ከወዳደቁ ፕላስቲኮች የጫማ ቀለም የሚያመርቱት ሁለቱ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

ላዕከ ማርያም ጌቱ እና ልመንህ ሙላት በቤተ-ሙከራ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Icoglabs

ላዕከ ማርያም ጌቱና ልመንህ ሙላት የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው። ላዕከ ማሪያም የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪ ሲሆን ልመንህ ደግሞ የውሃ ምህንድስና ነው የሚያጠናው።

ሁለቱ ተማሪዎች በጋራ በመሆን 'ድሪም ሹ ፖሊሽ' የተሰኘ የጫማ ቀለም መሥራታቸውን ይናገራሉ። ምርታቸውንም በ'አይኮግ ላብ' ላይ ለውድድር አቅርበው የምስክር ወረቀት ተሸልመዋል።

ላዕከ ማርያም ተወልዶ ያደገው ደምበጫ አካባቢ መሆኑን በማንሳት ከድሮ ጀምሮ የፕላስቲክ ምርቶች ለአካበቢ ደህንነት፣ ለአፈር ለምነት እንዲሁም ለአየር ብክለት ያላቸውን ተጽዕኖ በሬዲዮ እየሰማ በትምህርት ቤትም እየተነገረው ማደጉን ያስታውሳል።

ይህ ሕልሜ ነበር የሚለው ልመንህ፣ ናይጄሪያና ኬኒያ የላስቲክ ምርቶችን መጠቀም ማገዳቸውን ማወቁ ለምርምር ሥራው አነሳሳው።

ልመንሕ የሰማቸውን የላስቲክ ምርቶች አሉታዊ ጎኖች ለማስቀረት ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰብ የጀመረው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ መሆኑን ያስታውሳል።

ይህንን ሀሳቡን ይዞ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማ ሲገባ በአንድ የማደሪያ ክፍል ከተመደበው ላዕከማርያም ጋር በሀሳብ ተግባቡ። በቅድሚያ ግን ሀሳባቸውን እውን ለማድረግ የሚያስችል ማሽን መስራት እንዳለባቸው የተነጋገሩት ወጣቶቹ፤ ማሽኑን መስራት ላይ አተኮሩ።

ለልመንሕ በማሽኑ ለማምረት የሚያስቡት ነገር ግልፅ ነበር። የወዳደቁ ላስቲኮችን በመጠቀም የጫማ ቀለም ማምረት። እንዴት ለሚለው የወዳጁ የላዕከ ማርያም ጥያቄም ሲመልስ የራሳቸውን ቀመር እንደሚሰሩ ተግባቡ።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲው ውስጥ ያለው የኢንኪዩቤሽን ማዕከል በመሄድ ማሽናቸውን መስራታቸውን የሚናገረው ልመንሕ፣ ማሽኑን ከሠሩ በኋላ ወደ ምርት ሲገቡ አካባቢ እንዳይበክሉ የሚያደርግ ማሽን መስራታቸውን ይናገራል።

ማሽናቸው በሰዓት አምስት ኪሎ ግራም የምታመርት አነስተኛ ማሽን መሆኗን የሚናገረው ላዕከ፣ ከሰው እርዳታ ውጪ ማምረት እንድትችል ተደርጋ መሰራቷን ይገልጻል።

ማሽኑን ለማመስራት የተለያዩ እቃዎች የገዙ ሲሆን፣ አጠናቅቆ ለመስራት ሶስት ወር እንደፈጀባቸው ያስታውሳል።

ላዕከማርያምና ልመንህ የሰሩት ማሽን

የፎቶው ባለመብት, laekmariyam

በአካበቢው የወዳደቁ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብና የተወሰኑ ኬሚካሎችን በመጠቀም የጫማ ቀለም የሰሩት ሁለቱ ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የጫማ ቀለሙን ለመስራት የራሳችንን የሆነ ቀመር ተጠቅመናል ይላሉ።

