ትናገራለች። የገንዘብ ማበረታቻ ኩላሊት ለመለገስ ፍቃደኛ የሚሆኑ ሰዎችን ቁጥር እንደሚጨምረውም ታምናለች። ጉዳዩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎችም አሳትማለች።

ኩላሊት መለገስ ለክፍያ የሚደረግ ነገር ሳይሆን በበጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚሹ ሰዎች የሳሊን ሀሳብ ይነቅፉታል። ሳሊ በበኩሏ ኩላሊት የሚፈልጉ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የክፍያ አሠራሩ መዘርጋት እንዳለበት ትከራከራለች።

የኩላሊት ህመም ያለባቸውን ሰዎች ለማስታመም የሚወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ ማስቀረት እንደሚቻል በመግለጽም ሀሳቧን ታጠናክራለች። ግማሽ ሚሊዮን አሜሪካውያን የኩላሊት አጥበት እተደረገላቸው ሲሆን ለእያንዳዳቸው 100 ሺህ ዶላር ይወጣል።

ዶ/ር ኪት ሜላንኮን

የፎቶው ባለመብት, George Washington University Hospital

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ኪት ሜላንኮን

አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ አሜሪካ ውስጥ ለአንድ ኩላሊት ልገሳ 45 ሺህ ዶላር ቢከፈል፤ አገሪቱ 46 ቢሊየን ዶላር ገቢ ታገኛለች። በርካታ ለጋሾች ክፍያን እንደሚደግፉም ጥናቶች ያሳያሉ።

ናሽናል ኪድኒ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም፤ ለኩላሊት ለጋሾች ገንዘብ መስጠትን ያገደው ሕግ እንዲሻሻል አይፈልግም። የሰዎችን የኩላሊት ልገሳ በገንዘብ መተመን ሰብዓዊነትን እንደሚጻረርም ይናገራሉ።

ሰዎች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ብቻ ለኩላሊት ክፍያ የመቀበል አሠራርን ሊበዘብዙት እንደሚችሉ የሚሰጉ ባለሙያዎችም አሉ።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1984 የወጣውን ሕግ ለማሻሻል የተደረጉ ሙከራዎች ቢኖሩም ውጤታማነቸው አጠያያቂ ነው። በ2016 ለምክር ቤት የቀረበውና ኩላሊት ለጋሾችን ገንዘብ ከመክፈል ይልቅ በሌላ መንገድ ማበረታቻ መስጠት ላይ ያተኮረው ሀሳብ እስካሁን ውሳኔ አላገኘም።

አገሪቱ ውስጥ ያለው ሀኔታ እስኪለወጥ እንደ ዱዋን ያሉ የኩላሊት ህመምተኞች ጊዜ ያላቸው አይመስልም። ዱዋን ፖለቲከኞች የሕግ ማሻሻያ እስኪያደርጉ ከመጠበቅ ይልቅ ቤተሰቡና ፈጣሪ ላይ ተስፋ መጣልን ይመርጣል።

"ብርታት የሚሰጡኝ ልጄና ባለቤቴ ናቸው። ተስፋ ለመቁረጥ የተቃረብኩ ሲመስለኝ እነሱን በማሰብ እጽናናለሁ፤ ብርታትም አገኛለሁ" ይላል።