ሰሜን ኮሪያ የባይደን አሜሪካ 'ጠብ ጫሪ ናት' ስትል ኮነነች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የባይደን አስተዳደር ከሰሜን ኮሪያ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ ይፋ ሊያደርግ ነው።
ይህን ተከትሎ ፒዮንግያንግ የወቅቱን የአሜሪካ አስተዳደር ተችታለች።
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በቅርቡ የአሜሪካ መንግሥት የሰጠው አስተያየት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን 'ጠብ ጫሪ ፖሊሲ' እንዳላቸው የሚያሳይ ነው ብሏል።
በያዝነው ሳምንት መባቻ ጆ ባይደን የሰሜን ኮሪያን የኒውክሊዬር ፕሮግራም ለዓለም ደህንነት 'አስጊ' ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ዋይት ሃውስ እንደሚለው ፕሬዝደንቱ ሰሜን ኮሪያን በተለመከተ "ጥንቃቄ የታከለበት" ፖሊሲ እንዲኖራቸው ይሻሉ።
የባይደን አስተዳደር ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ባለው አርብ እንዳሉት አዲሱ አስተዳደር ሰሜን ኮሪያን እንዴት መቅረብ እንዳለበት የሚያሳይ ስትራቴጂ አውጥቷል።
ቃል አቀባይዋ አክለው ባይደን ሞክሮ ካልተሳካለት ካለፈው አስተዳደር ተምረው ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ፕሮግራሟን እንድታቆም ያደርጋሉ ብለዋል።
"ዩናይትድ ስቴትስ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ዲፕሎማሲን በመጠቀም ከሰሜን ኮሪያ ጋር ግንኙነት ታደርጋለች።" ሲሉ ቃል አቀባይዋ አክለዋል።
አሜሪካ በቅርቡ ከጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪዎች ጋር ስለ ሰሜን ኮሪያ ትመክራለች።
በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ መልዕክት የሰሜን ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባይደን ከሰሞኑ ያደረጉትን ንግግር "ትዕግስት አልባ" እንዲሁም "አወዛጋቢ" ነው ብሏል።
"ለግማሽ ምዕተ አመታት እንደነበረው የባይደን አስተዳደርም በሰሜን ኮሪያ ላይ ጠብ አጫሪ ፖሊሲ ለመተግበር እንደተዘጋጀ የሚያሳይ ነው" ብሏል ሚኒስቴሩ።
በሌላ መግለጫ ደግሞ ይኸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን ሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከተ የሰጠችው አስተያየት "የመሪያችን ኪም ጆንግ ኡን ክብር የሚነካ ነው" ሲል የባይደንን አስተዳደር ኮንኗል።
ሚኒስቴሩ ለየትኛው የዋሺንግተን አስተያየት መልስ እንደሰጠ ግልፅ ባይሆንም ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ አሜሪካ የሰሜን ኮሪያን ሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚመለከት መልዕክተኛ ልትሾም ነው የሚል ጽሑፍ አትሞ ነበር።
ሥልጣን ከያዙ 100 ቀን መድፈናቸውን ተከትሎ ለላይኛውና ታችኛው ምክር ቤት ንግግር ያሰሙት ባይደን የሰሜን ኮሪያን የኢራን ኒውክሌር ፕሮግራም "ለአሜሪካና ለዓለም ስጋት ነው" ብለዋል።
ዋሺንግተን ከፒዮንግያንግ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመሥረት ከባለፈው ወር ጀምሮ ጥረት እያደረገች እንዳለ ይፋ አድርጋለች።
እስካሁን ድረስ ሰሜን ኮሪያ ለጆ ባይደን አስተዳደር እውቅና አልሰጠችም።
ባይደን ፕሬዝደንት ሆነው ከመሾማቸው በፊት ኪም ጆንግ ኡንን "ቦዘኔ" ብለዋቸው ነበር።
ባይደን ሥልጣን ከያዙ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ንግግር ያሰሙት ኪም አሜሪካን የሃገራቸው "ትልቋ ጠላት" ሲል እንደገለጿት ይታወሳል። ነገር ግን ዲፕሎማሲን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገቡም ተናግረው ነበር።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኪም ጋር ሦስት ጊዜ በመገናኘት ታሪክ ሠርተዋል።
ነገር ግን በሦስቱም ስብሰባዎች ሁለቱ መሪዎች ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም።