የሠሩት ማሽን ውስጥ የትኛውም ዓይነት አገልግሎት ሰጥተው የተጣሉ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብና በማስገባት ከዚያም የእፅዋቶችንና ኬሚካሎችን በመጠቀም የጫማ ቀለም ለማምረት የሚያስችል መሆኑን ይናገራል።

ልመንሕ አክሎም ለወደፊት ይህንን ምርታቸውን በፋብሪካ ማሳደግ ከቻሉ፤ በርካታ ሥራ አጥ ግለሰቦች የተጣሉ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብ የሥራ እድል ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ እንዲሁም የአካባቢ ደህንነት ጥበቃው ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ይናገራል።

እስካሁን ድረስ ለጥቁርና ቡኒ ቆዳ የጫማ የሚያገለግል ቀለም እያመረቱ መሆኑን የሚናገረው ላዕከ፣ በቀጣይ ለሌሎች ጫማዎችም የሚያገለግሉ የተለያዩ አይነት ቀለሞች ለማምርት እንደሚያስቡ ይናገራል።

በሚማሩበት ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ አቅራቢያ ምርታቸውን በርካሽ ዋጋ ለጫማ ጠራጊዎች መሸጥ መጀመራቸውን የሚገልፀው ላዕከ፣ ወደፊት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ይህንን ማሽንና ምርት ወደ ፋብሪካ ለማሳደግ ውጥን እንዳላቸው ይገልጻል።

ወጣቶቹ ይህ የጫማ ቀለም አሁን በገበያ ላይ ካሉት በምን ይለያል ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱ "ምርታችንን ሙሉ በሙሉ የምናመርተው ከወዳደቁ ፕላስቲኮች መሆኑ፣ ከምርት በኋላ የምንጥለው ተረፈ ምርት አለመኖሩ ይለየዋል" ሲል ላዕከ ያስረዳል።

በዋጋ ደረጃም በቀላሉ ከሚገኝ ጥሬ ዕቃ ስለሚያመርቱ በርካሽ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ ይገልፃሉ። ምርታችን በተማሪዎችና በሌሎች ጫማ ጠራጊዎች የተወደደበት ዐብይ ምክንያት በዋጋና ጫማን በቀላሉ ስለሚያስውብ ነው የሚለው ላዕከ ምርታቸውን ከየትኛውም ዓይነት የላስቲክ ምርት እንደሚያመርቱ ይገልፃል።

ልምንሕ አክሎም "በሀዋሳ ላለፉት አንድ ዓመት ምርቱን ጫማ ላይ ሞክረነው ምንም ዓይነት ጉዳት አለማስከተሉን አረጋግጠናል" በማለት ስራቸው ያለውን ጥራት ይናገራል።

ላዕከና ልመንሕ

የፎቶው ባለመብት, Icoglabs

አክሎም የሰራነው ማሽን የተለያዩ የፕላስቲክ ምርቶች ቢሰጠው እንደምርቱ ዓይነት ራሱን በመቀያየር ተፈላጊውን ቀለም እንዲያመርት ተደርጎ ነው የተሰራው ሲል ይገልጻል።

ወጣቶቹ የትዊተር ባለቤት፣ ጃክ፣ አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት አግኝቷቸው እንደነበር ሥራቸውንም በራሱ ገጽ ላይ ለማስተዋወቅ ቃል እንደገባላቸው ያስታውሳሉ።

እስካሁን ድረስ ምርታችንን ለማሻሻል በሐዋሳ፣ በአዳማ ዩኒቨርስቲ ቤተ ሙከራዎች ውስጥ በርካታ ጊዜ ማጥፋታቸውን የሚናገረው ላዕከ በአሁኑ ሰዓት ጥራቱን ስላሻሻሉትና ገበያው ላይ ጥሩ ተቀባይነት በማግኘታቸው ወደ ፋብሪካ ለማሳደግ የባለሀብቶችን ትብብር እየጠበቁ እንደሆነ ይናገራል።