ትውልደ ኢትዮጵያዊው የምክር ቤት አባል ስለአገሩ ወቅታዊ ሁኔታ ለፕሬዝዳንት ባይደን አስረዳ

የፎቶው ባለመብት, Oballa Oballa
በአሜሪካ በሚኒሶታ ግዛት የኦስቲን ከተማ ምክር ቤት አባል የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ ኦባላ በቅርቡ ክፕሬዝደንት ባይደን ጋር በተገናኘበት ወቅት፤ ስለወቅታዊው የኢትጵያ ሁኔታ አንስቶ አስተዳደራቸው ህወሓትን መደገፍ እንደሌለበት እንደነገራቸው ገለጸ።
ኦባላ ኦባላ ጆ ባይደንን ባገኛቸው ወቅት ከትውልድ ክልሉ ጋምቤላ በምን ሁኔታ ተሰዶ ከአገር እንደወጣ እና አሁን ኢትዮጵያ ስለምትገኝበት ሁኔታ ለፕሬዝደንቱ መናገሩን ለቢቢሲ አስረድቷል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር በተመለከተ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መልዕክት ካስተላለፈ በኋላ ፕሬዝዳንቱ የሰጡትን ምላሽም እንዲህ ገልጿል።
በአኛዋክ ሕዝብ ላይ ህወሓት አድርሶታል ያለውን በደለ እንዲሁም ከአገር ለመሰደዱ ምክንያት ይህ መሆኑን ለፕሬዝደንቱ መናገሩን ኦባላ ይገልጻል።
"ህወሓት የሐሰት መረጃ እያሰራጨ ነው። እኔ በህወሓት የተጀመረ የዘር ጭፍጨፋ ሰለባ ነኝ። ይህን ተናግሪያለሁ" ይላል ኦባላ።
"የአሜሪካ ፕሬዝዳንት እንዲሁ በቀላሉ ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም። ነገር ግን የደረሰብኝ እንግልት እንደሚያሳዝናቸው ነግረውኛል። ከዚያም አብረን ፎቶ እንድንነሳ ጠይቀውኝ ፎቶ ተነስተናል።"
ባይደን "ለወደፊቱ እንገናኛለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" እንዳሉት የተናገረው ኦባላ፤ ለወደፊቱ ዋይት ሐውስ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተገናኝቶ እንደሚወያይ ተስፋ ያደርጋል።
አሁን እየሆነ ያለው ነገር "ለእኔ የግል ጉዳይ ነው" ሲል ለቢቢሲ የሚናገረው ኦባላ፤ ጋምቤላ ውስጥ ተፈጸመ የሚለውን የዘር ጭፍጨፋ እስካሁን ድረስ "ማንም አላወራውም" በማለት ይገልጻል።
"እኔ ይህንን ለመናገር አልፈራም። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ህወሓት በጀመረው ጦርነት ብዙ ሰዎች እየተጎዱ ነው። መንግሥት ሰላም ነው የሚፈልገው" ሲልም አክሏል።
ላለፉት 27 ዓመታት ህወሓት በበላይነት ሥልጣን ጨብጦ በነበረበት ወቅት "የተገለሉ ብሔሮች አሉ" ሲልም ህወሓትን ይወቅሳል።
አሁን ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት "በአብላጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመረጠ ነው" የሚለው ኦባላ፤ "ህወሓት ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩን አውርዶ ወደ ሥልጣን መመለስ ይፈልጋል። ያሳዝናል" ሲልም አክሏል።
የ27 ዓመቱ ኦባላ ኦባላ የኦስቲን ከተማ ምክር ቤት አባል ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ያነበረው ጉዞ ምን እንደሚመስል ከቢቢሲ ተጠይቆ "እስካሁን ያለው ጉዞዬ ጥሩ ነው" ሲል መልስ ሰጥቷል።
በሚወክለው ከተማ ብዙ አበረታች ለውጦች እንዳሉ እና እሱም ተግቶ በመሥራት እንደሚገፋ አክሏል።
"ኦስቲን ከአሜሪካ ከተሞች ሁሉ በጣም የምትወደድ ከተማ ናት። ሰው ተቀባይ ነች። ማንም ሰው ሃብታምም ይሁን ድሃ፣ ከየትም መጥቶ ይኖርባታል። ኦስቲን ውስጥ ሁሉም ሰው ሠርቶ ስኬታማ መሆንም ይችላል።"
ኦባለ ከፕሬዝደንት ባይደን ጋር እንዴት ተገናኘ?
