አትሌት ሹራ ቂጣታ የአበበ ቢቂላን የቶኪዮ ኦሊምፒክ ታሪክ ለመድገም እቅድ አለኝ አለ

ሹራ ቂጣታ

የፎቶው ባለመብት, Emilee Chinn/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ሹራ ቂጣታ

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የወንዶች የማራቶን ውድድር ትልቅ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ሹራ ቂጣታ የአበባ ቢቂላን የቶኪዮ ኦሊምፒክ ታሪክ ለመድገም እቅድ አለኝ አለ።

"አበበ ቢቂላ ባስገኘው ድል ለአገር ትቶ ያለፈውን ታሪክ ለማስመለስ ጥረት እያደረግን ነው። ይህን ውድድር አሸንፌ የአበበ ቢቂላን ታሪክ ወደ አገር ቤት ለመመለስ ሐሳብ አለኝ" ሲል አትሌት ሹራ ቂጣታ ለቢቢሲ ተናግሯል።

አበበ ቢቂላ አእአ በ1964 በቶኪዮ ተካሂዶ በነበረው የኦሊምፒክ መድረክ በማራቶን ውድድር ተወዳዳሪዎቹን ከ4 ደቂቃዎች በላይ ጥሎ በመግባት ማሸነፉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድንም በዘንድሮው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በማራቶችን ወርቅ በማምጣት የአበበ ቢቂላ የማራቶን ድል ለመድገም ከፍተኛ መነሳሳት ውስጥ እንዳለ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ደራርቱ ቱሉ ትናገራለች።

በኦሊምፒክ መድረክ ወርቅ የወሰደችው የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ደራርቱ ቱሉ፤ "አበበ ቢቂላ ያስመዘገበው ድል ዛሬ የሆነ ይመስለኛል" ትላለች።

በዘንድሮው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ለማሸነፍ ጠንካራ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁማለች።

"እኛም አገርም የወርቅ ሜዳሊያ እንጠብቃለን" ያለው ደግሞ በማራቶን ውድድሩ ተስፋ የተጣለበት አትሌት ሹራ ቂጣታ ነው።

"እኛ የወርቅ ሜዳሊያ እየጠበቅን ነው። አገርም እንዲሁ የወርቅ ሜዳሊያ ያመጠሉ ብሎ ይጠብቀናል" በማለት አትሌት ሹራ ቂጣታ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በኦሊምፒክ መድረክ አገሩን ሲወክል የመጀመሪያ ጊዜ የሆነው ሹራ፤ "በራስ በመተማመን የሚሮጥ ሰው ሊያሸንፍ ይችላል" በማለት ይናገራል።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ በወንዶች ማራቶችን አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

በሮም እና በቶኪዮ ኦሊምፒክ አበበ ቢቂላ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለአገሩ አስገኝቷል። እአአ በ1968 በተካሄደው የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ደግሞ ማሞ ወልዴ ወርቅ ሲያስገኝ ገዛኸኝ አበራ በሲድኒ ኦሊምፒክ ወርቁን ወስዷል።

አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ አሸናፊ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Maja Hitij

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ ከሁለት ዓመት በፊት በተደረገው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ አሸናፊ ነበር።

በወንዶች ማራቶን እነማን ተጠባቂ ናቸው?

ኢትዮጵያን በወንዶች ማራቶን የሚወክሉት አትሌቶች ሹራ ቂጣታ፣ ለሊሳ ዴሲሳ እና ሲሳይ ለማ ናቸው።

በወንዶች ማራቶን የአሸናፊነት ግምቱ የተሰጠው ኬኒያዊው ኢሊዩዲ ኪፕቼጌ ነው። ኪፕቾጌ የርቀቱ ክብረ ወሰን ባለቤት ከመሆኑም በላይ በሪዮ ኦሊምፒክም የወቅት ሜዳሊያ አሸንፏል።

ከአንድ ዓመት በፊት በተደረገው የለንደን ኦሊምፒክ ግን ሹራ ኬንያዊውን ኪፕቾጌን ማሸነፍ ችሎ ነበር።

ኪፕቾጌ፤ "በኦሊምፒክ አሁንም ወርቅ ማግኘት እፈልጋለሁ። ይህን ማድረግ ከቻልኩ ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው" በማለት ለሮይተርስ ተናግሯል።

ኪፕቾጌ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ድል ከቀናው በተከታታይ የማራቶን ውድድር በማሸነፍ የአበበ ቢቂላን ታሪክ ይጋራል።

ኢትዮጵያ ከኪፕቾጌ ቀጥሎ በማራቶን ፈጣን ሰዓት ያለውን አትሌቷ ቀነኒሳ በቀለን ትታ ነው ወደ ቶኪዮ ያቀናችው።

ቀነኒሳ የኦሊምፒክ ማጣሪያ ላይ ለመወዳደር ፍቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ በዚህ ውድድር አይሳተፍም ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እንደነ ሹራ ባሉት ጠንካራ አትሌቶች ተስፋ ሰንቃለች።

ሌላኛው ተጠባቂ አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ ነው። አትሌት ሌሊሳ ከሁለት ዓመት በፊት በኳታር፣ ዶሃ በተደረገው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በማራቶን የወርቅ አሸናፊ ነበር።

አትሌት ሲሳይ ለማ ደግሞ በ2020 ሎንዶን ማራቶን ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል።

line

በቶኪዮ ከፍተኛ ሙቀት ስላለ የማራቶን ውድድሩ ከቶኪዮ ከተማ በ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሳፖራ ከተማ ይከናወናል።

ውድድሩ የፊታችን እሁድ ይካሄዳል።