በቂ እርዳታ ወደ ትግራይ እየገባ አይደለም ተባለ

የዓለም ምግብ ፕሮገራም እርዳታ የጫኑ መኪኖች

የፎቶው ባለመብት, WFP

በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባት ትግራይ በቂ እርዳታ እየገባ እንዳልሆነ የትግራይ ክልል አስታውቋል።

በትግራይ ኃይሎችና በመንግሥት መካከል የተኩስ አቁም ቢታወጅም እርዳታ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን መድረስ አልተቻለም ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የዓለም ምግብ ፕሮግራም 20 እርዳታ የጫኑ መኪኖችና አንድ ቦቲ ነዳጅ ወደ ክልሉ ማስገባት ቢቻልም ከቅርብ ቀናት ወዲህ የእርዳታ ጭነት መኪኖች ወደ ክልሉ አልገቡም።

በወቅቱ የዓለም ምግብ ፕሮግራም 46 እርዳታ የጫኑ መኪኖች ለሙከራ ወደ ክልሉ እንዲያስገቡ ተፈቅዶላቸው እንደነበር የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር አትንኩት መዝገበ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት አካባቢው ሰላም እንደሆነ ለማረጋገጥ ለሙከራ መግባት የነበረባቸው 25 የእርዳታ ጭነት መኪኖች ፈቃድ ባለማግኘታቸው ሰመራ ላይ ቆመው እንዳሉ ዶክተር አትንኩት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የመንግሥት ቃለ አቀባይ አቶ ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው መንግሥት ገደብ አላደረገም ይላሉ።

ወደ ትግራይ የሚደርሰው የእርዳታ መጠን "በእርዳታ ድርጅቶች አቅርቦት ላይ የተመሰረተ ነው" ሲሉ አቶ ለገሰ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ወደ ትግራይ 21 የእርዳታ ጭነት መኪኖችና የነዳጅ ቦቲ ማስገባት የቻለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም በበኩሉ በአሁኑ ወቅት ወደ ትግራይ እና ሰሜን አፋር እርዳታ ለማድረስ በሶስት ዙር የሚገቡ የእርዳታ ጭነት መኪኖችና ሁለት የነዳጅ ቦቲዎች በሰመራ እየጠበቁ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።

የእርዳታ ጭነት መኪኖቹ በአሁኑ ወቅት በሰመራ ከተማ እንዳሉና ከአፋር ክልል ባለስልጣናት ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ማለፍ እንዲችሉ ማረጋገጫ ከተሰጣቸው ለትግራይና ለአፋር ህዝብ እርዳታው እንደሚደርስ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለቢቢሲ ገልጿል።

"ለትግራይ እና ለአፋር ህዝብ ቅድሚያ በመስጠት ሁሉም አካላት በሙሉ የድርሻቸውን ሊያደርጉ ይገባል። ተጨማሪ ስቃይ በማህበረሰቡ ላይ እንዳይደርስና ሰብዓዊ ድጋፍ በወቅቱ እንድናደርስላቸው" ብሏል የዓለም ምግብ ፕሮግራም።

የተባበሩት መንግሥታት በረሃብ አፋፍ ያሉ በመቶ ሺዎችን ለመታደግ በየቀኑ አንድ መቶ የጭነት መኪናዎች እርዳታ እንደሚያስፈልግ ማስታወቁ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ለረጅም ጊዜ እርዳታ ተቋርጦ ስለቆየ በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው የእርዳታ መጠን ቦስስት እጥፍ አድጎ፣ 300 መኪኖች በቀን እንዲገባ ከተራድኦ ድርጅቶቹ ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰ ዶክተር አትንኩት ይናገራሉ።

በየብስ ይገባ የነበረው እርዳታ ከተቋረጠ ከወራት በኋላ የምግብ እርዳታ እና ነዳጅ ጭነው ወደ ትግራይ ያቀኑት ባለፈው ሳምንት ሲሆን ይህም ሁኔታ ወደ ክልሉ የሚገባውን እርዳታ ይጨምራል የሚል ተስፋ ፈንጥቆ ነበር።

በተኩስ አቁሙ ምክንያቱ እርዳታ ይገባል በሚል በርካቶች እየጠበቁ በመሆኑም የገባውን ሶስት ሺህ ኩንታል የሚገመት የእርዳታ እህል እርዳታ ለማሰራጨት እክል ፈጥሮብናል ብለዋል ዶ/ር አትንኩት።

"ስርጭቱን በተመለከተ የመጀመሪያ ዙር መቀለ ላይ ነው የምናሰራጨው ብለን ነበር። አሁን የተላከውን እንደ ህዝብ እናሰራጭ ብንል ግን ካለው ፍላጎት አንፃር ከፍተኛ መረባበሽ ይፈጥራል በሚል ለጊዜው አቆይተነዋል። እናከፋፍል ብንልም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም" ብለዋል ዶ/ር አትንኩት

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና አጋሮቹ የተራድኦ ድርጅቶች በሰሜን ኢትዮጵያ ለተጎዱ ህዝቦች ሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ አቅሙ እንዳላቸውም ለቢቢሲ አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአፋር በኩል ወደ ትግራይ እርዳታ መግባቱ የተሻሻለ መሆኑን ቢያሳይም በቂ አይደለም ብሏል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለቢቢሲ።

እርዳታው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰበው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ እርዳታ ፈላጊዎችን በትግራይ፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የአፋር እና የአማራ ህዝቦችን ለመድረስ እርዳታ የጫኑ መኪኖች በየቀኑ መጉረፍ እንዳለባቸውም ገልጿል።

አለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ መድኃኒቶች፣ የህክምና መገልገያዎችና የምግብ እርዳታ የጫኑ መኪኖቹ ከስድስት ወራት በኋላ መጋቢት 24፣ 2014 ዓ.ም ወደ ትግራይ መግባታቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።

በተጨማሪም የዓለም ምግብ ፕሮግራም 20 የእርዳታ ጭነት መኪኖች መቀለ የደረሱ ሲሆን በተጨማሪም አንድ ቦቲ ነዳጅም ወደ መቀለ ከስምንት ወራት በኋላ መድረሱንም አስታውቋል።

ሆኖም በትግራይ ክልል ያለውን መጠነ ሰፊ ፍላጎት ለማሟላት በየሳምንቱ 200 ሺህ ሊትር ነዳጅ እንደሚያስፈልግም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ጠቁሟል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።

አስራ ሰባት ወራት ያስቆጠረው ይህ ጦርነት እንዲቋጭ አሜሪካን ጨምሮ የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች አጋሮች ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥትና የትግራይ ኃይሎች ለሰብዓዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን ይህም ለሰላም በር ሊከፈትና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማብቃት ወደሚያስችል ውይይት መሄድ እንደሚችል ተስፋ ተጥሎበታል።