በሚኒሶታ ግዛት በምትገኘው ኦስቲን ከተማ የምክር ቤት አባል የሆነው ኦባላ ኦባላ ከአሜሪው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር ፊት ለፊት የተገናኘበትን አጋጣሚ አስረድቷል።
ኦባላ "ፕሬዝደንቱን ፊትለ ለፊት ማግኘት ትልቅ ነገር ነው" ይላል።
ምንም እንኳ ኦባላ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ወቅት ፕሬዝደንቱን ማግኘት ባይችልም የፕሬዝደንቱ መኖሪያ እና መስሪያ ቤት የሆነውን ዋይት ሐውስ ከአንድ ዓመት በፊት ጎብኝቶ እንደነበረ ያስታውሳል።
"ሰኞ ዕለት ከሚኒሶታ ግዛት ስልክ ተደውሎልኝ ፕሬዝደንቱ ወደ ሚኒሶታ እንደሚመጡ ተነገረኝ። 'ለአንተ ቦታ አለን' አሉኝ። በጣም ተደስተኩ" በማለት ኦባላ ይናገራል።
ባይደን በሚኒሶታ ግዛት ተገኝተው በቅርቡ ስላጸደቁት ሕግ ንግግር ካደረጉ በኋላ እየተዘዋወሩ ሰዎችን ማነጋገር ጀመሩ።
በዕለቱ ፕሬዝደንቱን የማግኘት እድል የነበራቸው የግዛት አስተዳዳሪዎች እና ሴናተሮች ነበሩ የሚለው ኦባላ፤ የሚኒሶታ ግዛት አስተዳዳሪ ጠጋ ብዬ ለፕሬዝደንቱ ሰላምታ እንድሰጥ አበረታቱኝ ይላል።
"ይህ በሕይወት ዘመን እንዴ ያሚያጋጥም እድል ነው። ጠጋ ብዬ 'ሚስተር ፕሬዝደንት' ብያቸው ሰላምታ ተለዋወጥን። ቀልባቸውን መሳብ ቻልኩ። ከዚያ መጡና ስሜን ጠይቁኝ" በማለት ኦባላ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።
"ስሜ ኦባላ ኦባላ መሆኑንና የኦስቲን ከተማ ምክር ቤት አባል መሆኔን ነገርኳቸው። ኦስቲን ስላቸው ከኦስቲን ቴክሳስ መስሏቸው ነበር።"
ኦባላ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ፎቶ ከተነሳ በኋላ "እያደረግክ ያለኸውን መልካም ነገር ቀጥልበት" እንዳሉትም ለቢቢሲ ገልጿል።
ዲሞክራቱ ባይደን ዶናልድ ትራምፕን በማሸነፍ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በተመረጡበት ያለፈው ዓመት ምርጫ ወቅት ነበር ከኢትዮጵያ በስደት የሄደው ኦባላ ኦባላ በሚኒሶታ ግዛት ለኦስቲን ከተማ ምክር ቤት የተመረጠው።
በዚህም የኦስቲን ከተማ ነዋሪዎች የአሜሪካ ዜግነትን ካገኘ ረጅም ጊዜ ያልሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ስደተኛ የምክር ቤት አባል እንዲሆን መርጠውታል።
ወጣቱ ኦባላ ገና የ28 ዓመቱ ሲሆን ከዓመታት በፊት በምዕራብ ኢትዮጵያ ጋምቤላ ውስጥ በአኝዋክ ብሔር አባላት ላይ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከተፈጸመው ጥቃት በመሸሽ ነበር ከአገሩ የወጠው።
ኦባላ በስደት ባቀናባት አሜሪካ ውስጥ ለዓመታት ከቆየ በኋላ የምክር ቤት አባል ለመሆን የሚኣስፈልገውን ዜግነት ያገኘው ከሁለት ዓመት በፊት ገደማ ነበር።












