ኪፕቾጌ በቶኪዮ የኦሎምፒክ ማራቶን ሻምፒዮንነቱን አስጠበቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኬንያዊው አትሌት ኢሉይድ ኪፕቾጌ በተከታታይ የማራቶን ኦሎምፒክን በማሸነፍ ሻምፒዮንነቱን አስጠብቋል።
በአውሮፓውያኑ 1980 የኦሎምፒክ ሻምፒዮንነቱን ያስጠበቀውን ሌላኛውን የአገሩን አትሌትም ተክቷል ተብሏል።
በተከታታይ የኦሎምፒክ ማራቶን ውድድሮችን በማሸነፍ የአለማችን ሶስተኛው አትሌት ኪፕቾጌ ውድድሩን በሁለት ሰዓት ከስምንት ደቂቃዎች ከ38 ሰኮንድ አጠናቋል።
በተከታታይ የኦሎምፒክ ማራቶን በማሸነፍ ከታሪክ መዝገብ ስሙ የሰፈረው ኢትዯጵያዊው አበበ ቢቂላ ነው።
በአለማችን ላይ ታላቁ የማራቶን ሯጭነትን ስፍራ ያገኘው የ36 አመቱ ኪፕቾጌ ከኔዘርላንዱ አትሌት አብዲ ናጌዬ በአንድ ደቂቃ ከ 20 ሰኮንድ ቀድሞም ነው ውድድሩን ያጠናቀቀው።
በዚህ ውድድር ላይ ሶስተኛ ሆኖ ውድድሩን ያጠናቀቀው ቤልጂየማዊው በሽር አብዲ ነው።
ኢትዮጵያን ወክለው በርቀቱ የተወዳደሩት አትሌቶቻችን ውድድራቸው ለማቋረጥ ተገደዋል።
የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ኪፕቾጌ ከውድድሩ በኋላም " ለሁለተኛ ጊዜ በተከታታይ የማራቶን ውድድር በማሸነፍ ራዕዩን ያስፈፀምኩኝ ይመስለኛል። ቀጣዩን ትውልድ አነሳሳለሁ ብየም ተስፋ አደርጋለሁ" በማለት ተናግሯል።
"በዚህ ሁሉ ውዥንብር ውስጥ ሆኖ የቶኪዮ ኦሎምፒክ ሊከናወን ችሏል። ይሄ ትልቅ ነገር ነው። ተስፋ አለ ማለት ነው። ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ በትክክለኛው ጎዳና ላይ ነን ማለት ነው" በማለት አትሌቱ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግሯል።
አክሎም " ወደተለመደው ህይወታችን ለመመለስ መንገዱን ጀምረናል ይሄም ነው የኦሎምፒክ ትርጉሙ" ብሏል።
"የሻምፒዮን ማዕረጌን ማስጠበቄና ለቀጣዩም ትውልድ በማሳየቴ ደስተኛ ነኝ። ስፖርቱን አንድ ሰው አክብሮ በስርዓት መቀጠል ከተቻለ ህልማቸውን ዕውን ማድረግ ይቻላል" በማለትም ምክሩን አስተላልፏል።
ከሁለት ሰዓት በታች በመሮጥ አለምን ላስደመመው አትሌት የቶኪዮ አራተኛ የኦሎምፒክ ሜዳልያው ነው።














